አይቲዮፒያ (የግሪክ ቃል)
አይቲዮፒያ (ግሪክ፦ Αιθιοπία፣ ሮማይስጥ፦ Aethiopia) የሚለው ቃል መጀመርያ በጥንታዊ ምንጮች የመልክዓ ምድር ስያሜ ሆኖ ሲታይ፣ የላየኛ አባይ ወንዝ አውራጃ እንዲሁም ከሳህራ በረሃ በስተደቡብ ላለው አገር በሙሉ ያመለከት ነበር። ይህ ስም በግሪክ በሆሜር ጽሁፎች በኢልያዳና ኦዲሲ (ምናልባት 850 ዓክልበ.) ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል። በተለይ ከግሪክ ታሪክ ምሁር ሄሮዶቱስ (440 ዓክልበ. ግድም) ጀምሮ «አይቲዮፒያ» ሲጻፍ ትርጉሙ ከግብጽ ወደ ደቡብ ለተገኘው የአፍሪካ ክፍል ሁሉ እንደ ሆነ ግልጽ ነው።
ከሄሮዶቱስ በፊት
ከሁሉ አስቀድሞ የግሪክ ባለቅኔው ሆሜር ስለ አይቲዮፒያ ሲጠቅስ፣ በዓለም ደቡብ ጫፎች የሚገኝ ብሔር ሲሆን በባሕር ተለይተው በምዕራብ (አፍሪካ) እና በምሥራቅ (እስያ) እንደሚካፈሉ ይዘግባል። የግሪክ አፈ ታሪክ ጸሐፊዎች ሄሲዮድ (700 ዓክልበ. ግድም) እና ፒንዳር (450 ዓክልበ. ግድም) ስለ አይቲዮፒያ ንጉሥ መምኖን ይተርካሉ፤ በተጨማሪ የሱሳን (በኤላም) መሥራች ይባላል።
በ515 ዓክልበ. ስኪላክስ ዘካርያንዳ የሚባል ግሪክ መርከበኛ በፋርስ ንጉሥ ዳርዮስ ትዕዛዝ በሕንዱስ ወንዝ፣ በሕንድ ውቅያኖስና በቀይ ባሕር በመጓዝ የአረብ ልሳነ ምድርን በሙሉ ዞረ። ኢትዮጵያውያን የሚለው ስም ይጠቅመው ነበር፤ ስለ አይቲዮፒያ የጻፈው ጽሑፍ ግን አሁን ጠፍቷል። ሄካታዮስ ዘሚሌቶስ (500 ዓ.ዓ.) ደግሞ ስለ አይቲዮፒያ አንድ መጽሐፍ እንደ ጻፈ ይነገራል፤ አሁን ግን ጽሁፉ በአንዳንድ ጥቅሶች ብቻ ይታወቃል። አይቲዮፒያ ከአባይ ወንዝ ወደ ምሥራቅ እስከ ቀይ ባሕርና እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ ነው ሲል በዚያ «ጥላ እግሮች» የሚባል ጎሣ እንዳለበት፣ እግራቸውም እንደ ጥላ እስከሚጠቅማቸው ድረስ ሰፊ እግር እንዳላቸው አፈ ታሪክ ያወራል። በዚያ ዘመን የኖረውም ፈላስፋ ክሴኖፋኔስ፦ «የጥራክያውያን አማልክት እንደነሱ ወርቃማ ጽጉርና ሰማያዊ አይን ናቸው፤ የኢትዮጵያውያን አማልክት እንደነሱ ጥቁሮች ናቸው» ሲል አይቲዮፒያ የጥቁር ሕዝቦች አገር መሆኑን ያረጋግጣል።
በሄሮዶቶስ
«ሂስቶሪያይ» (ታሪኮች) በሚባል ጽሑፍ ሄሮዶቶስ ስለ «አይቲዮፒያ» ጥንታዊ መረጃ ይዘርዝራል። ሄሮዶቶስ እራሱ እስከ ግብጽ ጠረፍ እስከ ኤሌፋንቲን ደሴት (የአሁኑ አስዋን) ድረስ በአባይ መንገድ ወጥቶ እንደ ተጓዘ ያወራል። በአስተያየቱ፣ «አይቲዮፒያ» ማለት ከኤለፋንቲን ጀምሮ ከግብጽ ወደ ደቡብ የሚገኘው አገር ሁሉ ነው። አንድ ዋና ከተማ በሜሮዌ አላቸው፤ እዚያ አማልክታቸው ዜውስ እና ዲዮናስዮስ ብቻ ናቸው ይላል። በፈርዖን 1 ፕሳምቲክ ዘመን (650 ዓ.ዓ.) ብዙ የግብጽ ወታደሮች አገራቸውን ከደው በኢትዮጵያውያን መካከል እንደ ሰፈሩ ይዘግባል። ከግብጽ 330 ፈርዖኖች፣ 18ቱ ኢትዮጵያውያን (ማለት የኩሽ ፈርዖኖች ወይም የግብጽ 25ኛው ሥርወ መንግሥት) እንደነበሩም ጽፏል። ግዝረት ከሚፈጽሙት አገሮች አንድ መሆናቸውን ይመስክራል።
የፋርስ ንጉሥ ካምቢስስ (570 ዓክልበ. ገደማ) ሰላዮችን «በደቡባዊው ባሕር ላይ በሚካለለው በሊብያ (የአፍሪቃ አህጉር) ክፍል ወደሚኖሩት» ኢትዮጵያውያን እንደ ላከ ሄሮዶቶስ ይነግረናል። ጠንካራና ጤነኛ ሕዝብ አገኙ። ካምቢስስ ከዚያ ወደ አይቲዮፒያ ቢዘምትም በቂ ስንቅ ባለማዘጋጀታቸው ለሥራዊቱ በፍጹም አልተከናወነምና በቶሎ ተመለሱ።
በሦስተኛው መጽሐፍ፣ ሄሮዶቱስ የ«አይቲዮፒያ» ትርጉም ከሁሉ የራቀው «ሊብያ» (አፍሪካ) እንደ ሆነ ያስረዳል። «ደቡቡ ወደሚገባው ፀሓይ በሚወርድበት ቦታ አይቲዮፒያ የተባለው አገር ይቀመጣል፤ ይህም በዚያ አቅጣጫ መጨረሻው ንዋሪዎች የሚገኙበት አገር ነው። በዚያ ወርቅ በታላቅ ብዛት ይገኛል፣ ታላቅ ዝሆኖች ይበዛሉ፣ የዱር እፅዋትም በየአይነቱም፣ ዞጲም፤ ሰዎቹም ከሌላ ሥፍራ ሁሉ ይልቅ ረጃጅም፣ ቆንጆና እድሜ ያላቸው ናቸው።»
ሌሎች ጸሐፍት
የግብጽ ቄስና ታሪክ ምሁር ማኔቶን (300 ዓክልበ. ግድም) ስለ ግብጽ ኩሻዊ ሥርወ ወንግሥት ሲዝረዝር፣ «የአይቲዮፒያ ሥርወ መንግሥት» ብሎ ሰየመው። እንደገና የእብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳን) ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጎምም (200 ዓክልበ. ያህል) በእብራይስጡ «ኩሽ / ኩሻውያን» የሚለው አጠራር በግሪኩ «አይቲዮፒያ» ሆነ።
የኋላ ዘመን ግሪክና ሮማ ታሪክ ሊቃውንት እንደ ዲዮዶርና ስትራቦን የሄሮዶቶስ ወሬ በማረጋገጥ በሰፊው «አይቲዮፒያ» ውስጥ አያሌው ልዩ ልዩ ብሔሮች እንዳሉ ጽፈዋል። ከነዚህ ብሔሮች መካከል «ዋሻ ኗሪዎች» (Troglodytae /ትሮግሎዲታይ/) እና «አሣ በሎች» (Ichthyophagi /ኢቅጢዮፋጊ/) በአፍሪካ ቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ (በዘመናዊው ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲና ሶማሊላንድ)፣ እና ከዚያ ወደ ምዕራብ የሚኖሩ ብዙ ሌሎች ሕዝቦች እንዳሉ ገለጹ። እነዚህ ጸሐፍት ደግሞ የአባይ ምንጮች የሚነሡበት የአይቲዮፒያ ተራራማ ክፍልን የሚገልጽ አፈታሪክ ጨመሩ። ስትራቦን እንደሚለው (i.2) አንዳንድ ሊቃውንት የአይቲዮፒያ ግዛት ከደብረ አማና ጀመሮ ወደ ደቡብ (ከነሶርያ፣ እስራኤልና ዓረብ ሁሉ) ይቆጥሩ ነበር
አንዳንድ የኢትዮጵያ ጸሐፊ «ኢቅጢዮፋጊ» የሚለው ግሪክ ስም የ«ኢትዮጵያ» ደባል ሆኖ የስያሜው ጥንታዊነትና ኗሪነት ምስክር ነው የሚል አሣብ አቅርበዋል። በዚህ አሣብ ስሙ «ዕንቁ» «ቶጳዝዮን» ከሚሉ ቃላት ጋር ዝምድና እንዳለው ባዮች ናቸው። (መጽሐፈ ኢዮብ ደግሞ «የኢትዮጵያ (የኩሽ) ቶጳዝዮን» ይጠቅሳል።
ፕሊኒ ዘ ኤልደር አዱሊስን ገለጸ፣ ይህም ወደብ የኢትዮጵያውያን ዋና ገበያ እንደ ነበር ይተርካል። ከዚህ በላይ «አይቲዮፒያ» የሚለው ቃል መነሻ «አይቲዮፕስ» ከትባለው ግለሠብ እንደ ነበር አስረዳ፤ እርሱም የሃይፌስቱስ (ወይም ቩልካን) ወንድ ልጅ ነው።[1] (በግሪኮች ዘንድ ግን «የሃይፌስቱስ ልጅ» ቀጥቃጭ ማለት ሊሆን ይችል ነበር።) ይህ ታሪክ በአብዛኛው ሊቃውንት እስከ 1600 ዓ.ም. ግድም ድረስ የታመነ ነበር።
በ400 ዓ.ም. ግድም ማውሩስ ሴርቪኡስ ሆኖራቱስ የሚባል ሊቅ በሮማይስጥ ጽፎ ከዚህ በተለየ ሃልዮ አቀረበ። በዚህ ዘንድ፣ የአይቲዮፕስ / አይቲዮፒያ ስም ከግሪኩ ግሦች «አይተይን» (መቃጠል) እና «ኦፕተይን» (መጥበስ) መጣ። ከዚያ በኋላ ከግሪኩ ቃላት «አይቶ» (አቃጥላለሁ) እና «ኦፕስ» (ፊት) እንደ መጣ የሚለው ሀሣብ መጀመርያ የተገለጸው በ850 ዓ.ም. ግ. በወጣ ግሪክኛ መዝገበ ቃላት Etymologicum Genuinum ይመስላል። «የፊት ማቃጠል» የሚለው አስተሳሰብ እንደገና ፍራንሲስኮ ኮሊን (1584-1652 ዓ.ም.) በተባለ የእስፓንያ ቄስ በመጽሐፉ ኢንዲያ ሳክራ (India Sacra «ቅዱስ ሕንድ») ስለ ኢትዮጵያ ረጅም ምዕራፍ (በሮማይስጥ) አለበት።[2] በጀርመን ጸሐፍት ክሪስቶፈር ቮን ቫልደንፈልስ (1669 ዓ.ም.) እና ዮሐንስ ሚኔሊዩስ (1675 ዓ.ም.) ይጠቀስ ነበር። ከዚያም በአብዛኛው የአውሮፓ ሊቃውንት ተቀባይነትን ቶሎ አገኘ።
አይቲዮፒያ በእስያ
በግሪክ አፈታሪክ፣ ብዙ ጊዘ በእስያ የተገኘ «አይቲዮፒያ» የሚባል መንግሥት ይጠቀሳል። ይህ መንግሥት በአንድሮሜዳ ትውፊት በፊንቄ ኢዮጴ (አሁን በተል አቪቭ እስራኤል) ይቀመጣል። ስቴፋኖስ ዘቢዛንትዩም (500 ዓ.ም. ግድም) እንዳለው፣ «ኢዮጴ» የሚለው ስም የአይቲዮፒያ ማሳጠሪያ ነው፤ በጥንት ግዛቱም ወደ ምሥራቅ እስከ ባቢሎኒያ ድረስ እንደ ተስፋፋ ይዘግባል።
አንዳንዴም በልድያ ወይም በትንሹ እስያ፣ በዛግሮስ ተራሮች ወይም በሕንድ «አይቲዮፒያ» ስለሚባል መንግሥት ይጠቀሳል።
ደግሞ ይዩ
ዋቢ ምንጭ
- Nat. Hist. 6.184–187
- (ሮማይስጥ) India Sacra: hoc est suppetiae sacrae, ex vtraque India in Europam, pro ... by Francisco Colin, p.5.