ዛልፓ

ዛልፓ ወይም ዛልፑዋ በትንታዊ አናቶሊያጥቁር ባሕር ጠረፍ ላይ የተገኘ ከተማ-አገር ነበረ። ሥፍራው በእርግጥ አልተገነም።

የዛልፓ ሥፍር ያሕል በጥቁር ባሕር ላይ

በአንድ ትውፊት እንዲህ ይላል፦ «የካነሽ ንግሥት አንዴ ፴ ወንድ ልጆች በአንድ ዓመት ወለደች። «ይህን ያህል ሥራዊት የወለድኩ ምንድነው?» አለች። ፋንዲያ በቅርጫት አዘጋጅታ ልጆቿን ሰክታ በወንዝ ላይ ሰደደቻቸው። ወንዙ ወደ ባሕር በዛልፓ ምድር ወሰዳቸው። ከዚያ አማልክት ከባሕሩ አውጥተዋቸው አሳደጓቸው። ጥቂት ዓመታት ሲያልፉ ንግሥቷ እንደገና ወለደች፣ ይህ ጊዜ ፴ ሴት ልጆች ወለደች። በዚህ ጊዜ እርስዋ እራሷ አሳደገቻቸው።» ወንዶቹም አድገው በኋላ ወደ ካነሽ ተጉዘው ሳያውቁ እኅታቸውን ያግባሉ፤ ከዚህ ቀጥሎ ግን ምን እንደ ሆነ ከጽላቱ ጠፍቷል። ይህ አፈ ታሪክ የጥንታዊ ግሪክ ጸሐፍት እንደ ዘገቡት የአማዞኖች ትውፊት ይመስላል። [1]

በ1745 ዓክልበ. ግድም የዛልፒያ ንጉሥ ኡሕና ካነሽን ዘርፎ ጣኦታቸውን ወደ ዛልፒያ ወሰደ። በዚህ ሰዓት ደግሞ የአሦር ነጋዴዎች ሠፈር (ካሩም) እንዳቃጠለው ይታሥባል።

በኋላ ግን ምናልባት 1662 ዓክልበ. አካባቢ የካነሽ ንጉሥ አኒታ ዛልፑዋን ዘርፎ ጣዖቱን ንጉሣቸውንም ሑዚያ ወደ ካነሽ አመጣ።

«የዛልፓ ጽሑፍ» በተባለ ሌላ መዝገብ ዘንድ፣ የዛልፑዋ ንጉሥ ፐርዋ የሃቱሳሽ ንጉሥ ሴት ልጅ አግብቶ ነበር። በከተማው ግን የፐርዋ ሎሌ አሉዋ ሁከት አደረገና እርሷ ተገደለች። ስለዚህ ጥፋት የሐቱሳሽ ሥራዊት ጦርነት አድርጎ አሉዋን ገደሉና የዛልፓ ሕዝብ ወደ ተራሮች ሸሹ። ከተመለሱ በኋላ የሐቱሳሽ ንጉሥ ልጁን ሐካርፒሊሽ በዛልፓ ዙፋን ሾመው፤ እሱ ግን በዛልፓ በአባቱ ላይ አመጸ። የሐቱሳሽ ንጉሥ ዛልፓን ከበበው፤ ተከታዩም ያዘው። በአንድ አስተያየት፣ በሰነዱ መጀመርያው «የሐቱሳሽ ንጉሥ» ሕሽሚ-ሻሩማ ነው፤ ተከታዩም ላባርና ነው። የሰነዱም ደራሲ የላባርና ተከታይ 1 ሐቱሺሊ መሆኑ ይታመናል[2]

ኬጥያውያን መንግሥት ንጉሥ 1 አርኑዋንዳ ዘመን (14ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ.) በተጻፈ ጸሎት ዛልፒያ ይጠቀሳል፤ የካስካ ሰዎች ዛልፓንና ኔሪክን እንደ ያዙ ይመስላል።

  1. http://rbedrosian.com/Memyth.htm
  2. Richard H. Beal, "The Predecessors of Hattusili I" in Hittite Studies in Honor of Harry A. Hoffner, Jr, 2003.
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.