ክርስትና

ክርስትናኢየሱስ ክርስቶስ (1ኛ ክፍለዘመን ዓ.ም.) ሕይወትና ትምህርት የተመሠረተ እምነት ነው።

የክርስትና መጀመርያ የሚተረክበት አዲስ ኪዳን በተለይም ወንጌልየሐዋርያት ሥራ ነው። የቅሌምንጦስ ስነ ጽሑፍ እንደሚለው ረቢ ኢየሱስ በይሁዳ ክፍላገር ገና ሲያስተምር፣ ደቀ መዝሙሩ ባርናባስሮሜ ከተማ አደባባይ ቆሞ ኢየሱስ መሲኅ መሆኑን አዋጀ፤ ይህ ታሪክ ግን አሁን በምዕራባውያን መምኅሮች ዘንድ አጠያያቂ ሆኗልና በሰፊ አይታወቅም። በሌላ ልማድ ኢየሱስ ለኦስሮኤና ንጉሥ ለ5ኛው አብጋር ደብዳቤ ጻፈ፣ ታዓምራዊ መልክም እንደ ላካቸው ይባላል (የጄኖቫ ቅዱስ መልክን ይዩ።)

በወንጌል መሠረት ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ፣ እንደገና በሕይወት ከመቃብር ተነሥቶ ለደቂቀ መዝሙሮቹ እንደገና ታይቶ ከዚያ ወደ ሰማይ ዓረገ። ከዚህ በኋላ የአይሁድ ጉባኤ ጴጥሮስንና ሌሎችን ሐዋርያት አስገረፋቸው፣ በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ከለከሉዋቸው። ጴጥሮስ ግን፦ «ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል» ብሎ መለሳቸው (የሐዋርያት ሥራ 5:29)።

የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብኢየሩሳሌም የቤተክርስቲያን መጀመርያ መሪ ሆኑ። ከትንሽ በኋላ አይሁድ ያልሆኑ አሕዛብ ምዕመናን እንዲሆኑ ፈቀደ፣ ግርዘት ወይም ሌሎች የሕገ ሙሴ ከባድ ደንቦች አላስገደዳቸውም፣ ነገር ግን ከሕገ ሙሴ «ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከተናቀም (ከመብላት)፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ» አስገደዳቸው (የሐዋርያት ሥራ 15)። ከዚያ በተለይ በቅዱስ ጳውሎስ ስብከት ምክንያት ክርስትና ወንጌልም በቶሎ በሮማ መንግሥት እስከ ሮሜ ከተማ ድረስ ተስፋፋ። በተጨማሪ ልዩ ልዩ ሐዋርያት ወንጌሉን እስከ አክሱም መንግሥትና እስከ ሕንድ ድረስ ቶሎ ወሰዱ።

በ41 ዓም የሮሜ ቄሣር ክላውዴዎስ «አይሁዶችን» ከሮሜ ከተማ ባሳደዳቸው ዘመን፣ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች እንደ ነበሩ ይመስላል። ክርስቲያኖች በሮሜ መንግሥት ብዙ ጊዜ እስከ 303 አም ድረስ ከቄሣሮቹ መከራዎች ቢያገኙም፣ ሃይማኖቱ ግን ምንጊዜም እየተበዛ ነበር።

የአይሁዶች ትምህርት ግን በረቢ አኪቫ በን ዮሴፍ መሪነት በሌላ አቅጣቻ ሄዶ አዋልድ መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን አጠፉና ተልሙድ በተባለ ጽሑፍ አዳዲስ ትምህርቶችን ፈጠሩ። ስለዚህ የሮሜ ንጉሥ ቤስጳስያን የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ62 ዓም ካጠፋ በኋላ፣ አይሁድና እና ክርስትና እንደተለያዩ ሃይማኖቶች ተቆጥረዋል።

በ303 ዓም ክርስትና በሮሜ መንግሥት በጋሌሪዎስ ዘመን ሕጋዊ ሆነ። የሚቀጠለው ቄሳር ቆስጠንጢኖስመጋቢት 10 ቀን 313 ዓ.ም. በአዋጅ እሑድ ለሮማ ዜጎች ሁሉ ስለ ጣኦቱ አፖሎ የእረፍት ቀን እንዲሆንላቸው አዘዘ። በኋላ በ317 ዓም እርሱ የንቅያ ጉባኤ ጠራ፣ በዚህ ጉባኤ በዚያን ጊዜ በዕብራይስጥ የተገኙት ጸሐፍት ብቻ (አዋልድ መጻሕፍት ሳይሆኑ) በብሉይ ኪዳን እንዲቀበሉ ተስማሙ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቆስጠንጢኖስ እራሱ ተጠመቀ። ከዚያስ የሮሜ ቤተ ክርስቲያን የአይሁዶችን «አጭር» ብሉይ ኪዳን የሚያጸድቀው ምንም ቢሆንም፣ እንደ አስርቱ ቃላት ሰንበትቅዳሜ የከበሩት ሁሉ እንደ «አይሁዳውያን» ሀራ ጤቆች በአውሮጳ ይቆጠሩ ጀመር።

በዚህ ዘመን ያህል ብዙ ሌሎች ተወዳዳሪ ትምህርቶች በሮሜ መንግሥት ይሄዱ ነበር፣ በተለይም፦

  • የአሪያን ቤተ ክርስቲያን - በመሪያቸው አሪዩስ ትምህርት ኢየሱስ ወይም ወልድ ከእግዚአብሔር አብ በታች የተለየ አምላክ ነበር እንጂ ሥላሴን አላስተማረም። ይህ እምነት በብዙ ጀርመናውያን ብሔሮች ለጊዜ ይቀበል ነበር።
  • ሞንታኒስም - ነቢያቸው ሞንታኑስ «እኔ ፓራቅሌጦስ (መንፈስ ቅዱስ) ነኝ» ብሎ ሰበከ።
  • ኖስቲሲስም - ወይም ኖስቲኮች - አንዳንድ ሐሣዌ የተቆጠሩት ወንጌሎች ጽፈው ነበር፣ ሌሎች ትምህርቶች በምስጢር ጠበቁ።
  • ማኒኪስም - እንደ ኖስቲሲሲም የመሰለ በምስጢር የተማረ የፋርስ ነቢይ ማኒ ሃይማኖት
  • ሚትራይስም - ሌላ የፋርስ (ዞራስተር) ጣኦት በአረመኔዎች በኩል ዘመናዊ ሆነ፣ እሱ ደግሞ በምስጢር ይማር ነበር።
  • የዱሮ አረመኔነት ወዳጆች - ከ353 እስከ 356 ዓም ድረስ በቄሳሩ ዩሊያኖስ ከሐዲ ሥር ለአጭር ጊዜ ወደ ሥልጣን ተመለሱ፤ ጸረ-ክርስቲያን ትምህርቶች አስገቡ። ሆኖም ከበፊቱ ይልቅ ጨዋዎች ሆነው ነበር።
የለጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለዚህ የንቅያ ጉባኤ የንቅያ ጸሎተ ሃይማኖት ወሰነ። በዚህ ውስጥ ኢየሱስ ወልድ፣ ከአብ ጋራ አንድ ባሕርይ አለው ይላል። በ372 ዓም በተሰሎንቄ ዐዋጅ ቄሣሩ ጤዎዶስዮስ ይህን እምነት በሮሜ ግዛት ውስጥ የመንግሥት ሃይማኖት አደረገው፤ ብዙ የአረመኔ መቅደሶች ተፈረሱ። በሚከተለው ዓመት በ373 ዓም ፩ኛው የቁስጥንጥንያ ጉባኤ የጸሎተ ሃይማኖቱን ይፋዊ ቃላት ትንሽ ቀየሩ፤ በተለይም ስለ መንፈስ ቅዱስ ባሕርይና መለኰታዊነት በይበልጥ የሚገልጹ ቃላት ተጨመሩ።

ከዚያ የተነሣ ወደፊት ቄሣሮች በማንም ሰዓት ጉባኤ በመጥራት ይፋዊ የመንግሥት ሃይማኖት ቀይረው በፍጹም ሊያባልሹት ይቻላል የሚል ጭንቀት ነበር። በተለይ ኢየሱስ «ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ አለው» ቢልም፣ ሆኖም ሁለት ልዩ ልዩ ጸባዮች አሉት የሚሉ አስተማሪዎች ሲቀርቡ፣ ይህ ኢየሱስ በሁለት ልዩ ልዩ ጸባዮች ተለይቷል ማለታቸው ወደፊት ቄሣሮቹ በተንኮላቸው ብዛት የመለኮታዊነቱን ጸባይ በይፋ አስለይተው ወደፊትም አንዱን ጸባይ መካድ ይችላሉና የሃይማኖት ጽሑፉን እንደገና ቀይረው 'ተራ ሰው ብቻ መሆኑ የሮሜ ይፋዊ እምነት ነው' ማለት ይችላሉ የሚል ጭንቀት ተነሣ። የንቅያ (ቁስጥንጥንያ የ373 ዓም) ጸሎተ ሃይማኖት ግን እስካሁን ድረስ ምንም ቃል ሳይቀየር በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ (ካቶሊክተዋሕዶኦርቶዶክስ እና ፕሮቴስታንት) ይደገፋል።

ኢየሱስ አንድ «ተዋሕዶ» ጸባይ (ሰውና አምላክ) ያመነበት ወገን እንዲህ ካልሆነ ፈጣሪ ወደ ፍጥረቱ በፍጹምነት ተዋሕዶ ካልገባ በቀር የሰውን ልጅ አያድንም ነበር ባዮች ነበሩ። ነገር ግን የኢየሱስ «ሁለት ጸባዮች» ትምህርት ወዳጅ ወገን በመጨረሻ በፓፓ ኬልቄዶን ጉባኤ (443 አም) ስለ ተቀበለ፣ የሮሜ ፓፓ ከሌሎቹ ጳጳሳት (የእስክንድርያ፣ የአንጾኪያ ጳጳሳት) ተለያየ። እስካሁንም ድረስ ተዋሕዶ የተባሉት አብያተ ክርስቲያናት መጀመርያ ፫ቱ ጉባኤዎች (ንቅያ፣ ቁስጥንጥንያ፣ ኤፌሶን) ብቻ የሚቀበሉ ናቸው እንጂ የኬልቄዶን ጉባኤ አይቀበሉም።

እስከ 777 ዓም ድረስ በጥምቀት ሥርዓት ወደ ክርስትና የገቡት በጠቅላላ በፈቃደኝነትና በሰላም ነበር። ከነዚህ መካከል ብዙ ሕዝቦች ክርስትናን ተቀበሉ (የክርስትና መስፋፋት ይዩ።) በ777 ዓም ግን የፍራንኮች ንጉሥ ካሮሉስ ማግኑስሳክሶኖች ብሔር (በጀርመን የቀሩትን ሕዝብ) በግድና በዛቻ አስጠመቁዋቸው። ጀርመኖች ደግሞ በበኩላቸው ዞረው የባልቲክ ቋንቋ ተናጋሪ ነገዶችን (በተለይ ላትቪያሊትዌኒያ እና የቀድሞው ፕሩሳውያን) በጨካኝ ጦሮች አስጠመቁዋቸውና እንደ ባርዮች ያህል አደረጉዋቸው። ከነዚዎች ጉዳዮች በስተቀር ግን በክርስትና ታሪክ በአጠቃላይ አብዛኞቹ ብሔሮች የገቡት በሰላምና በፈቃደኝነት ሆኖዋል።

ቋንቋዎች

ኢየሱስ የሰበከው በተለይ በአረማይስጥና በዕብራይስጥ እንደ ነበር ይታመናል። ግሪክኛ ደግሞ በዙሪያው በሰፊ ይነገር ነበርና የአዲስ ኪዳን መጀመርያ የምናውቀው ቅጂ ግሪክኛ ነው። በሉቃስና ዮሐንስ ወንጌላት ዘንድ በመስቀል የተጻፉት ልሳናት ዕብራይስጥ፣ ግሪክኛና ሮማይስጥ ስለ ሆኑ እነዚህም ለዚያው ይከበራሉ። አዲስ ኪዳን በኋላ የተተረጎመባቸው ሌሎች ልሳናት ደግሞ እንደ ክቡራን ቋንቋዎች ተቆጠሩ፤ ግዕዝቅብጥኛአርሜንኛጥንታዊ ስላቭኛ እና ሌሎች በአብያተ ክርስትያናት መደበኛ ሆኑ። በአሁኑ ጊዜ አዲስ ኪዳን ወይም ቢያንስ ወንጌል በብዙ ሺህ የሰው ልጅ ቋንቋዎች ተተርጎመዋል።

:
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.