የአሜሪካ ታላቅ ማኅተም

አሜሪካ ብሔራዊ ምልክት የአሜሪካ ታላቅ ማኅተም ይባላል። መጀመርያው የተገለጸው በ1774 ዓ.ም. ነበር። እንዲያውም በይፋ 'አርማ' ሳይሆን 'ማኅተም' ነው። ነገር ግን ይፋዊ አርማ ስለማይኖር በዘልማድ ይህ ማኅተም እንደ አርማ ይጠቀማል። በአሜሪካ ዶላር ላይ (ከ1927 ዓ.ም. ጀምሮ) እንዲሁም በአሜሪካ ፓስፖርት ላይ ይታያል።

የአሜሪካ ታላቅ ማኅተም (ፊት)

ፊት

በማኅተሙ ፊት ላይ ክንፎቹን የሚዘረጋ የመላጣ ንሥር ስዕል እሱም የአሜሪካ ምልክት ይታያል። በግራው ጥፍሩ (ከንሥሩ አንጻር) ውስጥ አሥራ ሦስት ፍላጻ ይዟል። እነርሱም ከእንግሊዝ ያመጹ የመጀመርያ 13 ክፍላገሮች ያመልክታሉ። በቀኙም ጥፍር የወይራ ቅርንጫፍ ይይዛል። ይህ 13 ቅጠልና 13 ፍሬዎች አሉበት። ፍላጻ የጦር ምልክትና ወይራ የሰላም ምልክት በመሆኑ የንሥሩ ራስ ወደሱ ቀኝ ሲዞር ስላምን ይመርጣል እንደ ማለት ነው። በመንቁራው ውስጥ ደግሞ E PLURIBUS UNUM የሚለውን መፈክር ይይዛል። ይህም በሮማይስጥ ማለት 'አንድ ከብዙ' ነው። ከራሱ በላይ 13 ከዋክብት በሰማያዊ በስተኋላ መደብ አለ። እኚህ ከዋክብት የዳዊት ኮከብ ይሠራሉ። በፍርምባው ላይ የሚሸክመው ጋሻ እንደ አሜሪካ ሰንደቅ አለማ ዝንጉርጉር ነው።

ጀርባ

የአሜሪካ ታላቅ ማኅተም (ጀርባ)

በማኅተሙ ጀርባ ላይ ያልተጨረሰ ሀረም (ፒራሚድ) ይታያል። ይህ 13 ደረጃዎች ሲኖሩት በመሠረቱ ላይ MDCCLXXVI ይላል። ይህ በሮማይስጥ ቁጥሮች ማለት '፼፯፻፸፮' ወይም 1776 ሲሆን በአውሮጳውያን አቆጣጠር የአሜሪካ ነጻነት አዋጅ የተፈረመበት አመት (1768 ዓ.ም.) ለማመልከት ነው። በሀረሙ ጫፍ ፈንታ 'የእግዚአብሔር ጥበቃ ዓይን' የሚባል ምልክት ይታያል። በዚሁ ዙሪያ «ANNUIT CŒPTIS» የሚለው መፈክር አለ፤ ይህም በሮማይስጥ 'የተጀመረው ተስማምቶታል' ለማለት ነው። በግርጌው ደግሞ «NOVUS ORDO SECLORUM» የሚል መፈክር እያለ ይህ ትርጉም 'የዘመናት አዲስ ሥርዓት' ነው።

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.