ጨኖ

ጨኖ ግራጫ ቢጤ የሆነ፣ ፈርጠም ያለ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪቃ፣ በተጨማሪም በኮንጎ ደኖች የሚገኝ ዝንጀሮ ነው። በኢትዮጵያ የሚገኘው ዓይነት ጨኖ የፀጉሩ ቀለም ግራጫና ጥቁር የሆነ፣ ፊቱ የጠቆረ ሰማያዊ የሆነ፣ አገጭና አንገቱ ነጭ ነው። የወንዶቹ ክብደት እስከ 12 ኪ.ግ. ሲሆን፤ አማካዩ 4.5 ኪ.ግ ይመዝናሉ።

?ጨኖ
ጨኖ በአሩሻ ብሔራዊ ፓርክ፣ ታንዛኒያ
ጨኖ በአሩሻ ብሔራዊ ፓርክታንዛኒያ
የአያያዝ ደረጃ

ብዙ የማያሳስብ (LC)[1]
ሳይንሳዊ ደረጃ መስጫ
ስፍን: ጉንደ እንስሳ (Animalia)
ክፍለስፍን: አምደስጌ (Chordata)
መደብ: አጥቢ (Mammalia)
ክፍለመደብ: ሰብአስተኔ (Primates)
አስተኔ: የምሥራቅ ክፍለአለም ዝንጀሮች (Cercopithecidae)
ወገን: የጨኖ ወገን (Cercopithecus)
ዝርያ: ጨኖ (C. mitis)
ክሌስም ስያሜ
Cercopithecus mitis
Wolf፣ 1822 እ.ኤ.አ.

ጨኖ የደን ዝንጀሮ ነው። የደን ዝንጀሮች ብዙ ጊዜ ከዝናባማ ሥፍራዎች ደኖች ውጪ አይገኙም። ጨኖ ግን ከነዚህ ደኖች ውጪም በሚገኙ ደኖች ውስጥ ይኖራል። በኢትዮጵያ፣ በጎደሬ ደን ውስጥ፣ ቴፒ አጠገብ ሜጢ አካባቢ ይገኛሉ። በተራራማ ሥፍራዎች ደኖችም እስከ 3000 ሜትር ከፍታ ድረስ ይገኛሉ። እጅጉን በዛፍ ላይ የሚገኝ ዝንጀሮ ነው። የሚገኘው በደን ዛፎች ግማሽ ላይ ነው።

ጨኖ ከማንኛቸውም የዝንጀሮ ዓይነቶች የበለጠ ቅጠል በል ቢሆንም ብዙ ዓይነት ምግቦች ይመገባል። ቅጠላ ቅጠል፣ ፍራፍሬ፣ ትላትልና ሦስት አፅቄዎች፣ አበቦች፣ ጥራጥሬዎች ወዘተ ይበላሉ። ዛፍ ላይ ታቁሮ የሚያገኙትን ውኃ ይጠጣሉ። የሚያስፈልጋቸውን ብዙ ውኃ የሚያገኙት ግን ውኃማ ከሆኑ ፍሬዎችና ቅጠሎች ነው። የተገኘውን ብዛት ያለው ምግብ በመመገብ፣ ጨኖዎች አነስተኛ በሆነ የመኖሪያ አካባቢዎች ሊኖሩ ይችላል።

ማህበራዊ አደረጃጀታቸው፣ ክልልተኛና ሴቶቹ ዘመዳሞች የሆኑበት፣ ባለአንድ ወገን ቡድኖች ናቸው። የደን ጦጣዎች ባህርይ እንዲህ ነው። የሴቶቹን የክልላቸው ባለቤት ወንዱ ነው። ሴቶቹንና ክልሉን በመጠበቅ ብዙ ትግል አለበት። ለዚህም ይሆናል የወንዱ ክብደት የሴቷን እጥፍ የሚሆነው። አንድ ወንድ ሁለት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ፣ እንዲህም ክልሉንም ሴቶቹንም እየተቆጣጠረ ይቆያል። ሥልጣኑን ከሌላ ቡድን በመጣ ወንድ ሲነጠቅ፣ በዚያም ቡድን አካባቢ እያንዣበበ ይቆያል። ይህን በመሰለ የሥልጣን ንጥቂያው አንዳንዴ ቶሎ ቶሎና ብዙ ሕፃኖች የሚሞቱበት ይሆናል። አንዳንዱ ጊዜ፣ የደረሱት ሴቶች ቁጥር በቡድኑ ውስጥ ብዙ ሲሆን፣ ብቸኛ ወንዶች ቡድኑን ተደብቀው ይቀላቀላሉ። ይህ ሁኔታ የቡድኑ አለቃ የሆነው ወንድ ሳይገነዘበው፣ በሴቶቹ ፍላጎት የተደበቁት ወንዶች ግንኙነት ያድጋሉ። በእንዲህ ያለ ጊዜ ከአለቅየው ይልቅ፣ የሰረቁት ወንዶች ልጆች ብዛት ሊኖራቸው ይችላል። አለቅየው ወንድ ሌሎች ወንዶችን በቡድኑ መሃል ባገኛቸው ቁጥር ያባርራቸዋል። ሆኖም፣ ቡድኑ ሴቶች ስርቆሽ ለመቆጣጣር አይችልም። ምክንያቱም በደን ወስጥ በሰፊው ተበትነው ስለሚመገቡ ነው። አንዳንዴ ሴቶቹ ራሳቸው እንግዳ ወንዶች ያባርራሉ። ሆኖም ሴቶቹ ብዙውን ጊዜ ከእንግዶቹ ወንዶች ግንኙነት ሲያደርጉ፣ በምርጫቸው ነው። ብዙ ጊዜ፣ ሥልጣን ነጣቂዎቹ ተደብቀው የቡድን አለቃውን የሚታዘቡ ወንዶች ናቸው። በየጊዜው አቅሙን ይፈትናሉ። በቡድኑ ክልል ገብተው የአለቅነት ድምፅ ያስማሉ። ሴቶቹን ያጠጋሉ። እንዲህ ሲሆን ወኔውን ያላሰየ ወንድ ለግልበጣ ምቹ ነው። ከተገለበጠም ሌሎች አድፍጠው ያሉ ስለሚኖሩ ፣ የመገለባበጥ ሰሞን ይሆናል።

ጨኖዎች በድምፅና በአካላዊ ንቅናቄ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ። በተለያዩ ዓይነት ተግባሮች መገለጫ የሚሆኑ ሰባት ዓይነት ድምፆች አሏቸው። በቡድናቸው ውስጥ የሚታየው አብዛኛው ፀብ፣ በዋናው ወንድና ለአካለ መጠን ባልደረሱና ጎረምሳ ወንዶች መሃል የሚታየው ነው። በሴቶቹና ሕፃናትን በሚገድሉ ወንዶች መኻከል ከባድ ግጭት ያድጋል። በቡድኖች መኻከል የሚደረግ ግጭት የሚሆነው አልፎ አልፎ ነው። እንዲህ ያለ ግጭት የሚነሳው በድንበር አካባቢ በምግብ ሽኩቻ የተነሳ ነው።

የእርግዝና ጊዜአቸውን 140 ቀን ነው። የልጆቻቸውን እድገትም ቀስ ያለ ነው። ከወለዱ ወዲያ ለሚቀጥለው እርግዝና 15 ወራት መቆየት አለባቸው። ሆኖም የወለደችው የሞተባት፣ በ45ኛው ቀን ግንኙነት ታደርጋለች። ስለዚህም ይመስላል አዲስ ወንድ የቡድን አለቅነቱን ሲያሸነፍ ሕፃናቱን የሚገድለው። እንዲህ በማድረግ የሴቶቹን የግንኙነት ጊዜ በብዙ ወራት ያሳጥረዋል።

ምንጭ

  • ዶ/ር ሰሎሞን ይርጋ «አጥቢዎች» (2000)
  1. (እንግሊዝኛ) Kingdon, J., Gippoliti, S., Butynski, T. M., Lawes, M. J., Eeley, H., Lehn, C. & De Jong, Y. (2008). Cercopithecus mitis. In: IUCN 2008. IUCN Red List of Threatened Species. Downloaded on 4 January 2009.
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.