አንሻን
አንሻን (ፋርስኛ: انشان ፣ ዘመናዊ ታል-ኢ ማልያን ኢራን) በዛግሮስ ተራሮች የተገኘ (29.9° N 52.4° E) ጥንታዊ የኤላም ዋና ከተማ ነበረ።
በ1965 ዓ.ም. ከሥነ ቅርስ ምርመራዎች የተነሣ ሥፍራው ታል-ኢ ማልያን መሆኑ ታወቀ[1]። ከዚያው አመት አስቀድሞ ቦታው ከዚያ ወደ ምዕራብ በመካከለኛ ዛግሮስ ሰንሰለት እንደ ነበር ይገመት ነበር[2]።
ይህ ኤላማዊ ከተማ እጅግ ጥንታዊ መሆኑ አይጠራጠርም፤ በጥንታዊው ሱመርኛ አፈ ታሪክ ኤንመርካርና የአራታ ንጉሥ መሠረት ከኡሩክ ወደ አራታ በሚወስድ መንገድ ላይ ይገኝ ነበር፤ ይህም መጻፍ የተለማበት ዘመን ያሕል እንደ ነበር ይባላል። በአንዳንድ ዘመን አንሻን ከሌሎች ትልልቅ የኤላም ከተሞች ጋራ ሲወዳደር የብዙ ኤላማዊ ስርወ መንግሥታት ምንጭ ሆነ።
የአካድ ንጉሥ ማኒሽቱሹ አንሻንን እንዳሸነፈ ብሎ አስመዘገበ። በተከታዮቹ ሥር ግን የአካድ መንግስት በደከመበት ወራት (2013 ዓክልበ.)፣ የሱሳ ኗሪው አገረ ገዥ ኩቲክ-ኢንሹሺናክ እሱም የአዋን ሥርወ መንግሥት ተወላጅ ነጻነቱን ከአካድ አዋጀና አንሻንን ማረከ። (አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ 'አዋን'ና 'አንሻን' አንድ ቦታ እንደ ነበር የሚል ግምት አቅርቧል።) ከዚህ ቀጥሎ የላጋሽ ንጉሥ ጉዴኣ አንሻንን እንዳሸነፈ የሚል መዝገብ ቀረጸ። የኋለኛ ኡር ነገሥታት ሹልጊና ሹ-ሲን ደግሞ በአንሻን ላይ የራሳቸው አገረ ገዦች እንደነበሯቸው በጽላት ላይ ተጽፎ ይገኛል። ሆኖም የነሱ ተከታይ ኢቢ-ሲን በዘመኑ በሙሉ አመጽ በአንሻን ለመስበር ይታገል ነበር፤ በመጨረሻም ኤላማውያን በ1879 ዓክልበ. ገዳማ ዑርን በዝብዘው የናና ጣኦትና ኢቢ-ሲንም እራሱ እስከ አንሻን ድረስ ተማረኩ[3]።
ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ. ጀምሮ የኤላም ነገሥታት በሱሳ «የአንሻንና የሱሳ ንጉሥ» የሚል ማዕረግ ይጠቅማቸው ነበር። በአካድኛ መዝገቦች ግን እነዚህ ስሞች ተገልብጠው «የሱሳና የአንሻን ንጉሥ» ተብሎ ይጻፋል[4]። በመካከለኛ ኤላማዊ ዘመን አንሻንና ሱሳ በአንድ ግዛት እንደ ተወሐዱ ይመስላል። ይህም ስያሜ የወሰደው መጨረሻው ኤላማዊ ንጉሥ 2ኛ ሹትሩክ-ናሑንተ (700 ዓክልበ. ያሕል የነገሠ) ነበረ[5]።
የአሐይመኒድ ፋርስ እምብርት
በ650 ዓክልበ. ገደማ አንሻን በፋርስ ነገድ አለቃ ተይስፐስ ተይዞ ከዚያ እሱ «የአንዛን ንጉሥ» ተባለ። በሚከተለው መቶ አመት የኤልማውያን መንግሥት ሲደከም፣ አንሻን ጥቃቅን አገር ነበር፤ ከ550 ዓክልበ. ገደማ የፋርሳውያን አሐይመኒድ ሥርወ መንግሥት ከአንሻን ተነሥቶ የፋርስ መንግሥት ያስፋፉ ጀመር።
የግርጌ ነጥቦች
- Reiner, Erica (1973 እ.ኤ.አ.) «The Location of Anšan», Revue d'Assyriologie 67, pp. 57-62፤ Majidzadeh (1976)፣ Hansman (1985)
- Gordon (1967) p. 72 note 9፤ Mallowan (1969) p. 256፣ (1985) p. 401, note 1
- Cambridge History of Iran p. 26-27
- Birth of the Persian Empire
- Cambridge History of Iran
ዋቢ መጻሕፍት
- Excavations at Anshan (Tal-E Malyan): The Middle Elamite Period ከElizabeth Carter፣ Ken Deaver 1996 እ.ኤ.አ.
- The Archaeology of Elam: Formation and Transformation of an Ancient Iranian State ከD. T. Potts, 1999 እ.ኤ.አ.