ወደ ሮማውያን ፫
ወደ ሮማውያን በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያው መልዕክት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንጦስ እያለ በ፶፮ - ፶፰ ዓ.ም. የጻፈው መልዕክት ነው ። ይህ ምዕራፍ ፫ ሲሆን በ፴፩ ንዑስ ክፍሎች ይከፈላል ።
ወደ ሮማውያን ፫ | |
---|---|
| |
አጭር መግለጫ | |
ፀሐፊ | ጳውሎስ |
የመጽሐፍ ዐርስት | ወደ ሮማውያን |
የሚገኘው | በአዲስ ኪዳን ፮ኛው መጽሐፍ |
መደብ | የጳውሎስ መልዕክት |
ቅዱስ ጳውሎስ ለሮማውያን መልዕክቱን የጻፈበት ምክኒያት አይሁዳውያንና ሮማውያን በሰላም አንድላይ በሮም ለብዙ ዘመን ሲኖሩ ቆይተው ክርስትና በተመሠረተበት ወቅት ፣ አይሁዳውያን ክርስቶስ እኛን ነው የመረጠን ለመንግሥቱ እናንተን አይደለም... ሲሊ ሮማውያን ደግሞ እናንተ ሰቀላችሁት እንጂ ምን አረጋቹህለት... እየተባባሉ እርስበርሳቸው ጥል ስለፈጠሩ እነሱን ለማስታረቅ ጻፈው ።
የሐዋርያው የጳውሎስ፡ መልእክት ወደ ሮማውያን ምዕራፍ ፫
ቁጥር ፩ - ፲
1፤እንግዲህ፡የአይሁዳዊ፡ብልጫው፡ምንድር፡ነው፧ወይስ፡የመገረዝ፡ጥቅሙ፡ምንድር፡ነው፧በዅሉ፡ ነገር፡ብዙ፡ነው። 2፤አስቀድሞ፡የእግዚአብሔር፡ቃላት፡ዐደራ፡ተሰጧቸው።ታዲያ፡ምንድር፡ነው፧ 3፤የማያምኑ፡ቢኖሩ፡አለማመናቸው፡የእግዚአብሔርን፡ታማኝነት፡ያስቀራልን፧ 4፤እንዲህ፡አይኹን፤ በቃልኽ፡ትጸድቅ፡ዘንድ፡ወደ፡ፍርድ፡በገባኽም፡ጊዜ፡ትረታ፡ዘንድ፡ ተብሎ፡እንደ፡ተጻፈ፥ሰው፡ዅሉ፡ ውሸተኛ፡ከኾነ፡እግዚአብሔር፡እውነተኛ፡ይኹን። 5፤ነገር፡ግን፥ዐመፃችን፡የእግዚአብሔርን፡ጽድቅ፡የሚያስረዳ፡ከኾነ፡ምን፡እንላለን፧ቍጣን፡ የሚያመጣ፡እግዚአብሔር፡ዐመፀኛ፡ነውን፧እንደ፡ሰው፡ልማድ፡እላለኹ። 6፤እንዲህ፡አይኹን፤እንዲህ፡ቢኾን፡እግዚአብሔር፡በዓለም፡እንዴት፡ይፈርዳል፧ 7፤በእኔ፡ውሸት፡ግን፡የእግዚአብሔር፡እውነት፡ለክብሩ፡ከላቀ፡ስለምን፡በእኔ፡ደግሞ፡እንደ፡ ኀጢአተኛ፡ ገና፡ይፈርድብኛል፧ 8፤ስለ፡ምንስ፡መልካም፡እንዲመጣ፡ክፉ፡አናደርግም፧እንዲሁ፡ይሰድቡናልና፥አንዳንዱም፡ እንዲሁ፡እንድንል፡ይናገራሉና።የእነርሱም፡ፍርድ፡ቅን፡ነው። 9፤እንግዲህ፡ምን፡ይኹን፧ከነርሱ፡እንበልጣለንን፧ከቶ፡አይደለም፤አይሁድም፡የግሪክ፡ሰዎችም፡ ዅሉ፡ከኀጢአት፡በታች፡እንደ፡ኾኑ፡አስቀድመን፡ከሰናቸዋልና፤
10፤እንዲህ፡ተብሎ፡እንደ፡ተጻፈ፦
ቁጥር ፲፩ - ፳
11፤ጻድቅ፡የለም፡አንድ፡ስንኳ፤አስተዋይም፡የለም፤እግዚአብሔርንም፡የሚፈልግ፡የለም፤ዅሉ፡ ተሳስተዋል፥ 12፤በአንድነትም፡የማይጠቅሙ፡ኾነዋል፤ቸርነት፡የሚያደርግ፡የለም፥አንድ፡ስንኳ፡የለም። 13፤ጕረሯቸው፡እንደ፡ተከፈተ፡መቃብር፡ነው፥በምላሳቸውም፡ሸንግለዋል፤የእባብ፡መርዝ፡ ከከንፈሮቻቸው፡በታች፡አለ፤ 14፤አፋቸውም፡ርግማንና፡መራርነት፡ሞልቶበታል፤ 15፤እግሮቻቸው፡ደምን፡ለማፍሰስ፡ፈጣኖች፡ናቸው፤ 16፤ጥፋትና፡ጕስቍልና፡በመንገዳቸው፡ይገኛል፥ 17-18፤የሰላምንም፡መንገድ፡አያውቁም።በዐይኖቻቸው፡ፊት፡እግዚአብሔርን፡መፍራት፡የለም። 19፤አፍም፡ዅሉ፡ይዘጋ፡ዘንድ፡ዓለምም፡ዅሉ፡ከእግዚአብሔር፡ፍርድ፡በታች፡ይኾን፡ዘንድ፡ ሕግ፡የሚናገረው፡ዅሉ፡ከሕግ፡በታች፡ላሉት፡እንዲናገር፡እናውቃለን፤ 20፤ይህም፡የሕግን፡ሥራ፡በመሥራት፡ሥጋ፡የለበሰ፡ዅሉ፡በርሱ፡ፊት፡ስለማይጸድቅ፡ነው፤ ኀጢአት፡በሕግ፡ ይታወቃልና።
ቁጥር ፳፩ - ፴፩
21፤አኹን፡ግን፡በሕግና፡በነቢያት፡የተመሰከረለት፡የእግዚአብሔር፡ጽድቅ፡ያለሕግ፡ተገልጧል፥ 22፤ርሱም፥ለሚያምኑ፡ዅሉ፡የኾነ፥በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡በማመን፡የሚገኘው፡የእግዚአብሔር፡ጽድቅ፡ ነው፤ልዩነት፡የለምና፤ 23፤ዅሉ፡ኀጢአትን፡ሠርተዋልና፥የእግዚአብሔርም፡ክብር፡ጐድሏቸዋል፤ 24፤በኢየሱስ፡ክርስቶስም፡በኾነው፡ቤዛነት፡በኩል፡እንዲያው፡በጸጋው፡ይጸድቃሉ። 25፤ርሱንም፡እግዚአብሔር፡በእምነት፡የሚገኝ፡በደሙም፡የኾነ፡ማስተስረያ፡አድርጎ፡አቆመው፤ይህም፡ በፊት፡የተደረገውን፡ኀጢአት፡በእግዚአብሔር፡ችሎታ፡ስለ፡መተው፡ጽድቁን፡ያሳይ፡ዘንድ፡ነው፥ 26፤ራሱም፡ጻድቅ፡እንዲኾን፡በኢየሱስም፡የሚያምነውን፡እንዲያጸድቅ፡አኹን፡በዚህ፡ዘመን፡ጽድቁን፡ያሳይ፡ ዘንድ፡ነው። 27፤ትምክሕት፡እንግዲህ፡ወዴት፡ነው፧ርሱ፡ቀርቷል።በየትኛው፡ሕግ፡ነው፧በሥራ፡ሕግ፡ ነውን፧አይደለም፥በእምነት፡ሕግ፡ነው፡እንጂ። 28፤ሰው፡ያለሕግ፡ሥራ፡በእምነት፡እንዲጸድቅ፡እንቈጥራለንና። 29-30፤ወይስ፡እግዚአብሔር፡የአይሁድ፡ብቻ፡አምላክ፡ነውን፧የአሕዛብስ፡ደግሞ፡አምላክ፡ አይደለምን፧አዎን፥የተገረዘን፡ስለ፡እምነት፡ያልተገረዘንም፡በእምነት፡የሚያጸድቅ፡አምላክ፡አንድ፡ስለ፡ኾነ፡ የአሕዛብ፡ደግሞ፡አምላክ፡ነው። 31፤እንግዲህ፡ሕግን፡በእምነት፡እንሽራለንን፧አይደለም፤ሕግን፡እናጸናለን፡እንጂ።