ኩግባው
ኩግባው በሱመራዊ ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ ኪሽ በሱመር ላዕላይነቱን በያዘበት ጊዜ የኪሽ ንግሥት ነበረች። በነገስታት ዝርዝሩ ሁሉ፣ ከርሷ ብቻ በቀር ሌላ ንግሥት አትጠቀስም።
ዝርዝሩ «የኪሽ መሠረቶችን ያጸናችው ባለ ቡናቤትዮዋ» ሲላት ለመቶ ዓመታት ሱመርን እንደ ገዛች ይለናል። ይህ ቁጥር ግን ታማኝ አይሆንም። በአንዳንዱ ቅጂ ቀደም-ተከተል አክሻክ ከተሸነፈ በኋላ የሱመር ላዕላይነት ወደርሷ ተዛወረ፣ ከእርሷም ቀጥሎ ልጇ ፑዙር-ሲን ተከተላት። በሌላ ቅጂ ግን ይህ ትንሽ እንደ ተዛባ መስሏል፣ ከማሪ ንጉሥ ሻሩም-ኢተር ቀጥላ እና ከአክሻክ ላዕላይነት አስቀድማ ያደርጓታል።
ሌላ የሚጠቅሳት ሰነድ የባቢሎን መቅደስ ዜና መዋዕል (ወይም «የቫይድነር ዜና መዋዕል» [1]) የተባለው ጽላት ነው። ዜና መዋዕሉም «ኩባባ» ሲላት እንዲህ ይተርካል፦
( <...> ጽሕፈቱ የጠፋበት ሕዋእ ለማመልከት ነው። ጽላቱ እራሱ ቅጂ ሆኖ «[ጠፍቷል]» የሚለው ማመልከቻ ቃል በጽላቱ ላይ ይታያል።)
- በአክሻክ ንጉሥ ፑዙር-ኒራሕ ዘመን፣ የመቅደሱ አሣ አጥማጆች ለጣኦቱ ለማርዶክ መሥዊያ አሣን እያጠመዱ ነበር። የንጉሡ መኳንንት ዐሣዎቹን ይቃሙ ነበር። <...> ሣምንቱም ካለፈ በኋላ ዐሣ አጥማጆቹ አሣን እያጠመዱ ነበር። <...> ባለ ቡናቤት ወደ ሆነችው ወደ ኩባባ (ኩግባው) መኖርያ አመጡት። <...> ለመቅደሱም ቅርብ ሆነው ወደዚያ አመጡት። ያንጊዜ [ጠፍቷል] እንደገና ለመቅደሱ <...> ኩባባ ለአሣ አጥማጆቹ ዳቦ ሰጠች፣ ውሃም ሰጠች፣ <...> ዐሣውንም ለመቅደሱ ቶሎ አቀረበ። ጣኦቱ ማርዶክ ደስ ብሎት 'ይሁን' አለ። ለባለ ቡናቤትዮዋ፣ ለኩባባ፣ የዓለሙን ሁሉ ገዥነት ሰጣት።
ከዚህ እንደሚታይ፣ የአክሻክ ንጉሥ ፑዙር-ኒራሕ የአሣ መሥዊያን ለመከልከል እንዳሰበ፣ የአጥማጆቹ ወገን ግን በኩግባው እርዳታ እንደ ተቋቋሙት፣ በኒፑርም የተገኙት የቄሳውንት ወገን ድጋፋቸውን ከፑዙር-ኒራሕ አዛውረው ሽረውት የተወደደችውን የኪሽ ባለ ቡናቤት (ባለ ጠጅቤት) ኩግባውን የመላ ሱመር ንግሥት ሆና እንዳሾሙአት መገመት እንችላለን።
በነገሥታት ዝርዝሩ ዘንድ ከኩግባው በኋላ በኪሽ የገዙት 7 ወይም 8 የሱመር ነገሥታት ይዘረዝራሉ። ከነዚህ አንዱ ብቻ የኩግባው ልጅ ልጅና የፑዙር-ሲን ልጅ ኡር-ዛባባ ከሌላ ሰነድ ታውቋል። ሌሎቹ ሁሉ ምንም ቅርስ ስላላስቀሩልን፣ በሱመር እንደ ገዙ አጠራጣሪ ነው። በዚህ ዘመን ሁሉ (ከኩግባው በፊትና እስከ ታላቁ ሳርጎን ድረስ) ሉጋል-ዛገ-ሢ የኡሩክ ንጉሥ መሆኑ ይታወቃል፣ ስለዚህ የኪሽ ላዕላይነት በሙሉ ለበጣም ረጅም ዘመን አልነበረም።
በኋለኖቹ ዘመናት በአረመኔዎች በኩል «ኩባባ» እንደ ሴት አምላክ ተቆጠረች። እርሷን ለማስታወስ የተሠሩት መቅደሶች በሱመር ብቻ ሳይሆን አምልኮቷ ወደ ስሜን መስጴጦምያ እና ወደ ኬጥያውያን መንግሥት ተስፋፋ። በተለይ በከርከሚሽ የከተማቸው ጣኦት አደረጓት። ለብዙ ምዕተ ዓመታት እስከ ግሪኮችም ዘመን ድረስ በፍርግያውያን እምነት «ኩቤቤ» ወይም «ኩቤሌ» በተባለች ሴት ጣኦት እንዳመኑባት ታውቋል።
ቀዳሚው የአክሻክ ንጉሥ ፑዙር-ኒራሕ |
የሱመር (ኒፑር) አለቃ 2097-2091 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ ኡር-ዛባባ |
- "ABC19". Archived from the original on 2006-02-28. በ2013-06-13 የተወሰደ.