ጥርኝ

ጥርኝ (ሮማይስጥCivettictis civetta) ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ አጥቢ እንስሳ ነው። ጥርኞች ከአፍሪቃሸለምጥማጥና ጥርኝ አስተኔ ዘመድ ውስጥ በመጠን ትልቆቹ ናቸው።

?ጥርኝ

የአያያዝ ደረጃ

ብዙ የማያሳስብ (LC)
ሳይንሳዊ ደረጃ መስጫ
ስፍን: ጉንደ እንስሳ (Animalia)
ክፍለስፍን: አምደስጌ (Chordata)
መደብ: አጥቢ (Mammalia)
ክፍለመደብ: ስጋበል (Carnivora)
አስተኔ: የጥርኝ አስተኔ Viverridae
ወገን: ጥርኝ Civettictis
ዝርያ: C. civetta
ክሌስም ስያሜ
''Civettictis civetta''
(ዮሐን ክሪስቲያን ዳንኤል ቮን ሽሬበር፣ 1776 እ.ኤ.አ.)

የእንስሳው የተፈጥሮ ሁኔታና ባሕርይ

ክብደታቸው ከ፯ እስከ ፳ ኪሎግራም፣ ከፍታቸው ከ፴፭ እስከ ፵ ሴንቲሜትር፣ ከጅራታቸው በስተቀር ርዝመታቸው ከ፷፰ እስከ ፹፱ ሴንቲሜትር የሆነ ሥጋ በሎች ናቸው። ጅራታቸው የጠቅላላ አካላቸውን ርዝመት ሢሦ ይሆናል። በመጠን ወንዶቹ ጥርኞች ከሴቶቹ ይበልጣሉ። ፈርጠም ያሉ ቅልጠሞቻቸው ከሌሎቹ የዘመዱ አባሎች ይልቅ ረዘም ያሉ፣ ታፋቸው ከፍ ብሎ የኋላ እግሮቻቸው ከፊተኞቹ የበለጠ ጠንካራ የሆኑ፣ በያንዳንዱ እግር አምስት ጣቶች ያሏቸው፣ እያንዳንዱ ጣት ዱልዱም ኮኮኔ ያለው እንስሳ ነው። ጥርኞች ጥርሶቻቸው ትላልቅ ሆነው እንደ ውሻ ሁሉ ሰፋፊ የመንጋጋ ጥርሶች አሏቸው። ጆሮዎቻቸው ሰፋፊ ናቸው።የቆዳቸው ፀጉር ግራጫ ሆኖ ጥቋቁር መስመሮችና ረጃጅም ነጠብጣቦች አሉት። አንገታቸው ላይ ሁለት ጥቋቁር መስመሮች አሏቸው። ልጆቻቸው ጥቁር ቡናማ ቀለም ሲኖሯቸው ምልክቶቹ ግን አይለዩም። ትልቅ የእዥ ዕጢና የቂጥ ከረጢት ዕጢ አላቸው።

ጥርኞች ለስሪያ ከአካባቢያቸው ርቀው ሊሄዱ ይችላሉ። ከወትሮው በተለየ ይንቀዠቀዣሉ። ወንዱ የሴቷን ዝባድና ሽንት እያሸተተና ሽቅብ እያነፈነፈ የመቀበል ጊዜዋ መድረሱን ያረጋግጣል። በመጀመሪያ ሴቷ በቁጣ ስታባርረው ወንዱ በተሸናፊነት ይመለሳል። ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ የሆነችው ሴት በወንዱ አጠገብ በመሮጥ እንዲከተላት ትቆሰቁሰዋለች። በስሪያ ጊዜ ከታፋዋ ከፍ አድርጋ በፊት እግሮቿ ላይ ትተኛለች። ሴቱቱ ጮሃ ወደፊት ለመንቀሳቀስ ከፈለገች ወንድየው የአንገቷን ጸጉር በጥርሱ ጨምድዶ ይገታታል። አንድ ደቂቃ ያህል ከሚፈጀው ስሪያ በኋላ ሁለቱም ብልቶቻቸውን ይልሳሉ።

ጥርኞች ከአንድ እስከ አራት ቡችሎችን በጉድጓድ ውስጥ ይወልዳሉ። የቡችሎቹ ዓይኖች ሲወለዱ ወይም በጥቂት ቀኖች ውስጥ ይከፈታሉ። በአምሥት ቀኖች ውስጥ መራመድ ይችላሉ። ሆኖም ከጉድጓዳቸው የሚወጡት በሥስተኛው ሳምንት ነው። በሁለት ሳምንት ውስጥ እርስ በርስ መጫወት ይጀምራሉ። እያንዳንዱ ቡችላ አንድ ጡት ይጠባል። እናቶች ከአንድ ወር ጀምረው ጡት ማስጣል ይጀምሯቸዋል። ሆኖም ጨርሰው መጥባት የሚተዉት ከ፲፬ እስከ ፳ ሳምንት ሲሞላቸው ነው። በአምስተኛው ወር ዝባድ ማውጣት ይጀምራሉ። በዚህ ወቅት ወንዶቹ ቡችላዎች ምልክት ማድረግና ሽንት ማሽተት ይጀምራሉ። የቆለጣቸውም መጠን ትልቅ እየሆነ ይሄዳል።

በሰው ቁጥጥር ስር ሆነው በዓመት ሦስት ጊዜ የሚወልዱ መሆናቸው ቢታወቅም በተፈጥሮ ሁኔታ የሚወልዱት ክረምት ሲጀምር ነው። አንድ ዓመት የሞላት ጥርኝ ማርገዝ ትችላለች። ከወለደች ከሦስት ወር ተኩል በኋላም እንደገና ማርገዝ ትችላለች። የእርግዝናቸው ጊዜ ወደ ፹ ቀኖች ግድም ነው።

ማኅበራዊ አደረጃጀታቸው ብቸኛ፣ ሌቴ፣ እና ምናልባትም ክልልተኛ ነው። ቀን ቀን በጉድጓዶችና ጥቅጥቅ ባለ ጥሻ ይጠለላሉ። ቀን በግልፅ የሚታዩት አልፎ አልፎ ብቻ ነው። ጥርኞች በአንድ ሥፍራ ተወስነው የሚኖሩ፤ ምግባራቸው የማይለዋወጥ አልፎ አልፎ ምልክት ባደረጉበት መንገድ የሚጓዙ እንስሶች ናቸው። ምንም እንኳ የሽታ ምልክት ማድረጋቸውና ዓይነ ምድራቸውን በተወሰኑ የድንበር ሥፍራዎች መጣላቸው የታወቀ ቢሆንም ክልልተኛው ወንዱ ብቻ ይሁን ወይስ ሴቷም ጭምር የታወቀ ነገር የለም። የተያዙ ጥርኞች በስሪያ ጊዜ መጣላታቸው እንዲሁም የቡችሎቻቸው የጨዋታ ትግል ወደ ምር ፀብ መለወጡ ማኅበራዊ አለመሆናቸውን ያመለክታሉ። ወንድና ሴት አብረው የሚገኙት ለስሪያ ብቻ ነው።

ጥርኞች ማታ ለአደን ሲወጡ ጸጥ ብለው ራሳቸውን ወደ መሬት ደፍተው እጅግ ጥሩ የሆነውን የማሽተትና የመስማት ኃይላቸውን በመጠቀም ጥሻ ውስጥ ያሉትን ታዳኞች ለማግኘት ይጥራሉ። ጥርኞች የሚያድኑት እንደ ሸለምጥማጥ አድፍጠውና አሳደው ሳይሆን በያሉበት ቀጨም እያደረጉ ነው። ጥርኞች የሚያድኑትን ሁሉ የሚይዙት አገጫቸውን ተጠቅመው ቢሆንም የአጠቃቅ ዘዴያቸው እንደታዳኙ መጠንና የመከላከል ችሎታ ይለያያል። አይጥእባብን የመሰሉት ሲገድሉ፣ ነክሰው በኃይል በመነቅነቅ የጀርባ አጥንቶቻቸውን በመሰባበር ነው። ተለቅ ያለ እንስሳ ሲሆን የራስ ቅሉን በጽኑ በመንከስ ነው። ጥርኞች ሲበሉ እየተጣደፉ ነው፤ ሲውጡም በደንብ ሳያኝኩ ነው። ጥርኞች ለምግብ ፍለጋ ቀስ ብለው ቢራመዱም ሲያስፈልግ በፍጥነት መሮጥ ይችላሉ። እስከ ግማሽ ሜትር ያህል ከፍታ እየሮጡ መዝዘል ይችላሉ። ብዙ ጊዜ ግን ከመሮጥ ይልቅ ወደሚሸሸጉበት ጥሻ እጥፍ ማለትን ያዘወትራሉ።

የመኖሪያው መልክዓ ምድር

እጅግ በረሃማ ከሆኑ ሥፍራዎች በስተቀር በቂ ሽፋን ባለበት ቦታ በመላው አፍሪቃ ይገኛሉ። ብዙ ጊዜ ውኃ ካለበት ሥፍራ አይርቁም። በአካሉ መዋቅር የተነሳ ምድቡ ከሥጋ በሎች ቢሆንም ጥርኝ ሥጋም ሆነ ዕፅ ያገኘውን የሚበላ እንስሳ ነው። የተለያዩ ዕፅዋትን፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ሦስት አፅቄዎችና ሌሎች የጀርባ አጥንት የሌላቸው እንስሳትን ይበላሉ። የጀርባ አጥንት ካላቸውም ውስጥ አዲስ የተወለዱ አነስተኛ የቀንድ እንስሳት ጭምር አድነው ይበላሉ። ጥንብም ይበላሉ።

የእንስሳው ጥቅም

በቂጥ ከረጢት እዣቸው ምልክት የሚያደርጉት በመንገዳቸው ዳር ያሉ ዛፎች ግንዶች ላይ ነው። በተለይም ፍሬውን የሚበሉት ዛፍ ላይ በየ ፹፭ ሜትሩ ገደማ በዚህ እዥ ምልክት ያደርጋሉ። ይህ እዥ ዝባድ ይባላል። ወፈር ያለ፣ ቢጫ ቅባት ዓይነት ነው። እየቆየ ሲሄድ ግን ይጠጥርና ጥቁር ቡኔ ይሆናል። ሽታው ደግሞ እስከ አራት ወር ይቆያል። ተይዘው የሚገኙ ጥርኞች አልፎ አልፎ በየጊዜው ዝባድ ይጨለፍባቸዋል። ዝባድ ሴቬቶን ወደሚባል ውሕድ ይጣራና ውድ የሆኑ ሽቶዎች የሚሠሩ ፋብሪካዎች ይጠቀሙበታል። ወንዶቹም ሴቶቹም በጣም የሚሸተውን ዓይነ ምድራቸውን በአንድ ሥፍራ ይጥላሉ። በሽንታቸው ምልክት የሚያደርጉት ግን ወንዶቹ ብቻ ናቸው።

ዋቢ ምንጭ-

  • ሪፖርተር (20 JANUARY 2013) ፤«ጥርኝ (African Civet) Civettictis civetta»፤ ሰሎሞን ይርጋ (ዶር.) ‹‹አጥቢዎች›› (2000)
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.