ወደ ሮማውያን ፩
ወደ ሮማውያን በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያው መልዕክት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንጦስ እያለ በ፶፮ - ፶፰ ዓ.ም. የጻፈው መልዕክት ነው ። ከመልዕክቶቹ ሁሉ ረዥም ይኸው ወደ ሮማውያን ነው ፣ በ፲፮ ምዕራፎች ይከፈላል ። ይህኛው ምዕራፍ ፩ ሲሆን ፴፪ ንዑስ ክፍሎችን ያካትታል ።
ወደ ሮማውያን ፩ | |
---|---|
| |
አጭር መግለጫ | |
ፀሐፊ | ጳውሎስ |
የመጽሐፍ ዐርስት | ወደ ሮማውያን |
የሚገኘው | በአዲስ ኪዳን ፮ኛው መጽሐፍ |
መደብ | የጳውሎስ መልዕክት |
ቅዱስ ጳውሎስ ለሮማውያን መልዕክቱን የጻፈበት ምክኒያት አይሁዳውያንና ሮማውያን በሰላም አንድላይ በሮም ለብዙ ዘመን ሲኖሩ ቆይተው ክርስትና በተመሠረተበት ወቅት ፣ አይሁዳውያን ክርስቶስ እኛን ነው የመረጠን ለመንግሥቱ እናንተን አይደለም... ሲሊ ሮማውያን ደግሞ እናንተ ሰቀላችሁት እንጂ ምን አረጋቹህለት... እየተባባሉ እርስበርሳቸው ጥል ስለፈጠሩ እነሱን ለማስታረቅ ጻፈው ። መገለጥ ያለበት የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነም ጻፈው ።
ቆሮንጦስ | |
የቆሮንጦስ ወደብ መግቢያ ግሪክ ቆሮንጦስ |
የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮማውያን ምዕራፍ ፩
ቁጥር ፩ - ፲
1-2፤ሐዋርያ፡ሊኾን፡የተጠራ፡የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ባሪያ፡ጳውሎስ፥በነቢያቱ፡አፍ፣በቅዱሳን፡መጻሕፍት፡ አስቀድሞ፡ተስፋ፡ለሰጠው፡ለእግዚአብሔር፡ወንጌል፡ተለየ። 3-4፤ይህም፡ወንጌል፡በሥጋ፡ከዳዊት፡ዘር፡ስለ፡ተወለደ፥እንደ፡ቅድስና፡መንፈስ፡ግን፡ከሙታን፡መነሣት፡ የተነሣ፡በኀይል፡የእግዚአብሔር፡ልጅ፡ኾኖ፡ስለተገለጠ፣ስለ፡ልጁ፡ነው፤ርሱም፡ጌታችን፡ኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ ነው። 5፤በርሱም፡ስለ፡ስሙ፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡መካከል፡ከእምነት፡የሚነሣ፡መታዘዝ፡እንዲገኝ፡ጸጋንና፡ ሐዋርያነትን፡ተቀበልን፤ 6፤በእነርሱም፡መካከል፡የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ልትኾኑ፡የተጠራችኹ፡እናንተ፡ደግሞ፡ናችኹ። 7፤በእግዚአብሔር፡ለተወደዳችኹና፡ቅዱሳን፡ልትኾኑ፡ለተጠራችኹ፡በሮሜ፡ላላችኹት፡ዅሉ፥ከእግዚአብሔር፡ ከአባታችን፡ከጌታም፡ከኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ጸጋና፡ሰላም፡ለእናንተ፡ይኹን። 8፤እምነታችኹ፡በዓለም፡ዅሉ፡ስለ፡ተሰማች፡አስቀድሜ፡ስለ፡ዅላችኹ፡አምላኬን፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ አመሰግናለኹ። 9-10፤በልጁ፡ወንጌል፡በመንፈሴ፡የማገለግለው፡እግዚአብሔር፡ምስክሬ፡ነውና፤ምናልባት፡ብዙ፡ቈይቼ፡ ወደ፡እናንተ፡አኹን፡እንድመጣ፡በእግዚአብሔር፡ፈቃድ፡መንገዴን፡እንዲያቀናልኝ፡እየለመንኹ፡ዅልጊዜ፡ ስጸልይ፡ስለ፡እናንተ፡ሳላቋርጥ፡አሳስባለኹ።
ቁጥር ፲፩ - ፲፱
11፤ትጸኑ፡ዘንድ፡መንፈሳዊ፡ስጦታ፡እንዳካፍላችኹ፡ላያችኹ፡እናፍቃለኹና፤ 12፤ይህንም፡ማለቴ፡በመካከላችን፡ባለች፡በእናንተና፡በእኔ፡እምነት፡ዐብረን፡በእናንተ፡እንድንጽናና፡ነው። 13፤ወንድሞች፡ሆይ፥በሌላዎቹ፡አሕዛብ፡ደግሞ፡እንደ፡ኾነ፡በእናንተም፡ፍሬ፡አገኝ፡ዘንድ፡ብዙ፡ጊዜ፡ ወደ፡እናንተ፡ልመጣ፡እንዳሰብኹ፡እስከ፡አኹን፡ግን፡እንደ፡ተከለከልኹ፡ታውቁ፡ዘንድ፡እወዳለኹ። 14፤ለግሪክ፡ሰዎችና፡ላልተማሩም፥ለጥበበኛዎችና፡ለማያስተውሉም፡ዕዳ፡አለብኝ፤ 15፤ስለዚህም፡በሚቻለኝ፡መጠን፡በሮሜ፡ላላችኹ፡ለእናንተ፡ደግሞ፡ወንጌልን፡ልሰብክ፡ተዘጋጅቻለኹ። 16፤በወንጌል፡አላፍርምና፤አስቀድሞ፡ለአይሁዳዊ፡ደግሞም፡ለግሪክ፡ሰው፥ለሚያምኑ፡ዅሉ፡የእግዚአብሔር፡ ኀይል፡ለማዳን፡ነውና። 17፤ጻድቅ፡በእምነት፡ይኖራል፡ተብሎ፡እንደ፡ተጻፈ፡የእግዚአብሔር፡ጽድቅ፡ከእምነት፡ወደ፡እምነት፡በርሱ፡ ይገለጣልና። 18፤እውነትን፡በዐመፃ፡በሚከለክሉ፡ሰዎች፡በኀጢአተኝነታቸውና፡በዐመፃቸው፡ዅሉ፡ላይ የእግዚአብሔር፡ ቍጣ፡ከሰማይ፡ይገለጣልና፤ 19፤እግዚአብሔር፡ስለ፡ገለጠላቸው፥ስለ፡እግዚአብሔር፡ሊታወቅ፡የሚቻለው፡በእነርሱ፡ዘንድ፡ግልጥ፡ ነውና።
ቁጥር ፳ - ፳፱
20-21፤የማይታየው፡ባሕርይ፥ርሱም፡የዘለዓለም፡ኀይሉ፥ደግሞም፡አምላክነቱ፥ከዓለም፡ፍጥረት፡ዠምሮ፡ ከተሠሩት፡ታውቆ፥ግልጥ፡ኾኖ፡ይታያልና፤ስለዚህም፡እግዚአብሔርን፡እያወቁ፡እንደ፡እግዚአብሔርነቱ፡ መጠን፡ስላላከበሩትና፡ስላላመሰገኑት፡የሚያመካኙት፡ዐጡ፤ነገር፡ግን፥በዐሳባቸው፡ከንቱ፡ ኾኑ፥የማያስተውለውም፡ልባቸው፡ጨለመ። 22፤ጥበበኛዎች፡ነን፡ሲሉ፡ደንቈሮ፡ኾኑ፥ 23፤የማይጠፋውንም፡የእግዚአብሔር፡ክብር፡በሚጠፋ፡ሰውና፡በወፎች፡አራት፡እግር፡ባላቸውም፡ በሚንቀሳቀሱትም፡መልክ፡መስለው፡ለወጡ። 24፤ስለዚህ፥ርስ፡በርሳቸው፡ሥጋቸውን፡ሊያዋርዱ፥እግዚአብሔር፡በልባቸው፡ፍትወት፡ወደ፡ርኩስነት፡ አሳልፎ፡ሰጣቸው፤ 25፤ይህም፡የእግዚአብሔርን፡እውነት፡በውሸት፡ስለ፡ለወጡ፥በፈጣሪም፡ፈንታ፡የተፈጠረውን፡ስላመለኩና፡ ስላገለገሉ፡ነው፤ርሱም፡ለዘለዓለም፡የተባረከ፡ነው፤አሜን። 26፤ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡ለሚያስነውር፡ምኞት፡አሳልፎ፡ሰጣቸው፤ሴቶቻቸውም፡ለባሕርያቸው፡የሚገባውን፡ ሥራ፡ለባሕርያቸው፡በማይገባው፡ለወጡ፤ 27፤እንዲሁም፡ወንዶች፡ደግሞ፡ለባሕርያቸው፡የሚገባውን፡ሴቶችን፡መገናኘት፡ትተው፥ርስ፡በርሳቸው፡ በፍትወታቸው፡ተቃጠሉ፤ወንዶችም፡በወንዶች፡ነውር፡አድርገው፥በስሕተታቸው፡የሚገባውን፡ብድራት፡ በራሳቸው፡ተቀበሉ። 28፤እግዚአብሔርን፡ለማወቅ፡ባልወደዱት፡መጠን፥እግዚአብሔር፡የማይገባውን፡ያደርጉ፡ዘንድ፡ለማይረባ፡ አእምሮ፡አሳልፎ፡ሰጣቸው፤ 29፤ዐመፃ፡ዅሉ፥ግፍ፥መመኘት፥ክፋት፡ሞላባቸው፤ቅናትን፥ነፍስ፡መግደልን፥ክርክርን፥ተንኰልን፥ክፉ፡ ጠባይን፡ተሞሉ፤የሚያሾከሹኩ፥
ቁጥር ፴ - ፴፪
30፤ሐሜተኛዎች፥አምላክን የሚጠሉ፥የሚያንገላቱ፥ትዕቢተኛዎች፥ ትምክሕተኛዎች፥ክፋትን፡ የሚፈላለጉ፥ለወላጆቻቸው፡የማይታዘዙ፥ 31፤የማያስተውሉ፥ውል፡የሚያፈርሱ፥ፍቅር፡የሌላቸው፥ምሕረት፡ያጡ፡ናቸው፤ 32፤እንደነዚህ፡ለሚያደርጉት፡ሞት፡ይገባቸዋል፡የሚለውን፡የእግዚአብሔርን፡ሕግ፡እያወቁ፡እነዚህን፡ ከሚያደርጉ፡ጋራ፡ይስማማሉ፡እንጂ፡አድራጊዎች፡ብቻ፡አይደሉም።