1 እሽመ-ዳጋን

1 እሽመ-ዳጋን ከ1688 እስከ 1678 ዓክልበ. ('ኡልትራ አጭሩ' አቆጣጠር[1]) የአሦር ንጉሥ ነበረ። አባቱ 1 ሻምሺ-አዳድ የአሦር ንጉሥ እየሆነ፣ ልጁን እስመ-ዳጋንን በኤካላቱም ዙፋን ላይ አስቀምጦት ነበር። ታናሹ ወንድሙ ያስማሕ-አዳድ ደግሞ የማሪን ዙፋን ተቀበለው። በባቢሎን ንጉሥ ሃሙራቢ 17ኛው አመት (በ1688 ዓክልበ.) 1 ሻምሺ-አዳድ እንደ ሞቱ ልጁም እሽመ-ዳጋን የአሦርን መንግሥት እንደ ወረሰው ይታወቃል።

እሽመ-ዳጋን የወረሰው የ1 ሻምሺ-አዳድ መንግሥት

በዘመኑ መጀመርያ፣ የሑራውያን ቱሩኩ ጎሣ አለቃ ሊዳይ ጽኑ አመጽ በሹሻራ አገር አስነሣሣ። ክፍላገሩ በተለይ ተራራማ ስለ ሆነ፣ እሽመ-ዳጋን የአሦርን ሠራዊት ሹሻራን እንዲተው አደረገ። ከዚያ ግን ኡታን አገር አሸነፈ። በተሸነፈው አገር በኡታ ሥልጣኑን ለመጠብቅ፣ ወንድሙን ያስማሕ-አዳድ ከማሪ ወደ ኡታ እንደራሴነት አዛወረው። በስደት የኖረው የማሪ ቀድሞ ንጉስ ዚምሪ-ሊም በዚያ ዕድሉን አገኝቶ ማሪን ከያስማሕ-አዳድ ነጥቆ ወደ ዙፋኑ ተመለሰ።

በእሽመ-ዳጋን ዘመን፣ አሦር ከማሪ፣ ከኤሽኑና እና ከኤላም ጋራ ጦርነት ያደርግ ነበር። ስለዚህ እሽመ-ዳጋን ከበፊቱ ጠላቶች ከቱሩኩ ሕዝብ ጋር የስምምነት ውል አደረገ። የቱሩኩ አለቃ ዛዚያ ሴት ልጅ ለእሽመ-ዳጋን ወንድ ልጅ ለሙት-አሽኩር ታጨች። በዚህ ወቅት ደግሞ የባቢሎን ሃይል እየበረታ አሦር ከባቢሎን ወዳጅነት ተጠቀመ። ሆኖም እሽመ-ዳጋን የአባቱን ግዛት በሙሉ ሊጠብቅ አልተቻለውም። በመጨረሻ ግዛቱ የኤካላቱም፣ አሹርነነዌ ከተሞች ዙሪያ ብቻ ያጠቅልል ነበር።

ማሪ ጽሑፎች እንደሚዘገብ፣ በዚምሪ-ሊም 9ኛው አመት (በ1679 ዓክልበ.)፣ ኤላማውያን እሽመ-ዳጋንን ከአገሩ አባረሩትና ወደ ባቢሎን ሸሸ። በዚያ በጽናት ታመመ። እሽመ-ዳጋን ማዕረጉን በይፋ ቢጠብቅም የሃሙራቢን ሥልጣን እንዲቀብል ተገደደ። በዝምሪ-ሊም 11ኛው አመት እሽመ-ዳጋን ዙፋኑን ለልጁ ለሙት-አሽኩር እንደ ተወው ይታወቃል። ሙት-አሽኩር ይቅርና ብዙ ሌሎች ሰዎች ዙፋኑን ለመያዝ ሞከሩ። ከነዚህም አሹር-ዱጉል አገሩን ለጥቂት አመት እንዲገዛ በቃ።

የዓመት ስሞች

የአሦር ነገሥታት ዝርዝር እሽመ-ዳጋን ለ40 አመት እንደ ነገሠ ሲል፣ አሁን ከሃሙራቢ ፲፯ኛው እስከ ዝምሪ-ሊም ፲፩ ኛው ዓመት መግዛቱ ስለሚታወቅ፣ ዘመኑ ፲፩ ዓመታት ብቻ እንደ ቀረ ማለት እንችላለን።[2] ባለፈው ቅርብ ጊዜ ደግሞ (1995 ዓ.ም.) ተጨማሪ ሰነዶች በካነሽ (በዛሬው ቱርክ) በመገኘታቸው የዚሁ ዘመን «ሊሙ ስሞች» ማወቅ ትችሏል።

የያንዳንዱ አሦራዊ ዓመት ስም ለዚያ ዓመት የተሾመው የሊሙ ስም ነበረ። ከዚህ በታች የዓመቱ ሊሙ እና የሊሙ አባት ስም እንደ ኡልትራ አጭር አቆጣጠር ይዘርዝራሉ።[3]

1688 ዓክልበ. - ጣብ-ጺላ-አሹር / ኤናም-አሹር፣ አሹር-ታክላኩ ልጅ
1687 ዓክልበ. - አሹር-ኤሙቂ
1686 ዓክልበ. - አቡ-ሻሊም
1685 ዓክልበ. - ፑሣኑም፣ አዳድ-ራቢ ልጅ
1684 ዓክልበ. - ኢኩፒ-እሽታር፣ አቡ-ሻሊም ልጅ
1683 ዓክልበ. - አሂያ፣ ታኪኪ ልጅ
1682 ዓክልበ. - በሊያ፣ ኤና-ሲን ልጅ
1681 ዓክልበ. - ኢሊ-ባኒ፣ ፑሣያ ልጅ
1680 ዓክልበ. - አሹር-ታክላኩ፣ ኢላፕራት-ባኒ ልጅ
1679 ዓክልበ. - ሳሣፑም፣ አሹር-ማሊክ ልጅ
1678 ዓክልበ. - አሁ-ዋቃር

ዋቢ መጽሐፍት

  1. http://chronosynchro.net/base.php?page=accueil (ፈረንሳይኛ)
  2. Gasche et al., Dating the Fall of Babylon, 1998 እ.ኤ.አ., p.52.
  3. የመስጴጦምያ ነገሥታት (ፈረንሳይኛ)
  • Jean-Marie Durand, Documents Epistolaires du Palais de Mari, Collection « Littérature Ancienne du Proche-Orient » N° 16. (1997); (2002) ISBN 2204056855 (ፈረንሳይኛ)
ቀዳሚው
1 ሻምሺ-አዳድ
የአሦር ንጉሥ
1688-1678 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
አሹር-ዱጉልሙት-አሽኩር
8 ሌሎች ተፎካካሪዎች
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.