ደመነፍስ
ደመነፍስ ወይም ውርስሜት ለማናቸውም ሕያው ፍጡር ከተፈጥሮ ከልደት እንጂ ከትምህርት ወይም ልምምድ የማይመጣው የሥራ አስተዋይነት ነው።
ለምሳሌ፦
የካንጋሮ (ወይም የማናቸውም ኪሴ እንስሳ) ግልገል ሲወለድ፣ እንደ ጥቃቅን ቀይ ስለግ ወይም ሺል ይመስላል እንጂ ካንጋሮን ምንም አይመስልም። ሆኖም፣ ካንጋሮ በጣም ሃይለኛ ደመነፍስ ስላለው፣ እንደ ተወለደ ወዲያው ያለ ምንም ልምምድ ከማሕፀን ወደ እናቱ ኪስ የጡት ጫፍ ወዳለበት ይጓዛል። የካንጋሮ እናት ጡት ደግሞ እንደ ልጆቹ እድሜ ልዩ ልዩ አይነት ወተት ያዘጋጃል፣ ታናሹም እስከሚታድግ ድረስ አዲስ ሺል በማሕፀን ከተፈጥሮ ይቆያል። በዚህ ካንጋሮች መርሃግብር ውስጥ የግልገሉ ደመነፍስ ምንጊዜም ወሳኝ ነው። ይህ ጥበብ ከየት እንደ መጣ ሳይንስ በግልጽ ባይነግረንም እንኳን ስያሜዎቹ «ደመ ነፍስ» ወይም «ውርስሜት» አንዳመለከቱ ከወላጅ የተወረሰ መንፈስ ወይም ስሜት እንደ ሆነ ይገመታል።
በተመሳሳይ ምሳሌ፣ የባሕር ኤሊ ግልገል በወደብ ላይ ከእንቁላል ወጥቶ ምንም ነገር ሳያውቅ በቀጥታ ወደ ባሕር ይጓዛል።
ክሥተቱ በሕፃንነት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ የሚታይ ደመነፍስ አለ። ለምሳሌ ንቦች ምንም ትምህርት ወይም ልምምድ ሳይማሩ የመብልን አቅጣጫ ና ርቀት የሚያጠቆመውን ጭፈራ ዝም ብለው ያውቃሉ። የካንጋሮ ወይንም የአጋዘን ወንድ ታድጎ ከሌላው ወንድ ጋር ቡጢ ሲያደርግ ደግሞ እንዲህ ነው።
የሰው ልጅ ነፃ ፈቃድ መጠን ከእንስሳ ይልቅ እጅግ ስለሚበልጥ፣ የደመነፍሳችን መጠን እንዲህ ከነርሱ ያንሳል፣ ደመነፍሳችንንም በነጻ ፈቃዳችን ማገልበጥ እንችላለን።
ለደመ ነፍስ (እንግሊዝኛ፦ instinct /እንስቲንክት/) የተዛመደ ሃሣብ ደመነፍሳዊ ስጦታ (intuition /ኢንቱዊሽን/) ይባላል። ልዩነቱም «ደመነፍሳዊ ስጦታ» ወይም ኢንቱዊሽን ከተፈጥሮ የምናገኘውን አስተዋይነት፣ ጥበብ፣ ዕውቀት ወይም መረጃ ያጠቁማል። «ደመነፍስ» ወይም ኢንስቲንክት ግን የምናውቀውን ሥራ እራሱን ያጠቁማል።