ፓርጦሎን
ፓርጦሎን በአየርላንድ ልማዳዊ አፈ ታሪክ ዘንድ ከማየ አይኅ ጥቂት ክፍለ ዘመናት ቀጥሎ መጀመርያው በአይርላንድ ደሴት ላይ የደረሱት ሰፈረኞች መሪ ወይም ንጉሥ ነበር።
የፓርጦሎን ስም በታሪክ መጻሕፍት መጀመርያው የሚታወቅ በ820 ዓ.ም. አካባቢ በሮማይስጥ በተጻፈው ሂስቶሪያ ብሪቶኑም («የብሪታንያውያን ታሪክ») ሊገኝ ይችላል። በዚሁ ጽሁፍ መሠረት፣ «ፓርጦሎሙስ» ከ1 ሺህ ሠፈረኞች (ወንዶችና ሴቶች) ጋር ደረሰ፣ እስከ 4 ሺህም ድረስ ቶሎ ተባዙ፣ ነገር ግን ድንገት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁላቸው ከቸነፈር ሞተዋልና አገሩ እንደገና ባዶ ሆነ።[1] ይኸው መጽሐፍ በአየርላንድኛ ትርጉም ደግሞ ቸነፈሩ በፓርጦሎን ሕዝብ ላይ የመጣበት ጠንቅ ፓርጦሎን ከኗሪ አገሩ ገና ሳይወጣ ወላጆቹን ገድሎአቸው ስለ ነበር የአምላክ ፍርድ ነው በማለት ይጨምራል።
ከዚህ በላይ የፓርጦሎን መነሻ አገር እስኩቴስ እንደ ነበር፣ የማጎግ ተወላጅ እንደ ነበር ይታመን ነበር። የስኮት (በስኮትላንድና ቀድሞ በአይርላንድ የተገኘ) ብሔር ስም ከዚህ እስኩቴስ እንደ መጣ በድሮው መጻሕፍት በሰፊው ይጻፍ ነበር።
በኋላ የተጻፉ ሌሎች የአይርላንድ ታሪክ መጻሕፍት ስለ ፓርጦሎን ብዙ ዝርዝር ጨምረዋል። በተለይ በ1100 ዓ.ም. ግድም በተጻፈው መጽሐፍ ሌቦር ገባላ ኤረን («የአይርላንድ ወረራዎች መጽሐፍ») ትውልዱ ፓርጦሎን ወልደ ስሩ ወልደ ባንባ ወልደ ማጎግ ይሠጣል። (ይህ ትውልድ ግን በየቅጂው እጅግ ይለያያል።) እርሱና ሦስት ልጆቹ (ላይግሊን፣ ስላንጋና ሩድራይግ) መሪዎች ሆነው 1 ሺህ ሠፈረኞች (ወንዶችና ሴቶች) ወደ አይርላንድ አመጡ። 7 ዓመት ከደረሱ በኋላ መጀመርያው የሞተው ሰው እሱም ፌአ ተብሎ ተቀበረ። 10 አመት ከደረሱ በኋላ የፓርጦሎን ሠራዊት በፎሞራውያን ላይ በማግ ኢጠ ውግያ አሸነፉ። እነዚህ ፎሞራውያን በመሪያቸው ኪቆል ግሪከንቆስ ተመርተው ከውጭ አገር የወረሩ መርከበኞች ነበሩ። ፓርጦሎን በአይርላንድ በደረሰበት ጊዜ 9 ወንዞች፣ 3 ሐይቆችና 1 ሜዳ ብቻ ነበሩ። በእርሱ ዘመን ግን 4 ተጨማሪ ሜዳዎች ተጣሩ፣ ከዚህ በላይ 7 ተጨማሪ ሐይቆች በተአምር ተፈጠሩ። በመጨረሻ ግን ፓርጦሎንና ሕዝቡ በሙሉ - 5 ሺህ ወንዶችና 4 ሺህ ሴቶች - በአንድ ሳምንት ውስጥ በቸነፈር አንድላይ ዓረፉ። (በሌላ ክፍል የጊላ ኮማይን ግጥም ሲጠቅስ ይህ የፓርጦሎን ወገን ከደረሰ 300 አመታት በኋላ ይለዋል።) ደሴቱም ከዚያ ለ30 አመት ባዶ ሆኖ ቀረ። ከዚህ በላይ ስለ ፓርጦሎን መንግሥት ብዙ ተጨማሪ ዝርዝሮች በሌቦር ገባላ ኤረን ይገለጻሉ[2]።
በ1620 ዓ.ም. ግድም የተቀነባበረው ምንጭ የአራቱ ሊቃውንት ዜና መዋዕሎች ደግሞ ተመሳሳይ ታሪክ ያቀርባል። አንዳንድ ዝርዝር ለምሳሌ የፎሞራውያን ቁጥር 800 እንደ ነበር ይጨምራል። በዚህ አቆጣጠር ፓርጦሎን 30 አመታት ከነገሠ በኋላ አረፈ፤ ሌሎቹ 9000 ሕዝብ ግን ከዚያ 270 ዓመታት በኋላ በቸነፈር ጠፉ።[3] በ1625 ዓ.ም. አካባቢ የታተመው የሴጥሩን ኬቲን ታሪክ መጽሐፍ የአይርላንድ ታሪክ ደግሞ ስለ ፓርጦሎን ተመሳሳይ አፈ ታሪኮች የሚያቀርብ ነው። በእርሱ መጽሐፍ ፎሞራውያን ከካም ዘር የወጡ መርከበኞች ነበሩ።[4]
ከፓርጦሎን ሕዝብ በኋላ የደረሱት ወገኖች የነመድ፣ ፊር ቦልግ፣ ቱዋጣ ዴ ዳናን እና ሚሌሲያን ነገዶች ሁላቸው ከማጎግ ወይም ከጋሜር ዘር እንደ ነበሩ በአይርላንድ ልማዶች ይባላል። ከነዚሁ መጨረሻዎቹ የሚሌሲያን ነገድ የደረሱ ከእስፓንያ መሆኑ ይተረካል። የሚሌሲያንና የፓርጦሎን ታሪኮች ግን ትንሽ እንደ ተደናገሩ ይመስላል። ስለዚህ በብዙ ምንጮች ዘንድ የፓርጦሎን ወገን ከእስኩቴስ ወደ አይርላንድ የደረሰው እንደ ሚሌሲያን በሜድትራኒያን ባሕርና በእስፓንያ በኩል በመጓዝ እንደ ነበር ይጻፋል።
ዋቢ መጽሐፍት
- ሂስቶሪያ ብሪቶኑም (እንግሊዝኛ)
- ሌቦር ገባላ ኤረን (እንግሊዝኛ)
- የአራቱ ሊቃውንት ዜና መዋዕሎች (እንግሊዝኛ)
- የአይርላንድ ታሪክ (እንግሊዝኛ)