አነር
አነር በሳይንሳዊ ስሙ Leptailurus serval የሚባል መካከለኛ ክብደት ያለው የድመት አስተኔ ዝርያ ነው። አነር ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ይገኛል።
?አነር | ||||||||||||||||
---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|---|
ሳይንሳዊ ደረጃ መስጫ | ||||||||||||||||
| ||||||||||||||||
Leptailurus serval (Schreber, 1776 እ.ኤ.አ.) | ||||||||||||||||
አነር የሚገኝባቸው አካባቢዎች | ||||||||||||||||
አነር፣ አነስተኛ ከሆኑት የድመት አስተኔ አባሎች ሁሉ እግሩ የረዘመ፣ አንጻራዊ ከፍታ ያለው ነው። የሚገኘው በአፍሪቃ ብቻ ነው። ክብደቱ 13 ኪ.ግ. ገደማ ሲሆን፣ የሴቷ ደግሞ 11 ኪ.ግ. ገደማ ነው። ቀጠን ብሎ አንገቱ ረዘም ያለ፣ ጭራው መካከለኛ ርዝመት ያለው ነው። አንገቱ፣ ትከሻው፣ እግሮቹና ጭራው ጥቋቋር መስመሮች አላቸው። ትላልቅ ጥቁር ነጠብጣቦች በእግሮቹና በጎኑ አሉት። ከጥቋቁሮቹ መስመሮችም ሆነ ነጠብጣቦች በስተቀር፣ ቀለሙ ወደ ቢጫ ያደላ ቡኒ ነው። ይህ እንደ የሥፍራው ልዩነት ሊያሳይ ይችላል። ከበረሃዎችና ከአፍሪቃ የዝናብ ደኖች በስተቀር የትም ይገኛል። አነር፣ አይጥና አይጠ መጎጥ የመሳሰሉት እንስሳት፣ እንዲሁም በረጃጅም ሣር ውስጥ የሚኖሩትን አዕዋፍ በማደን ጥበቡ የታወቀ ነው። ጆሮዎቹ የሚሠሩት ልክ እንደ ዲሽ አንቴና በመሆኑ፣ እነዚህ ምግቦቹ የሚኖራቸውን ድምፅ አግኝቶ፣ የት እንዳሉ ያመለክታል። ጉድጓድ ውስጥ ሆነው እንኳን ድምፃቸውን መጥለፍ ይችላል። የረጃጅም እግሮቹ አሠራር ለፍጥነት ሳይሆን፣ ከፍ ብሎ በሣር ውስጥ ለማየትና፣ የሚያድነውን ለመያዝ ለሚያደርገው የእመርታ ዝላይ ነው። የሣር አይጦች ዋነኞቹ ምግቦቹ ናቸው። ከዚህ በተረፈ ሻሎ፣ እባቦች፣ እንሽላሊቶች እንቁራሪቶች፣ ሦስት አፅቄዎችና አነስተኛ ግልገሎችና ጥጃዎች ይበላሉ።
አነሮች፣ ብቸኛና ክልልተኛ ናቸው። ተመሳሳይም ሆነ ተቃራኒ ጾታ ያላቸው አነሮች ተደራራቢ ክልል ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም፣ ብዙ ጊዜ ግንኑነት እንዳይኖራቸው ይሆናል። በየጊዜው ክልላቸውን ይለዋውጣሉ። ብዙ ጊዜ እጅግም ርቀው አይሄዱም። ምግባቸውን ከገደሉ በኋላ እዛው ላይ ወይም ደበቅ ወዳለ ቦታ ወስደው ይበላሉ። የተዋጣላቸው አዳኞች ናቸው። ከሚያልሟቸው ግድያዎች፣ ከቀኖቹ 40% ከሌሊቱ ደግሞ 59% ይሳካላቸዋል።
ከ65 እሰከ 75 ቀናት አርግዘው ሁለት ወይም ሦስት ግልገሎች ይወልዳሉ። በየሁለት ዓመት ተኩል ሊወልዱ ይችላሉ። በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ወንዱና ሴቷ ለጥቂት ቀናት እያደኑና እያረፉ አብረው ሊቆዩ ይችላሉ። ከዚያም ይለያያሉ። ሴቶቹ፣ ግልገሎቹን ወተት እያጠቡ ያሳድጋሉ። ወንዶቹ ብቻቸውን ማደን ሲችሉ፣ እናታቸው ታባርራቸዋለች። ሴቶቹ ግን ረዘም ላለ ጊዜ ከእናታቸው ጋር አብረው ይቆያሉ።
ምንጭ
- ዶ/ር ሰሎሞን ይርጋ «አጥቢዎች» (2000)
- (እንግሊዝኛ) Breitenmoser, C., Henschel, P. & Sogbohossou, E. (2008). Leptailurus serval. In: IUCN 2008. IUCN Red List of Threatened Species. Downloaded on 22 March 2009. Database entry includes justification for why this species is of least concern