ጌባል

ጌባል (አረብኛ፦ جبيل /ጁባይል/፤ ግሪክ፦ Βύβλος /ቢውብሎስ/) በሊባኖስ የሚገኝ ጥንታዊ ከተማ ነው።

የጥንቱ ፊንቄ ታሪክ ጸሐፊ ሳንኩኒያቶን እንዳለ፣ ጌባል ከሁሉ ጥንታዊ ከተማ ሲሆን በንጉሡ ክሮኖስ (ወይም 'ኤሎስ') በፊንቄ (ከነዓን) አገር ተመሠርቶ ነበር። ለረጅም ጊዜ ከተማው የምስር ፈርዖን ጓደኛ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመዝሙረ ዳዊት 83፡7 እና ትንቢተ ሕዝቅኤል 27፡9 ይጠቀሳል። በኋላ (747 ዓክልበ.) ጌባል ለአሦር ንጉሥ 3 ቴልጌልቴልፌልሶር ተገዥ ሆነ። እንዲሁም በየተራው ወደ ፋርስመቄዶን እና ሮማ መንግሥታት ተዛወረ፤ ከዚያም ለአረቦች ወደቀ። በመጀመርያው መስቀል ጦርነት (1092 ዓ.ም) ስሙ 'ጊብለት' ተብሎ ለጊዜ የፈረንጆች ማዕከል ሆነ። ከ1508 እስከ 1911 ዓ.ም. በኦቶማን (ቱርክ) መንግሥት ነበር። ከተማው እስከ ዛሬ ድረስ በሊባኖስ ይገኛል።

በጥንት ጌባል ፓፒሩስ (ቄጠማ ወይም የወረቀት ተክል) ወደ ግሪኮች የነገደው ዋናው ወደብ ስለ ሆነ፣ ግሪኮችም የከተማውን ስም Βύβλος /ቢውብሎስ/ ስላሉት፤ ይህ ስም በግሪክ ቋንቋ ደግሞ 'ፓፒሩስ' ወይም 'መጽሐፍ' ማለት ሆነ። ይህም ቃል በእንግሊዝኛ (በታላቅ የአናባቢ መፈራረቅ ምክንያት) የ«Bible» (/ባይብል/፣ መጽሐፍ ቅዱስ) ምንጭ ሆነ።

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.