ክሮኖስ
ክሮኖስ በጥንታዊ ግሪክ አፈ ታሪክ በኩል የአረመኔ እምነት አማልክት ኡራኖስና ጋያ ልጆች የሆኑት የቲታኖች መሪ የነበረ አምላክ ወይም ንጉሥ ነበረ። አባቱን ገልብጦ በአፈታሪካዊ ወርቃማ ዘመን ይነግሥ ነበር፤ በኋላ ግን የራሱ ልጆች ዚውስ፣ ሃይዴስና ፖሠይዶን ክሮኖስን ገለበጡ፣ በታርታሮስም አሠሩት።
የክሮኖስ ስም በሮማይስጥ «ሳቱርን» ሲሆን በነርሱም እምነት እንደ አምላክ ይቆጠር ነበር። የፈልኩ ሳተርን ስም እንዲሁም የቅዳሜ ዕለት ስም (ሳተርደይ) በእንግሊዝኛ ከርሱ የተወሰደ ነው።
የግሪክ ጸሐፊ ሄሲዮድ እንዳለው፣ ክሮኖስ አባቱን ኡራኑስን በመቀኝነት ያየው ነበር፤ እናቱም ጋያ በኡራኑስ ላይ ጠላትነት አገኘች። ስለዚህ ጋያ ክሮኖስን ማጨዳ ሠጠችውና ክሮኖስ አባቱን ሰለበው። ዳሩ ግን ሌሎች ታላላቅ ልጆች («ጊጋንቴስ») ከተፈሰሰው ደም ተወለዱ።
ከዚሁ በኋላ ክሮኖስ ዕኅቱን ሬያን አገባትና ንጉሥና ንግሥት ሆነው ዓለሙን ገዙ። ይህም «ወርቃማ ዘመን» የተባለው ነበር፤ እያንዳንዱ ግለሠብ በምግባር ስለ ሠራ ለድንጋጌዎች አስፈላጊነት ያልነበረበት ወቅት መሆኑ ታመነ።
ክሮኖስና ሬያ ብዙ ሌሎች አማላክት ወለዱ፦ ዴሜቴር፣ ሄራ፣ ሃይዴስ፣ ሄስቲያ እና ፖሠይዶን ነበሩ። ዳሩ ግን ክሮኖስ በገዛው ልጆች እንዲገለበጥ ስለሚል ትንቢት፣ እያንዳንዱ እንደ ተወለደ እርሱ በላቸው። ስለዚህ ስድስተኛው ልጅ ዚውስ ሲወለድ እናቱ በስውር ቦታ በክሬታ ደሴት እንዲታደግ አደረገች። ከታደገ በኋላ ዚውስ መድኃኒት ለክሮኖስ አጠጣውና ወንድሞቹን እንዲያውካቸው አስደረገው። ዚውስ፣ ወንድሞቹና ጊጋንቴስ ከክሮኖስ ኃያላት ጋር ቲታኖማኬ የተባለ አፈታሪካዊ ጦርነት ተዋጉ። ከዚሁ ጦርነት በኋላ ክሮኖስ በታርታሮስ ታሠረ። በፒንዳር ዕትም ግን ክሮኖስ ከዚያ በኋላ ወጣና የኤሊሲዩም ንጉሥ ሆነ። ዊርጊል ደግሞ እንደጻፈው፣ ሳቱርን (ክሮኖስ) ከዚያ ወጥቶ የላቲዩም (በጣልያን) ንጉስ ሆነ።
በጣልያን አፈ ታሪክ ረገድ ደግሞ የክሮኖስ ወይም የስቱርን ስም አንዳንዴ ከ«ካሜሲስ» ወይም ከ«ካሜሴኑስ» ስም ጋር ይለዋወጣል። ለምሳሌ አኒዩስ ዳ ቪቴርቦ ባሳተመው ዜና መዋዕል ውስጥ፣ «ሳቱርን» እንደ ማዕረግ ሲቆጠር፣ መጀመርያውም «የባቢሎን ሳቱርን» ናምሩድ ሲባል፣ የኖኅ ልጅ ካም (ወይም ካሜሴኑስ) «የግብጻውያን ሳቱርን» ሆኖ ከዚያ በሊብያ፣ በጣልያንና በባክትሪያ በተራ ይገዛል፤ ከሃሞን፣ ከቲታኖችና በኋላም ከኒንያስ ጋር ይዋጋል።
በዲዮዶሩስ ሲኩሉስ
ዲዮዶሮስ ሲኩሉስ በመዘገበው የሊብያ አፈ ታሪክ ዘንድ፣ ክሮኖስ ወይም ሳቱርን የኡራኖስና የቲቴያ ልጅ ሲሆን በጣልያን፣ ሲኪልያና ስሜን አፍሪካ ላይ ንጉሥ ነበረ። ለዚህ እንደ ማስረጃ በሲኪሊያ የተገኙ ክሮኒያ የተባሉትን ኮረብታዎች ይጠቅሳል። ክሮኖስና ቲታኖች በወንድሙ በክሬታ ንጉሥ በዩፒተር (ዚውስ) እና በኒሳ ንጉሥ በሃሞን ላይ ጦርነት ያደርጋል፤ ኒሳ በአፍሪካ ውስጥ በትሪቶን ወንዝ የሚገኝ ደሴት ነው። ክሮኖስ ድል አድርጎ እኅቱን ሬያን ሚስቱ እንድትሆን ከሃሞን ይሠርቃታል። ነገር ግን የሃሞን ልጅ ዲዮኒስዮስ (ባኩስ) በፋንታው ክሮኖስን ድል ያደርጋል፤ ከዚያ የክሮኖስና የሬያ ልጅ ዩፒተር ኦሊምፑስ የግብፅ አገረ ገዥ እንዲሆን ባኩስ ያሾመዋል። ባኩስና ዩፖተር ኦሊምፑስ ከዚያ የቀሩትን ቲታኖች በክሬታ ደሴት ያሸንፋቸዋል። ባኩስ ከሞተ በኋላ ዩፕተር ኦሊምፑስ መንግሥታትን ሁሉ ወርሶ የአለም ጌታ ሆነ። (ዲዮዶሩስ መጽሐፍ 3)
በሲቢሊን ራዕዮች
የሲቢሊን ራዕዮች እንደገና ክሮኖስን ይጠቅሳል፤ በተለይ በ3ኛው መጽሐፍ ዘንድ የኡራኖስና ጋያ 3 ልጆች ክሮኖስ፣ ቲታንና ያፔቱስ ይባላሉ። እያንዳንዱ ወንድም የመሬቱን ሢሶ በርስት ይቀበላል፤ ክሮኖስም በሁላቸው ላይ ንጉሥ ይደረጋል። ኡራኖስ ከሞተ በኋላ፣ የቲታን ልጆች የክሮኖስና የሬያ ልጆች እንደተወለዱ ሊያጥፏቸው ይሞክራሉ። ነገር ግን ሬያ በዶዶና ልጆቿን ዚውስን፣ ፖሠይዶንንና ሃይዴስን በሥውር ወለደች፤ በ3 ክሬታዊ ሰዎች ጥብቅና እንዲታድጉ ወደ ፍርግያ ትልካቸዋለች። ይህንን ባወቁ ጊዜ፣ ከቲታን ወገን 60 ሰዎች ክሮኖስንና ሬያን ይሥራሉ፤ ስለዚህ የክሮኖስ ልጆች መጀመርያውን ጦርነት በቲታን ወገን ላይ ይሠራሉ። በዚሁ ታሪክ ክሮኖስ አባቱን ወይም ልጆቹን ስለ መግደሉ ምንም ቃል የለም።
በሳንኩኒያጦን
ጥንታዊ የፊንቄ ታሪክ ጸሐፊ የተባለው ሳንኩኒያጦን እንደጻፈው፣ ክሮኖስ በመጀመርያ ጌባልን የመሠረተ በኋላም እንደ አምላክ የተቆጠረ ከነዓናዊ ገዢ ነበረ። በዚህ ዕትም ሌላ ስሙ «ኤሉስ» ወይም «ኢሉስ» ይባላል፤ በዘመኑ 32ኛው ዓመት አባቱን ኤፒገዩስን ወይም አውቶክጦንን «በኋላም ኡራኖስን ያሉትን» ሰለበው፣ ገደለውና እንደ አምላክ አደረገው። በተጨማሪ፣ መርከቦች ከተፈጠሩ በኋላ፣ ክሮኖስ ሰዎች የሚኖሩበትን ዓለም ሲጎብኝ፣ አቲካን ለሴት ልጁ አጤና አወረሳት፣ ግብጽንም ለሚሶር ልጅ ለጽሑፍ ፈጣሪ ታኡት አወረሰው።[1]
- Eusebius of Caesarea: Praeparatio Evangelica Book 1, Chapter 10.