ያፌት
ያፌት (ዕብራይስጥ፦ יֶפֶת /ዬፌት/) በብሉይ ኪዳንና በአይሁድ፣ ክርስቲያንና እስላም ሥነ ጽሑፍ ዘንድ በኖኅ መርከብ ላይ ከማየ አይኅ ካመለጡት ከኖኅ ሦስት ወንድ ልጆች መሃል አንዱ ነው። ወንድሞቹ ካምና ሴም ነበሩ፤ ልጆቹም ጋሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ቶቤል፣ ሞሳሕና ቲራስ ናቸው።
በመጽሐፈ ኩፋሌ ዘንድ ያፌት በ1212 ዓ.ዓ. ተወለደ፤ በዚህ አቆጣጠር በ1308 ዓ.ዓ. ማየ አይኅ ወይም የጥፋት ውኃ በደረሰበት ዓመት የያፌት ዕድሜ 96 ዓመት ያህል ነበር። ሚስቱም አዳታኔሲስ ተብላ በመርከቡ ላይ ደግሞ አመለጠች። በስምምነት ያፌት የተቀበለው የምድር ርስት ዕጣ በአውሮፓ ከጢና ወንዝ (ዶን ወንዝ)ና ከገዲር (ካዲዝ) መካከል ተገኘ፤ ጠረፉም ከገዲር ወደ ምዕራብ ተቀጠለ። (ስለ ያፌት ሚስት ስም በሌሎች ልማዶች ውስጥ፣ ሚስቶች በኖህ መርከብ ላይ ይዩ።)
በጸሐፊው ፍላቪዩስ ዮሴፉስ (1ኛው ክፍለ ዘመን ዓም) ዘንድ ልጆቹ የመሠረቱ ብሔሮች በርሱ ዘመን ገላትያ፣ እስኩቴስ፣ ሜዶን፣ ግሪክ፣ ኢቤሪያ፣ ቀጴዶቅያና ጥራክያ ነበሩ። በበርካታ አውሮፓ አገራት ጥንታዊ ልማዶች ደግሞ ከያፌት ልጆች ተወለዱ። በተለይ ማተሚያ ከተፈጠረ በኋላ ከ1500 ዓም ያህል ጀምሮ የአውሮፓ መኖኩሳት ያሳተሙት መዝገቦች ከያፌት ልጆች ተነሥተው ታረኩ።
በጥንታዊ ግሪክ አፈታሪክ ደግሞ «ያፔቶስ» የተባለው ከኡራኖስ ልጆች (ቲታኖች) መካከልና የክሮኖስ ወንድም ሲሆን፣ መታወቂያው ከያፌት ጋር ግንኙነት እንዳለው ታስቧል። ወንድሙም ሌላው ቲታን ክሮኖስ በተረቶቹ ውስጥ ከካም ጋር ተመሳሳይነቶች አሉት።
በአጠቃላይ የያፌት ልጆች በተለይ ሕንዳዊ-አውሮፓዊ ቋንቋዎችን የተናገሩትን ብሔሮች እንደ መሠረቱ በሰፊ ታስቧል።