ዔግሎም

ዔግሎም (ዕብራይስጥ፦ עֶגְלוֹן‎ /ዔግሎን/) በብሉይ ኪዳን መጽሐፈ መሣፍንት 3:12-30 መሠረት ዕብራውያንን ለ18 ዓመት የገዛ የሞዓብ ንጉሥ ነበር። ይህ በቅደም-ተከተል 1457-1439 ዓክልበ. ነበር።

ናዖድ ዔግሎምን በሰይፍ ሲገድል፣ በ1352 ዓም እንደ ተሳለ

ከፈራጁ ጎቶንያል በኋላ እስራኤላውያን እንደገና ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ዔግሎምን አበረታባቸው ይላል። ከሞዓብ ጭምር የአሞንና የአማሌቅ ሰዎችን ሰብስቦ ነበር። እነዚህ እንደ ሞዓባውያንና ዕብራውያን ሁሉ ሴማዊ ነገዶች ነበሩ፣ ከአብርሃም ወይም ከሎጥ ተወልደው ነበር። ከእስራኤልም «ዘንባባም ያለባትን ከተማ ያዙአት» ይላል።

እስራኤላውያን እንደገና ወደ እግዚአብሐር ሲጮኹ፣ ብንያማዊው የጌራ ልጅ ናዖድ ግራኙ ይነሣል። እሱ ሰይፉን ደብቆ ለወፍራም ንጉሡ ግብርን አስመስሎት ገደለው። ይህ የተደረገበት ቦታ ጌልገላ ተባለ ሲል (3:19)፣ የኢያሪኮ ዙሪያ ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ናዖድ ወደ ሴይሮታ (3:26) እና ወደ ተራራማ ኤፍሬም አገር (3:27) አምልጦ እስራኤላውያን ከዚያ ወረዱና የዮርዳኖስ ወንዝ መሻገርያ ይዘው (3:28) አሥር ሺህ ሞዓባውያንን ገደሉ። አገሩም 80 ዓመት ነጻ ነበር (1439-1359 ዓክልበ.)።

በቅደም-ተከተል ሲመለከት፣ እስራኤል ለዔግሎን የተገዙባቸው 18 ዓመታት የግብጽ ፈርዖን 3 ቱትሞስሶርያ አካባቢ ይዘመት ነበር። በተለይ በአንድ ዘመቻ በ1449 ዓክልበ. በከነዓን በሻሱ ወገን ላይ እንደ ዘመተ ይዘግባል። «ሻሱ» ማለት «ዘላኖች» ሲሆን አንዳንዴ በሞዓብ ወይም ኤዶምያስ፣ አንዳንዴም ከዮርዳኖስ ምዕራብ ተገኙ። በአንድ አስተሳሰብ ሻሱ ሞዓባውያን ነበሩ፤ ሌሎች ግን የእስራኤል ወላጆች ያደርጓቸዋል። እነዚህም ሻሱ ከሐቢሩ ብሔር ደግሞ የተለዩ ነበሩ። በመሳፍንት እስራኤላውያን የተገኙባቸው የኤፍሬም ተራሮች ከዮርዳኖስ መሻገርያ በላይ እንደ ነበሩ ይመስላል።

አይሁድ ተረቶች ዘንድ በመጽሐፈ ሩት ያለችው ሞዓባዊት ሩት የንጉሥ ዔግሎም ልጅ ነበረች፣ ከዚህም በላይ ዔግሎም የቀድሞው ሞዓብ ንጉሥ (በሙሴ ዘመን) የባላቅ ልጅ ልጅ ነበረ። ሆኖም ለዚህ መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም መሠረት የለም።

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.