አጠቃላይ አንጻራዊነት
አጠቃላይ አንጻራዊነት በ፲፱፻፲፭ ዓ.ም በአልበርት አንስታይን የታተመ አጠቃላይ የቁስ ግስበትን በጂዖሜትሪ የገለጸ መጽሃፍና ርዕዮት አለም ነው። በርግጥም በአሁኑ ዘመን የሚሰራበት ግስበትን ገላጭ የዘመናዊ ተፈጥሮ ህግጋት ጥናት አካል ነው። አጠቃላይ አንጻራዊነት የኒውተንን የግስበት ህግንና ልዩ አንጻራዊነትን በማዋሃድ የግስበትን አጠቃላይ ባህርይ በኅዋና ጊዜ ጥምር ጂዖሜትሪ የሚገልጽ ነው። በዚህ አዲስ የተፈጥሮ ህግጋት ጥናት መሰረት አንድ ቁስ በሚኖርበት ኅዋ አካባቢ የኅዋና ጊዜ ጥምር ጂዖሜትሪ ስለሚታጠፍ የቁስ ግስበት መሰረቱ ከዚህ እጥፋት ይነሳል ይላል።
ብዙው የአጠቃላይ አንጻራዊነት ትንቢቶች ከድሮው ፊዚክስ ትንቢቶች ይለያያል፣ በተለይ የጊዜን ፍሰት በተመለከተ፣ የኅዋን ጂዖሜትሪ በተመለከተ፣ የነገሮችን ወደ መሬት መውደቅ በተመልከተ፣ እንዲሁም የብርሃንን ጉዞ በተመለከተ። ለምሳሌ ብንወስድ፣ በአዲሱ ርዕዮተ አለም መሰረት ግስበታቸው ሃይለኛ በሆኑ ኮኮብ አካባቢ ጊዜ ዝግ ብሎ ይፈሳል፣ ብርሃንም በኒህ አካባቢ ሲያልፍ ቀለሙ ወደ ቀይ ይጠጋል። እኒህና ብዙ የአጠቃላይ አንጻራዊነት ትንቢቶች በተሞክሮ ተረጋግጠዋል።
የአይንስታይን ርዕዮት ብዙ መዘዞች አሉት። ከነዚህ ውስጥ ጥቁር ቀዳዳ የሚባሉት ይገኙበታል። ጥቁር ቀዳዳወች እንግዲህ በውኑ አለም ኅዋ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ ከከፍተና ግስበት የተነሳ በአካባቢው የሚገኘው ጊዜና ኅዋ በከፍተኛ ሁናቴ ከመናወጡ የተነሳ ምንም ነገር፣ ብርሃንም ሳይቀር፣ ከዚህ ነውጥ ማምለጥ ሲያቅተው፣ ያን ጊዜ ጥቁር ቀዳዳ ይፈጠራል። በተለይ ይህ የሚሆነው እጅግ ግዙፍ የሆኑ ከዋክብት ሙቀታቸው ጠፍቶ በራሳቸው ግስበት ተጨምቀው ሲሞቱ ነው። ሌላው መዘዝ ደግሞ እንዲህ ነው። በዚህ ርዕዮት መሰረት፣ ግስበት ያላቸው ቁሶች ኅዋንና ሰዓትን ስለሚያጥፉ በነሱ የሚያልፍ ማንም ነገር፣ ብርሃንን ጨምሮ፣ መታጠፍ ይኖርበታል። ስለሆነም ብርሃን በግዙፍ የሰማይ አካላት ሲያልፍ ስለሚታጠፍ ይህ ሁኔታ ግስበታዊ ሌንስ ይፈጥራል። ስለሆነም ብርሃኑ የሚመነጭበት አንዱ ቁስ በብርሃን መተጣጠፍ ምክንያት ምድር ላይ ሆኖ ሲታይ ሁለትና ከዚያ በላይ ሆኖ ይታያል። በሌላ በኩል አጠቃላይ አንጻራዊነት የግስበት ማዕበል መኖርን የሚተነብይ ሲሆን እኒህ ማዕበሎች በተዘዋዋሪ ተለክተዋል። ናሳና ሊጎ በአሁኑ ወቅት እኒህን ማዕበሎች ቀጥታ ለመለካት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ በዜና አውታሮች ይገለጻል። ከዚህ በተረፈ በአሁኑ ዘመን የሚታመንበት የአጠቃላይ ኅዋ እየሰፋ መሄድ መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብ የሚፈልቀው ከዚሁ ከአንስታይን ጥናት ነው።