ፑዙር-ኒራሕ

ፑዙር-ኒራሕሱመራዊ ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ አክሻክሱመር ላዕላይነቱን በያዘበት ጊዜ የአክሻክ ንጉሥ ነበር።

በዚህ ዘመን ላዕላይነት ማለት የሱመር ዋና ከተማ ኒፑርን የገዛው ወገን ነበር። በብዙ ቅጂዎች ዘንድ፥ ከማሪ ንጉሥ ሻሩም-ኢተር ዘመን በኋላ ማሪ ተሸነፈና የሱመር ንጉሥነት ከማሪ ወደ አክሻክ ተዛወረ። እንዲህ ከማለት ቀጥሎ 6 የአክሻክ ነገሥታት ስሞች ይዘርዝራል። ኡንዚ፣ ኡንዳሉሉ፣ ኡሩር፣ ፑዙር-ኒራሕ፣ ኢሹ-ኢል እና ሹ-ሲን ናቸው። ሹ-ሲን የኢሹ-ኢል ልጅ ቢባልም ከዓመታቸው ቁጥር በቀር ምንም ሌላ መረጃ አይጨምርም። በአንዳንድ ቅጂ ግን የፑዙር-ኒራሕ ስም ፑዙር-ሳሃን ተብሎ ተጽፏል። የፑዙር-ኒራሕ ትርጉም ፍች ከአካድኛው ፑዙር «ሥዩመ» እና ኒራሕ «የአረመኔ እባብ ጣኦት» ነው። በዝርዝሩ ዘንድ 20 ዓመታት ገዛ።

እነዚህ ሁሉ የአክሻክ ገዦች ወይም ከንቲቦች ቢሆኑም፣ ሁላቸው በመላ ሱመር ላዕላይነቱን እንደ ያዙ አይመስልም። ከነዚህ 6 የአክሻክ ገዢዎች አንዱ ብቻ እሱም ፑዙር-ኒራሕ ከሌላ ምንጭ ይታወቃል። ሌሎቹ 5 አንዳችም ትዝታ ወይም ቅርስ አላስቀሩልንም። ስለዚህ ከ6ቱ ገዢዎች ፑዙር-ኒራሕ ብቻ የመላ ሱመር ላዕላይነት የያዘ ነበር የሚል ሀሣብ ቀርቧል።[1]

ሌላው ፑዙር-ኒራሕን የሚጠቅሰው ሰነድ የባቢሎን መቅደስ ዜና መዋዕል (ወይም «የቫይድነር ዜና መዋዕል» [2]) የተባለው ጽላት ነው። ዜና መዋዕሉም እንዲህ ይተርካል፦

( <...> ጽሕፈቱ የጠፋበት ሕዋእ ለማመልከት ነው። ጽላቱ እራሱ ቅጂ ሆኖ «[ጠፍቷል]» የሚለው ማመልከቻ ቃል በጽላቱ ላይ ይታያል።)

በአክሻክ ንጉሥ ፑዙር-ኒራሕ ዘመን፣ የመቅደሱ አሣ አጥማጆች ለጣኦቱ ለማርዶክ መሥዊያ አሣን እያጠመዱ ነበር። የንጉሡ መኳንንት ዐሣዎቹን ይቃሙ ነበር። <...> ሣምንቱም ካለፈ በኋላ ዐሣ አጥማጆቹ አሣን እያጠመዱ ነበር። <...> ባለ ቡናቤት ወደ ሆነችው ወደ ኩባባ (ኩግባው) መኖርያ አመጡት። <...> ለመቅደሱም ቅርብ ሆነው ወደዚያ አመጡት። ያንጊዜ [ጠፍቷል] እንደገና ለመቅደሱ <...> ኩባባ ለአሣ አጥማጆቹ ዳቦ ሰጠች፣ ውሃም ሰጠች፣ <...> ዐሣውንም ለመቅደሱ ቶሎ አቀረበ። ጣኦቱ ማርዶክ ደስ ብሎት 'ይሁን' አለ። ለባለ ቡናቤትዮዋ፣ ለኩባባ፣ የዓለሙን ሁሉ ገዥነት ሰጣት።

ከዚህ እንደሚታይ፣ ፑዙር-ኒራሕ የአሣ መሥዊያን ለመከልከል እንዳሰበ፣ የአጥማጆቹ ወገን ግን በኩግባው እርዳታ እንደ ተቋቋሙት፣ በኒፑርም የተገኙት የቄሳውንት ወገን ድጋፋቸውን ከፑዙር-ኒራሕ አዛውረው ሽረውት የተወደደችውን የኪሽ ባለ ቡናቤት ኩግባውን የመላ ሱመር ንግሥት ሆና እንዳሾሙአት መገመት እንችላለን።

በነገሥታት ዝርዝሩ «አክሻክ ተሸነፈና የሱመር ንጉሥነት ከአክሻክ ወደ ኪሽ ተዛወረ» ይላል። አንዳንድ ሌላ ቅጂ ግን ኩግባው ከአክሻክ ላዕላይነት በፊት፣ የኩግባውም ልጅ ፑዙር-ሲን ከአክሻክ ቀጥሎ ያደርጋሉ።

ቀዳሚው
ማሪ ንጉሥ ሻሩም-ኢተር
ሱመር (ኒፑር) አለቃ
2100-2097 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ኪሽ ንግሥት ኩግባው
ቀዳሚው
ኡሩር
አክሻክ ገዢ
2117-2097 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ኢሹ-ኢል
  1. Akshak at Historyfiles
  2. "ABC19". Archived from the original on 2006-02-28. በ2013-06-12 የተወሰደ.
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.