ኦጋዴን

ኦጋዴን (ቀድሞ ውጋዴን) በኢትዮጵያሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኝ የደቡብ-ምሥራቅ ግዛት ነው። የግዛቱ ቆዳ ስፋት ወደ ሁለት መቶ ሺህ ካሬ ኪሎሜትር ሲሆን ከጅቡቲኬንያ እና ከሶማልያ ጋር አዋሳኝ ድንበሮች አሉት። ጅጅጋ፣ ደጋቡር፣ ጎዴ፣ ቀብሪዳር እና ወርዲር የመሳሰሉ ከተሞች ይገኙበታል።

አጭር ታሪክ

ኦጋዴን በ ፲፫ኛው እና በ ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመናት በይፋት እስላማዊ ግዛት ሥር ነበር። ከ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ እስከ ፲፱ ነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ይኼው ሥፍራ የአዳል ንጉዛት እንደነበረና በየጊዜው ከአበሻ (ኢትዮጵያ) ክርስቲያናዊ ንጉዛት ጋር ሲዋጋ እንደነበር ታሪክ ይተርካል።

ዓፄ ልብነ ድንግል በነገሡ በአሥራ አምስተኛው ዓመት ማለትም በ ፲፭፻፸፪ ዓ/ም ግራኝ መሐመድ በሚል ስም የሚታወቀው የአዳል ጀኔራል አህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋዚ የመራው ጦር በይፋት በማፉድ በኩል መጥቶ ዓፄ ልብነ ድንግልን በየሄዱበት ሥፍራ እየተከታተለ ሲወጋቸው ንጉሠ ነገሥቱ ልጆቻቸውን እና ቤተሰባቸውን ይዘው ከሸዋ ወደ አማራው አገር በኋላም ወደ ትግራይ ኮበለሉ። ወዲያውም ትግራይ ላይ ሲሞቱ ልጃቸው ዓፄ ገላውዴዎስ ዙፋኑን ከወረሱ በኋላ በፖርቱጋል ወታደሮች ዕርዳታ መሐመድ ግራኝን ድል አድርገው ገደሉት።

በ፲፱ ነኛው ክፍለ ዘመን ግዛቱ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ተማርኮ ከኢትዮጵያ ጋር ተዋሃደ። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅጅጋ በስተምሥራቅ ያለውን አካል ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ሳይችል ቆይቶ መጨረሻ ላይ በ ፲፱፻፳፮ ዓ/ም የእንግሊዝ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት የድንበር ስምምነት ለማድረግ ሞክረው ነበር።

ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በግፍ በወረረ ጊዜ የኦጋዴንን ግዛት ከጣልያን ሶማልያ ጋር አቀላቅለውት ነበር። እንግሊዝ የጣልያን ምሥራቅ አፍሪቃን ከጣልያን በማረከች ጊዜ ኦጋዴንን እና የጣልያን ሶማልያን ከእንግሊዝ ሶማልያ ጋር ቀላቅለው «ታላቋ ሶማልያ» የሚባል ግዛት ለመፍጠር ዶልተው ነበር። ይኼንንም ኃሣብ ብዙ የኦጋዴን ሶማሌዎች ደግፈውት እንደነበር ይወሳል። በ፲፱፻፵ ዓ/ም እንግሊዞች ኦጋዴንን ለኢትዮጵያ መንግሥት መለሱ።

በሙክታል ዳሂር የሚመራው የምዕራብ ሶማልያ ነጻነት ግንባር የኢትዮጵያን መንግሥት በደፈጣ ሲዋጋ በሲያድ ባሬ መሪነት የሶማልያ ሠራዊት ኦጋዴንን ሲወር በሁለቱ አገሮች መኻል የመጀመሪያው ጦርነት ተካሄደ።

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.