1 ሰኑስረት
ኸፐርካሬ 1 ሰኑስረት (ወይም ሰንዎስረት) ግብጽን በመካከለኛ መንግሥት (12ኛው ሥርወ መንግሥት) ከ1972 እስከ 1938 ዓክልበ. ግድም ድረስ የገዛ ፈርዖን ነበረ። የአባቱ 1 አመነምሃት ተከታይ ነበር።
1 ሰኑስረት | |
---|---|
የሰኑስረት ምስል | |
የግብጽ ፈርዖን | |
ግዛት | 1972–1938 ዓክልበ.? |
ቀዳሚ | 1 አመነምሃት |
ተከታይ | 2 አመነምሃት |
ባለቤት | 3 ነፈሩ |
ሥርወ-መንግሥት | 12ኛው ሥርወ መንግሥት |
አባት | 1 አመነምሃት |
በ፲ኛውና በ፲፰ኛው ዓመት በኩሽ መንግሥት ላይ እንደ ዘመተ ይታወቃል። ሆኖም ሰኑስረት በአባቱ በ፩ አመነምሃት ፳ኛው ዓመት (1982 ዓክልበ. ግድም) በጋርዮሽ ዘውዱን ስለ ተጫነው፤ መጀመርያው ዓመቱ ከዚያ ይቆጠራል። ስለዚህ በኩሽ ላይ የዘመቱ በ1972ና በ1964 ዓክልበ. ግድም ይሆናል። የግብጽ ደቡብ ጠረፍ ከኩሽ ጋራ ከ፩ኛው ሙላት እስከ ፪ኛው ሙላት አስፋፋው።[1] በተጨማሪ ሎሌዎችን ወደ ሲና ልሳነ ምድር ለማዕድን እንደ ላከ ይታወቃል።
የሲኑሄ ታሪክ በተባለው ጽሑፍ ዘንድ፣ አባቱ አመነምሃት በዋና ከተማው በኢጭታዊ እየነገሠ፣ የጋርዮሽም ንጉሥ ኸፐርካሬ ሰኑስረት በ«ጤሄኑ» (ሊብያ) እየዘመተ፣ ያንጊዜ በድንገት አመነምሃት ዓረፈ። (ይህ ከሤራ የተነሣ መሆኑ ቢመስልም ግልጽ አይደለም)። ወዲያው ሰኑስረት በአስቸኳይ ወደ ኢጭታዊ ተመለሠ። የሰኑስረት አለቃ ሲኑሄ ግን ወደ ግብጽ እንዳይመለስ ሁከት ፈርቶ እስከ «ረጨኑ» (ስሜን ከነዓን) ድረስ ይሸሻል። በዚያ ሲኑሄ የረጨኑ አለቃ አሙነንሺ ባለሟልና ጦር አለቃ ሆነ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ሲኑሄ ሽማግሌ ሆኖ ወደ አገሩ ወደ ሰኑስረት ግቢ ሲመልስ፣ የ«ፈንቁ» (ፊንቄ) አለቃ መኑስ እና የ«ቀደም» (?) አለቃ መኪ የፈርዖን ወዳጆች እንደ ሆኑ ይገልጻል። ይህ ጽሑፍ እንደ ልብ ወለድ ቢቆጠረም፣ ታሪካዊ መሠረት መኖሩ የሚከራከር ነው።
ሰኑስረት በግብጽ ብዙ ህንጻዎችና መቅደሶች አንዳሠራ ይታወቃል። አሁን በተለይ የሚታወቀው በካርናክ እንደገና ታድሶ የሚታየው «ነጭ መቅደስ» ነው። ከአማካሪዎቹ መጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስትር እንተፊቀርና ከዚያ ሰኑስረት ይታወቃሉ፤ እንዲሁም ባጀሮንዱ ሶበክሆተፕና ባጀሮንዱ መንቱሆተፕ ይታወቃሉ።
ማኔጦን (280 ዓክልበ. ግድም ጽፎ) ይህን ንጉሥ በግሪክኛ «ሰሶንኾሲስ» ይለዋል። የ2 ሰኑስረት ስም ግን «ሰሶስትሪስ» ስለሚለው፣ ይህም ስም ከሌላ ምንጮች የገነነ ስለሆነ፣ አንዳንዴ ይህም ፩ ሱኑስረት በግሪክ «ሰሶስትሪስ» ይባላል።
በሰኑስረት ዘመነ መንግሥት በ፵፫ኛው ዓመት (1940 ዓክልበ. ግድም) ልጁን 2 አመነምሃትን ከእርሱ ጋር በጋርዮሽ ወደ ዙፋኑ አስነሣው። የቶሪኖ ቀኖና የሚባለው የፈርዖኖች ዝርዝር ፵፭ ዓመታት እንደ ገዛ ስለሚለን፣ ከዚህ ሁለት ዓመት በኋላ በ1938 ዓክልበ. ግድም ሰኑስረት ዓረፈና ፪ አመነምሃት ለብቻው ፈርዖን ሆነ ይመስላል።
- የ፩ ሰኑስረት ሐውልት በሄሊዮፖሊስ
- የ«ኸፐርካሬ» ስም በአቢዶስ ነገሥታት ዝርዝር
- የ፩ ሰኑስረት ምስል
ቀዳሚው 1 አመነምሃት |
የግብፅ ፈርዖን 1972-1938 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ 2 አመነምሃት |