የግንቦት 7 ፖለቲካዊ ፓርቲ

አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲ ነው

የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ጥረታችን በአመጸኞችና በዕብሪተኞች ድርጊት አይገታም!

መጋቢት 18 ቀን 2011 ዓ.ም

አርበኞች ግንቦት 7 እንደ ንቅናቄ ለረጅም ዓመታት ከታገለላቸዉ መብቶች ዉስጥ አንዱ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ባልተስማማበት ሀሳብ፥ ፖሊሲና ፕሮግራም ላይ ህግና ደንብን እስካከበረ ድረስ ያለምንም መከልከል በፈለገዉ መንገድ ተቃዉሞዉን መግለጽ እንዲችል ነዉ። የሌሎችን መብት ሳይነካ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚደረግ ተቃዉሞ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሂደት አካል ነዉና ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 እንደዚህ ዓይነት ተቃዉሞዎች በራሱም ላይ ቢመጡ አስተማሪም ናቸዉና በጸጋ ነዉ የሚቀበለዉ። አርበኞች ግንቦት 7 በአምባገነን ሥርዓት ዉስጥ የሚኖሩ ዜጎች መብታቸዉ ተረግጦ ሀሳባቸዉን፣ ድጋፋቸዉንና ተቃዉሟቸዉን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መግለጽና ማሰማት ሲያቅታቸዉ፣ በማናቸዉም የሁለገብ የትግል ዘዴ ተጠቅመዉ የሚደርስባቸዉን ጥቃት መከላከልና የእነሱንም ሆነ የሌሎችን መብትና ነጻነት የማስከበር ተፈጥሯዊ መብት እንዳላቸዉ የሚያምን ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱም የሚታገል ድርጅት ለመሆኑ የቅርብ ጊዜ ታሪኩ ምስክር በመሆኑ ይህንን ከማናቸዉም ድርጅቶች ወይም ቡድኖች በላይ ጠንቅቆ የሚያዉቀዉ ጉዳይ ነዉ። ነገር ግን ዛሬ አገራችን ዉስጥ በግልጽ የሚታየዉ የዜጎች መብትና ነጻነት ሁኔታ በምንም ዓይነት ህገወጥነትንና አመጽን አማራጭ ለማድረግ የሚያሰገድድ ነዉ ብሎ አያምንም።

ባለፈዉ እሁድ መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ባህርዳር ዉስጥ አርበኞች ግንቦት 7 ያዘጋጀዉ ህዝባዊ ስብሰባ እንዳይካሄድና ህዝብ ሀሳቡን በነጻ እንዳይገልጽ መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች የወሰዱት ፍጹም ፀረ ሰላም የሆነ እርምጃ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈዉ በአርበኞች ግንቦት 7 ላይ ብቻ ሳይሆን አገርን ለማረጋጋት በሚደረገዉ ከፍተኛ ጥረት ላይና ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የረጅም ጊዜ የዴሞክራሲ ጥማቱን ለማርካት በሚያደርገዉ አገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ነዉ። የእሁዱ የባህርዳር ድርጊት በአንድ በኩል የተለያዩ ፀረ ለዉጥና ፀረ ሰላም ኃይሎች የጋራ ድርጊት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድርጊቱ በተናጠል፣ በአንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ ላይ የተወሰደ እርምጃ ሳይሆን፣ ለዘመናት ሲረገጥና ሲገፋ ለኖረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የመጨረሻ እድል በሆነዉ የለዉጥ ሂድት ላይ የተቃጣ አደገኛና ነገ ዛሬ ሳይባል በአፋጣኝ መቆም ያለበት የሁላችንም ፈተና ነዉ ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ከልቡ ያምናል። ስለሆነም አርበኞች ግንቦት 7 ይህንን አገራዊ ችግር ከምንም ነገር በላይ አክብዶ አይቶታል።

አርበኞች ግንቦት 7 ስለራሱ፥ ስለቤተሰቡ፥ ስለወገኑና ሰለ አገሩ የሚያስብ እያንዳንዱ ዜጋ፣ ቡድን፣ ድርጅት እንዲሁም የክልልና የፌዴራል መንግስት አካላት ባለፈዉ እሁድ ባህርዳር ዉስጥ የታየዉን አይነት በአደባባይ በነፍጥ የተደገፈ የእብሪት እንቅስቃሴ ገና በጥሬዉ የማስቆምና ድርጊቱን በማይሻማ ቋንቋ የማዉገዝ አገራዊ ኃላፊነት አለበት ብሎ ያምናል። እንደዚህ አይነት ፀረ ለዉጥና ፀረ ዲሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን በእንጭጩ መቅጨት ካልተቻለ ነገ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን በመደገፍም ሆነ በመቃወም የሚደረጉ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ሁላችንንም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍሉና ማናችንም በምንም አይነት ሁኔታ ከዚህ ጥፋት ማምለጥ እንደማንችል ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል።

የምርጫ ቦርድና ተፎካካሪ ድርጅቶች፣ ባለፈዉ እሁድ ባህርዳር ዉስጥ የታየዉ አደገኛ እንቅስቃሴ እየሰፋ ከሄደ በለዉጡ የተከፈተዉ የፖለቲካ ምህዳር ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊዘጋ እንደሚችል ተገንዝባችሁ ድርጊቱን የፈጸሙና እንዲፈጸም ያገዙ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ ለማድረግ በሚደረገዉ ጥረት ላይ የየራሳችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪዉን ያቀርባል።

ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራልም ሆነ የክልል የህግ አስከባሪ አካላት ባህርዳር ዉስጥ የተፈጸመዉንና የዜጎችን መብትና ነጻነት የረገጠዉን ድርጊት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ያቀዱ፣ የረዱና በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን ለህግ አቅርባችሁ አስፈላጊዉን የህግ እርምጃ እንድትወስዱና የወሰዳችሁትን እርምጃ ለመላዉ የሀገራችን ሕዝብ እንድታስታዉቁ አደራ እያልን፣ የዜጎችን መብትና ነጻነት ለማስከበር በምታደርጉት ጥረት ድርጅታችን አስፈላጊዉን ትብብር እንደሚያደርግ ከወዲሁ መግለጽ እንወዳለን። በባህርዳሩ ስብሰባ ተገኝታችሁ ነጻ የሃሳብ ልዉዉጥ ለማድረግ ግዜያችሁን ሰዉታችሁ ወደ አዳራሹ ከገባችሁ በኋላ አመጸኞችና ዕብሪተኞች በፈጠሩት ችግር የዜግነት መብታችሁን መጠቀም ላልቻላችሁ ወገኖቻችን በሙሉና ከቅርብና ከሩቅ ሆናችሁ በባህርዳሩ አሳዛኝ ድርጊት ለተበሳጫችሁና ለተናደዳችሁ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አርበኞች ግንቦት 7 የተሰማዉን ልባዊ ሀዘን ለመግለጽ ይወዳል። በሌላ በኩል ግን አሁን በሚደርሰን መረጃ መሰረት የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች፣ የባህርዳሩን የዕብሪት ድርጊት ባቀነባበሩ፥በረዱና በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ የአመጽ እርምጃ እንወስዳለን የሚለዉ አስተሳሰብ እናንተን፣ ንቅናቄያችንን እና በአጠቃላይ ዛሬ የተያያዝነዉን የለዉጥ ጉዞ በፍጹም የማይመጥን ከመሆኑም በላይ የአመጸኞቹን ድርጊት የሚደግምና ከነሱ እጅግ በጣም በተሻለ መንገድ የምናስብ መሆናችንን የማያሳይ እርምጃ ነዉና ከዚህ ዓይነት አስተሳሰብ እንድትታቀቡ እናሳሰባለን። እንዳዉም ይህንን አጋጣሚ አርበኞች ግንቦት 7፣ ለዜጎች መብትና ነጻነት፣ ለሰላም መስፈን እና ለህግ መከበር የሚሰጠዉን ከፍተኛ ቦታ ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ አብረን የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ አድርጋችሁ እንድትወስዱት አደራ እያልን፣ ድርጅታችን ከሚመለከታቸዉ የክልልም ሆነ የፌድራል ህግ አስከባሪ አካላት ጋር አጥፊዎቹ በህግ እስኪጠይቁ ድረስ በምንም ዓይነት የማንተወዉ ጉዳይ መሆኑ ልናረግጥለችሁ እንወዳለን።

ህግና ሥርዓት ከልተከበረ ሰላም አይኖርም፣ ሰላም ከሌላ ሀገርና ህዝብ አይኖርም! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጥፋት ይጠብቅ!

የፖለቲካ ራእይ ወደፊት እያየን የሚወሰን ይሆናል ለውጡን ማንም ያምጣው ማን እንዳይቀለበስ አእንተጋለን ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ቦንገር ዋና ሊቀመንበር

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.