ደሴ

ደሴ ወሎ ክፍለ ሃገር የሚገኝ ከተማ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የደቡብ ወሎ ዋና ከተማ ነው። የወይና ደጋ አየር ጸባይ ያለው ይህ ከተማ፣ በከተማነት ታዋቂ እየሆነ የመጣው በዓፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዘመን እንደሆነ ይጠቀሳል። የአካባቢው መሬት ከእሳተ ጎሞራ ቅሪት የሚመነጭ ስለሆነ፣ በንጥረ ነገር የዳበርና ለምነት ስለሚያሳይ፣ ከተማው በ20ኛው ክፍለዘመን በፍጠነት እንዲያድግና በኋላም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና ደርግ ዘመን ወሎ ተብሎ ለተሰየመው ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ እንዲሆን ዋና አስተዋጽዖ አድርጓል[1]

ደሴ
ፒያሳ ከሰሜን ወደ ደቡብ ያለው እይታ
አገር  ኢትዮጵያ
ክልል አማራ ክልል
ዞን ደቡብ ወሎ
ከፍታ 2470 ሜትር
የሕዝብ ብዛት
    አጠቃላይ 170,000 (ግምታዊ)
ደሴ is located in ኢትዮጵያ
{{{alt}}}
ደሴ

11°8′ ሰሜን ኬክሮስ እና 39°38′ ምሥራቅ ኬንትሮስ

ታሪክ

እንደ አርመን ኢምባሲ ታሪካዊ ሰነድ፣ የአርመን ክርስቲያኖች በ7ኛው ክፍለ ዘመን በአረቦች በተነሳባቸው ወከባ ምክንያት ብዙዎች ተሰደው በአሁኑ ደሴ ከተማ አካባቢ እንደሰፈሩና በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተሰኘውን ገዳም በሐይቅ እንደመሰረቱ ያትታል። በዚህ አካባቢ አርመኖች የመስፋፋትና የመጎልበት ሁኔታ እያሳዩ ስለመጡ አካባቢው የአርመን ደሴት እስከመባል እንደደረሰና በኋላ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አህመድ ወረራ ምክንያት ካሉበት ተነቅለው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደተበተኑ ይሄው የኢምባሲ ሰነድ ያትታል[2]

እ.ኤ.አ. በ 1882ዓ.ም. ነበር ን/ነገስት ዮሃንስ ጦራቸውን በዚሁ አካባቢ ሲያሰፍሩ ከአመት በፊት በአካባቢው የታየችውን ባለጭራ ኮከብ በማስታወስ " ይህን ቦታ ደሴ ብየዋለሁ" ብለው ከተማውን እንደቆረቆሩ ይጠቀሳል[3]። የደሴ ከተማ የፖስታ አገልግሎት ያገኘችው እ.ኤ.አ. 1920 ነው። የስልክ አገልግሎትም ቢሆን በቅርቡ ማለትም እ.ኤ.አ. በ 1954 ነው ያገኘችው። ፤የደሴ ከተማ የ መብራት አገልግሎት ያገኘችው እ.ኤ.አ. በ 1963 ነው። ይህን የመብራት አገልግሎት ያገኘችው በጊዜው በመገንባት ላይ በነበረው በናፍጣ የሚሰራ የኤሌክትሪክ ሃይል ነው።

አጠቃላይ መረጃ

አዲስ አበባ ተነስተን 401 ኪሎ ሜትር ወደ ሰሜን ስንጓዝ ከኮምቦልቻ ቀጥሎ የምናገኘዉ ከተማ የደሴ ከተማ ነው። ደሴ ጥንታዊ ስሙ ላኮመልዛ የሆነ የሰሜን-መሃል ኢትዮጵያ ከተማና ወረዳ ነው። ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ መስመር (መንገድ) ላይ በአማራ ክልልደቡብ ወሎ ዞን ሲገኝ በላቲቱድና ሎንግቱድ 11°8′ ሰሜን ኬክሮስ እና 39°38′ ምሥራቅ ኬንትሮስ ላይ ነዉ። የብሔራዊ ስታትስቲክ ባለስልጣን በ1998 እንደመዘገበው፤ ከኢትዮጵያ ሰፊ ከትሞች አንዱ ሲሆን የ169,104 ሕዝብ መኖሪያ ከተማ ነው። ከነሱም መኻከል 86,167 ወንዶች 82,937 ሴቶች ናቸው ተብሎ ተገምቷል።

ደሴ አሁን ስራ ቢያቆምም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያን ከጎረቤቱ ከኮምቦልቻ ከተማ ጋር ይጋራ ነበር።

አዲስ አመት አካባቢ የጥቅምት ወር ሲገባ በጣም ታዋቂ እና ብዙ የተዘፈነለት የጦሳ ተራራ በቢጫ (አደይ) አበባ ተሸፍኖ ማየት ምን ያህል ለበአል ድምቀት የመንፈስ እርካታ እንደሚሰጥ መግለጽ ያዳግታል።

ደሴ ለመስፋፋት ሰፊ እድል ያለዉ አይመስልም ምክንያቱም ዙሪያዉ በወግዲ የተከበበ በመሆኑ እና መሬቱ ዉሃ የሚበዛበት (ረግራጋማ ) ስለሆነ ነው። ከዚህም አንጻር በጣም ብዙ ህዝብ እንደሚኖርበት ይታወቃል።

ኪነ-ጥበብ

የውቦች ከተማ እንደሆነች የሚነገርላት ደሴ ከተማ በ ኪነ-ጥበቡ ረገድ በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካላቸው ከተሞች አንዷ ናት። በከተማይቱ መሃል ዕምብርት የሚገኙት ወሎ ባህል አምባ እና ምን ትዋብ አዳራሾች ለከተማዋ የኪነ ጥበብ እድገት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። ደሴ የበፊቱ ሙዚየም የተቀየረው የደጃዝማች ዮሴፍ ብሩ መኖሪያ ቤት መቀመጫ ናት።

ሙዚቃ

የ አራቱም የሙዚቃ ቅኝቶች መፍለቂያ የሆነችው ደሴ ከተማ በ ሙዚቃው ዘርፍ በሃገሪቱ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው ከተሞች አንዷ ናት። ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው ከከተማይቱ የሚዎጡ በርካታ ድምጻዊያንን መጥቀስ ይቻላል። በተጨማረም ከተማይቱን አስመልክቶ የተዘፈኑ ከ መቶ ሃያ በላይ የአማርኛ ዘፎኖች እንዳሉ ይነገራል። አብዛሃኛዎቹ ዘፈኖች በከተማዋ ስለሚገኙ ቆነጃጂቶች የተዜሙ ናቸው።ባህሩ ቃኘው፤ ማሪቱ ለገሰ፤ ዚነት ሙሃባ፤ መስፍን አበበን የመሳሰሉ ዘፋኞች የተገኙት ከደሴ ነው። ለኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉትና በሀገር ውስጥ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ እና በሁንጋርያ ቡዳፔሽት ሥልጠናቸውን በጥበቡ ቀስመው የምጀመርያ ዲግሪያቸውን አግኝተው በሃገራቸው ትያትር ቤቶች በመሥራት የሕዝብ ፍቅርንና ሙያዊ ልዕልና ከተጎናፀፍትና፣ በዓለም አቀፍ የፊልም ሥራ በመካፈል ቀደምት ሥፍራን የያዙት የጥበብ ሰው ደበበ እሸቱም የዚሁ የወሎ (ደሴ) ተወላጅ ናቸው።

መዝናኛ

በከተማይቱ ውስጥ በ 1996 የተገነባ ግዙፍ የወጣቶች ማእከል ይገኛል። ይህ ማእከል ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነ ግን ይታመናል። የቤተሰብ መምሪያ እና የሰርከስ ደሴን ጨምሮ በርካታ መካከለኛ እና አነስተኛ የሙዚቃ ባንዶች ይገኛሉ። ከተገነባ በርካታ አመታትን ያሳለፈውና ተገቢውን እድሳት ያላገኘው የ ደሴ እታዲየም በከተማይቱ እምብርት ይገኛል። ይህ እታዲየም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የ ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ የ እግር ኳስ ክለብ የመጫወቻ መዳ ሁኖ አገልግሏል። በዚህም በርካታ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን የማስተናገድ እድል አግኝቷል።

መሰረተ ልማት

ይህች ከተማ በመሰረተ ልማቱ ረገድ ተረስታ የቆየች ከተማ ናት ማለት ይቻላል። ለዚህም እንደ መንገድ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ማንሳት ይቻላል።

ትምህርት

በቅርቡ ማለትም በ እ.ኤ.አ. 2006 ስራ የጀመረው ወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም መምህር አካለ ወልድ፣ ወይዘሮ ስህን እና ሆጤ በመባል የሚጠሩት ሶስት ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች በዚሁ ከተማ ይገኛሉ። ብዙ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችም ይገኛሉ። ከ ቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተማይቱ የበርካታ የግል ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች መዳረሻ ሆናለች።

ጤና

በደሴ ከተማ ውስጥ ሁለት የመንግስት ሆስፒታሎች ማለትም የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል እና ቦሩ ሆስፒታል ይግኛሉ። በግሉ የ ጤና ዘርፍም ሶስት ሆስፒታሎች ማለትም ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ባቲ ጠቅላላ ሆስፒታል እና ኢትዮ ጠቅላላ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በርካታ የግል ክሊኒኮች አሉ።

ደሴ ፒያሳ ከደቡብ ወደ ሰሜን ያለው እይታ

መንገድ

ደሴ ከተማ ትልቅ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ይህ ዘርፍ ነው። ከተማይቱ ምንም እንኳን በቅርቡ የከተማው ዋና መንገድ እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ በመገንባት ላይ ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደረጃውን ያልጠበቀና የተጎዳ ባለ አንድ መስመር አስፋልት መንገድ ብቻን ነበር የነበራት። አሁን የተጀመረውና እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2002 አመተ ምህረት ይጠናቀቃል የተባለው መንገድ የከተማይቱን ዋና መንገድ ጨምሮ በተለያዩ የውስጥ ለውስጥ ክፍሎች የተዘረጋ ነው። መንገዱ የሚገነባው በ ሁለት አካላት ነው። አንደኛው የከተማይቱ መዘጋጃ ቤት ነው። ይህ ክፍል የሚያስገነባው ዋናውን የመሃል መስመር ሲሆን ይዘቱ ባለ ሁለት (መንታ) መንገድ ነው። ሁለተኛው አካል የሃገሪቱ የመንገድ ትራንስፖርት የሚያስገነባው ሲሆን የከተማይቱን የ ዳር ክፍሎችና ከ አዋሳኝ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ናቸው።

የአየር ሁኔታ

'ደሴ ከተማ በአመዛኙ ቀዝቃዛማ የአየር ጸባይ ያላት ደጋማ ከተማ ናት። በተለይ በክረምት ወራት የሚጥለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እና ውርጭ የተለመደ ነው። በከፍተኛ ቦታ ላይ መገኘቷ ለዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በተራራ የተከበበችው ደሴ ለበርካታ እንደ ገብስአጃባቄላ እና ሌሎች የ አዝእርት አይነቶች መብቀያ ናት። በዚህም የደሴ ዙሪያ አከባቢ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ናቸው።

ማጣቀሻ

  1. Encyclopaedia Aethiopica: D-Ha, edited by Siegbert Uhlig, 2005
  2. http://egypt.mfa.am/en/community-overview-et/
  3. "Archive copy". Archived from the original on 2016-03-04. በ2012-05-29 የተወሰደ.


This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.