የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር፣ በጠላት ወረራ ዘመን የተመሠረተ ድርጅት ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ ያሉት አዛውንት አባላቱ በዚያው የአምሥት ዓመት ትግል ዘመናት፣ መኳንንቱ፤ የጦር መሪዎቻቸውና ንጉሠ ነገሥቱም ጭምር እነዚያን ወጣት ኢትዮጵያውያን አንጀታቸውን ለረሀብ፤ እግራቸውን ለሾኽ ለጠጠር፤ ግንባራቸውን ለእርሳስ አጋልጠዋቸው በካዷቸው መራር ዘመን፤ ሞትም ቢመጣ እናት አገራችንን አሳልፈን ለጠላት አንሰጥም፤ ነፃነታችንን ለጊዜያዊ ሹመት፣ ሽልማት አንለውጥም ብለው የተጋፈጡ ጀግኖች ናቸው።
በጠላት ዘመን
ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፤ “የታሪክ ማስታወሻ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፤ ይህ ማኅበር በአርበኝነት ዘመን በሸዋ ክፍለ ሀገር በ፲፱፻፴፩ ዓ/ም «የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር» በሚል ስም ተሠይሞ የተቋቋመ ማኅበር እንደነበርና ዓላማውም «የአርበኞችን ክብ በማበረታታትና በየሀገሩ ካሉ አርበኞች ጋር በመላላክ የሚገኘውን ሥራ ፍሬ» እርስ በርስም ሆነ በስደት ላይ ከነበሩት ንጉሠ ነገሥት ጋርም መካፈል እንደነበር ይገልጻሉ። [1]
ከመሥራች ማኅበረተኞቹ በከፊሉ፦ ራስ አበበ አረጋይ፤ ወንድማማቾቹ ደጃዝማች ፀሐዩ እና ደጃዝማች ተስፋዬ ዕንቁ ሥላሴ፤ አቶ እምአእላፍ ኅሩይ፤ ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ፤ ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያት ይገኙባቸዋል። በመጀመሪያ ጊዜ የነበሩት መሥራቾች ሃያ ዘጠኝ አባላት ሲሆኑ በኋላ ጊዜ ግን ብዙ ማኅበረተኞች እየተጨመሩ የአባሎቹ ቁጥር ከሦስት መቶ በላይ ሆኖ ነበር።
ከድል በኋላ
የጠላት ኃይል ተሸንፎ የአገሪቱ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ፣ አርበኞቹ በየአውራጃውና በየጠቅላይ ግዛቱ ተሰማርተው ስለነበረና ማኅበሩም በመከራው ዘመናት የተቋቋመበት ዓላማ በነፃነት ጊዜ አላስፈላጊ በመሆኑ፤ የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያሳይ ብዙ ዓመታት አሳለፈ። ሆኖም በሚያዝያ ወር ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ጄኔራል ነጋ ኃይለ ሥላሴ «ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከዕውቅ አገር አፍቃሪዎች ጋራ፥ "ጥንታዊት ኢትዮጵያ ሀገራዊ የዠግኖች ማኅበርን" በታደሰ ሀገራዊ ዓላማና በተሻሻለ ደንብ አቋቋሙ። ኾኖም፥ ድርጅቱ እስከ ሰኔ ፲፱ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ/ም ድረስ ከመንግሥት ዕውቅናን ስላላገኘ ሥራው በዚሁ ምክንያት ለጊዜው ተገታ።» [2]
ጄኔራል ነጋ በዚህ ዕለት ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘውንና ለፍጹም ሰላማዊና ሀገራዊ ዓላማ፤ ለበጎ አድራጎት የተጀመረውን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሀገራዊ የዠግኖች ማኅበር፤ ጠቅላይ ሥራ አመራር ሸንጎ ሊቀ-መንበር ኾነው የማኅበሩን ሥራ በሰፊው በማንቀሳቀስ ባጭር ጊዜ ውስጥ ፬ሺ የፈረሙ አባላትን ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ እንዳስገኙ፥ አሁንም መንግሥታዊ እንቅፋት ገጥሞት ከሕገ-ወጥ በሆነ እርምጃ ፥ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት በጸጥታ ኀይሎች እንዲዘጋ ተደረገ። [3]
ማጣቀሻ
ዋቢ ምንጮች
- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፤ “የታሪክ ማስታወሻ” (፲፱፻፷፩ ዓ/ም)
- የሊ.፡ዤኔራል፡ነጋ፡ኀይለ፡ሥላሴ፡ቤተ፡ሰብ ፤ “ሊየተና ዤኔራል ነጋ ኀይለ ሥላሴ። (አባ፡ይባስ) ፲፱፻፲-፳፻፡ዓ.ም.።” ፤ (ዐምስተኛ፡ዕትም።)፥(ነሐሴ ፳፻ ዓ/ም - ነሐሴ ፳፻፩ ዓ/ም