ጥቅምት ፭
ጥቅምት ፭ ቀን በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የዓመቱ ፴፭ኛው ዕለት እና የመፀው ፲ኛው ቀን ነው። ከዚህ ዕለት በኋላ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ፣ በዘመነ ሉቃስ ፫፻፴፩ ዕለታት ሲቀሩ፤ በዘመነ ዮሐንስ ፣ ዘመነ ማቴዎስ እና ዘመነ ማርቆስ ደግሞ ፫፻፴ ዕለታት ይቀራሉ።
ታሪካዊ ማስታወሻዎች
- ፲፭፻፸፭ ዓ.ም. - የግሪጎሪያዊ ዘመን አቆጣጠር በዛሬው ዕለት በኢጣልያ፤ በፖላንድ ፤ በፖርቱጋል እና በእስፓንያ ከመስከረም ፳፭ ቀን በቀጥታ ወደ ጥቅምት ፭ ቀን በመዝለል ተጀመረ።
- ፲፯፻፩ ዓ/ም - ከ፪ዓመት በፊት በዚህ ዕለት ዳግማዊ ዓፄ ኢያሱን (ስመ መንግሥት አድያም ሰገድ) የገደሉትን ጳውሎስ እና ደርመንን ንጉሥ ዓፄ ቴዎፍሎስ የስቅላት ሞት ፍርድ ፈረዱባቸው።
- ፲፰፻፰ ዓ.ም. - የፈረንሳይ ንጉሥ፣ ቀዳማዊ ናፖሌዮን በወተርሉ ጦር ሜዳ ላይ ከተሸነፈ በኋላ በአሸናፊዎቹ በብሪታንያ ቁጥጥር ሥር አትላንቲክ ውቅያኖስ ወደምትገኘው የሴይንት ሄሌና ደሴት ተሰደደ።
- ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. - በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በፈረንሳይ አገር የናዚ ጀርመን ደጋፊ የነበረው የቪሺ አስተዳደር ጠቅላይ ሚንስቴር የነበሩት ፒዬር ላቫል በሞት ተቀጡ። ላቫል ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከነበሩት ዊሊያም ሆር ጋር በታኅሣሥ ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ኢትዮጵያን ለፋሽሽት ኢጣልያ በሚያመች መልክ ለመከፋፈል የምስጢራዊ ስምምነት የፈጸሙ ናቸው።
- ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. - የቀድሞዋ የሶቪዬት ሕብረት መሪ የነበሩት ኒኪታ ክሩስቼቭ ከሥልጣን ተሽረው፣ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት በአሌክሲ ኮሲጊን፤ በኮሙኒስት ፓርቲ ሊቀመንበርነት ደግሞ በሌዮኒድ ብሬዥኔቭ ተተኩ።
- ፲፱፻፷፯ ዓ/ም - የቀድሞው ንጉሠ ነገሥት የልጅ ልጅ መቶ-ዓለቃ ልዑል መኮንን መኮንን ትምህርት ላይ ከነበሩበት ከአሜሪካ ወደአገራቸው በአስቸኳይ እንዲመለሱ ደርግ ትዕዛዝ አስተላለፈ።
- ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. - የቀድሞዋ የሶቪዬት ሕብረት መሪ የነበሩት ሚካይል ጎርባቾቭ የኖቤል ሰላማዊ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ይፋ ተደረገ።
- ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. - የቻይና ሕዝባዊ ሬፑብሊክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው የያዘች የሰማይ መንኮራኩር ተኮሰች።
ልደት
- ፲፰፻፴፯ ዓ.ም. - ታዋቂውና ተቀዳሚው የጀርመን ፈላስፋ ፍሬድሪክ ቪልሄልም ኒቺ ተወለደ።
- ፲፱፻፫ ዓ.ም. - ታዋቂው ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ በደብረ ማርቆስ አውራጃ በጎዛመን ወረዳ በእንዳዶም ኪዳነ ምኅረት ቀበሌ ተወለዱ።
ዕለተ ሞት
- ፲፮፻፺፱ ዓ/ም - በዓፄ ተክለ ሃይማኖት (ስመ መንግሥት ልዑል ሰገድ) ትዕዛዝ፣ ሸሽተው ጣና ሐይቅ ላይ በጨቅላ መንዞ ደሴት የነበሩትን አባታቸውን ዳግማዊ ኢያሱ አድያም ሰገድን ጳውሎስ እና ደርመን የተባሉ ነፍሰ ገዳዮች ሕይወታቸውን ካጠፉ በኋላ አስከሬናቸውን በእሳት አቃጠሉት። ከቃጠሎ የተረፈውን ካኡናቱ በታንኳ ወስደው ምጽራሓ ደሥተ ላይ ቀበሩት።
- ፲፱፻፴፱ ዓ.ም. - በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወንጀለኛነቱ የሞት ቅጣት የተፈረደበት ኸርማን ጎሪንግ ለቅጣቱ መፈጸሚያ ጥቂት ሰዐታት ሲቀሩ ሳያናይድ መርዝ በመውሰድ ራሱን ገደለ
ዋቢ ምንጮች
- መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፤ ዕለታዊ የታሪክ ድርጊት - የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ፓትረያርክ (፲፱፻፶፩ ዓ/ም)
- {{en]] P.R.O., FCO 371/1829 - ANNUAL REVIEW FOR ETHIOPIA FOR 1974
- {{en]] "All Nobel Peace Prizes". Nobelprize.org. 14 Oct 2011
http://www.nobelprize.org/nobel_prizes/peace/laureates/
የኢትዮጵያ ወራት | |
---|---|
መስከረም - ጥቅምት - ኅዳር - ታኅሣሥ - ጥር - የካቲት - መጋቢት - ሚያዝያ - ግንቦት - ሰኔ - ሐምሌ - ነሐሴ - ጳጉሜ |
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.