አቡነ ሰላማ
አቡነ ሰላማ በአጼ ቴወድሮስ ዘመን የነበሩ ፓትሪያርክ ናቸው። የአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አጭር ታሪክ
“ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጒድጓድ ተቅበዘበዙ።” ዕብ. 11፥38። በእርግጥ ዓለም ለእገሌ ይገባል ለእገሌ አይገባም የምትባል አይደለችም። ቅዱሳን መናንያን ግን በራሳቸው ፈቃደ ዓለምን አንፈልግሽም ስላሏት ዓለም አልተገባቸውም ተባሉ። እንደ ማንኛውም ሰው በዓለም መኖር ሲችሉ ዓለምን ንቀው መኖሪያቸውን በተራራና በዋሻ አደረጉ። ያላቸውን ንቀው እንደ ሌላቸው በመሆን ስለ ሰማያዊ ፍቅር መከራን ተቀበሉ። “ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ” ዕብ. 11፥37 ወዳጄ ሆይ! ለመሆኑ ቅዱሳን አባቶቻችን የሞቀ ቤታቸውን ጥለው በዱር በጫካ ከአራዊት ጋራ መኖርን መምረጣቸው እንደ ሞኝነት ይቆጠር ይሆን? ወይስ እውቀት ያነሳቸው ይመስልሃል? አይደለም። በሳይንሱ ዓለም ትምህርት ተምረው ዲፕሎም፣ ዲግሪ፣ ማስትሬት የጨረሱ ዶክትሬትም ጨብጠው ወደ ገዳም የገቡ ብዙዎች ናቸው። እነዚህ ቅዱሳን በዓለም ላይ ሳሉ ብዙ ነገር ቢኖራቸውም እንኳን የሚበልጠውን ሰማያዊ ፍቅር ፈልገው ሁሉንም ትተው ወደ ምናኔ ገቡ። “እውነት እላችኋለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።” ማቴ. 19፥28። ወዳጄ ሆይ! የቅዱሳን ገዳማውያን ገድል የሕይወታቸው ኑሮ ለሁሉም መልካም ምሳሌና አርአያ ሊሆን ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ እምነታችን ለማጠንከርም ይረዳናል። ምክንያቱም ጠንካራ እምነት ማምጣት የምንችለው የእምነት ጀግኖች አባቶቻችንን የሰሩትን አብነት በማድረግ ነው። አዎ! የቅዱሳንን ሕይወት ማጥናት ለእኛም ከይስሙላ ወይም ከታይታ ኑሮ ወጥተን በትክክል የተቀየረ ሕይወት እንዲኖረን ያግዘናል። ስለሆነም ቅዱሳን በየዕለቱ ሥራቸውን እንድናስታውስና ሕይወታቸው የመንፈስ ምግብ ማድረግ ይገባናል። እንግዲህ ወዳጄ የቅዱሳን ገዳማውያን በረከታቸው ለማግኘትና ከሕይወታቸው ተምረን ብርሃን የሆነውን መንገዳቸውን እንድንከተል ወደ ታሪካቸው እንሻገር። “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው።” ምሳ. 4፥18 ወዳጄ ሆይ! ˝ባሕርን በጭልፋ˝ እንደሚባለው በዚህች ብጣሽ ወረቀት የሁሉንም ቅዱሳን መናንያን ታሪክ መዘርዘር ባይቻልም ከቅዱሳን ታሪክ የዚሁ ቅዱስ ጻድቅ ራሱ እንደ ሻማ እየቀለጠ ለእኛ ብርሃን የሆነ የታላቁ አባታችን አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ፍቅሩን እንመልከት። አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በሕዳር 26/ 245 ዓ.ም ከአባቱ ቅዱስ ምናጦስና ከእናቱ ቅድስት ማርያም ሰናይት በጢሮስ /ግሪክ/ ተወለደ። የመጀመሪያ ስሙ ፍሬምናጦስ ይባላል። አባታችን አቡነ ሰላማ የ12 ዓመት ልጅ እያለ ሜሮጵዮስ የተባለ ነጋዴ /ፈላስፋ/ ይዞት ወደ አገራችን በእግዚአብሔር ፈቃድ መጣ። ከእርሱም ጋር ኤድስዮስ የተባለም አብሮት እንደነበረ ይታወቃል። እነዚህን ሁለት ወጣቶች አስከትሎ የመጣው ሜሮጵዮስ በቀይ ባሕር አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በጣሉለት አደጋ በዚሁ እንደ ሞተ ታሪክ ይነግረናል። ፍሬምናጦስና ኤድስዮስ ግን በወቅቱ የአክሱም ንጉሥ የነበረው ንጉሥ ታዜር ጋር አድገዋል። ንጉሡ በአእምሮ መብሰላቸውን ተመልክቶ ፍሬምናጦስ በጅሮንድ ኤድስዮስም ጋሻ ጃግሬው አድርጎ ሾማቸው። ከዚያ በኋላ ንጉሥ ታዜር ሲያርፍ ወደ ፈለጉበት እንድሄዱ ነፃ ስለተለቀቁ ኤድስዮስ ወደ አገሩ ተመልሶ ሄዷል። አባታችን አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ግን በጨለማ የሚኖረውን ሕዝብ ትቼ ወደ አገሬ አልመለስም በማለት እኛን በማፍቀር እንደቀረ ታሪክ ያስረዳናል። ወዳጄ! የቅዱሳን ፍቅራቸው እውነትም ልብ ይነካል። በዚያን ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ ስርዓተ ንስሐ፣ ስርዓተ ጥምቀት፣ ስርዓተ ቅዳሴ፣ ስርዓተ ቅዱስ ቁርባን የሚያከናውን ጳጳስ ስላልነበረ ይህን የተመለከቱ ነገስታት ኢዛናና ሳይዛና ጵጵስና እንዲያመጣ አባታችን አቡነ ሰላማን ወደ ግብጽ ላኩት። አባታችንም ወደ ግብጽ በመሄድ ስርዓቶቹን በመማር በቅዱስ አትናትዮስ አንብሮተ እድ ˝ኤዽስ ቆጶስ ዘአክሱም ወዘኩላ ኢትዮጵያ” ተብሎ ጵጵስና ተቀበለ። ወደ አገራችን ከተመለሰ በኋላ መጀመሪያ ነገስታት ኢዛናና ሳይዛናን አጥምቆና አቁርቦ አብርሃ ወአጽበሃ በማለት ስመ ክርስትና ሰጣቸው። በመቀጠልም በመላው አገራችን እየተዘዋወረ በማስተማር ስርዓቱን ፈጽሟል። ከዚህም የተነሳ ጨለማን አስወግዶ ብርሃንን የገለጠ ቀዳሚ የምድረ ሐበሻ ታላቅ ሐዋርያ ነው። የቀናች ሃይማኖትን በማስተማር ጨለማውን ብርሃን በማድረጉ “ብርሃን ገላጭ ሰላማ” ተብሏል። የሓምሌ ወር ስንክሳር። አባታችን አቡነ ሰላማ በኢትዮጵያና ኤርትራ በመላው ምድረ ሓበሻ በኪደተ እግሩ ተመላለሶ ወንጌል እንዳስተማረና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ድውያንን ፈውሶ ሙታንን እንዳስነሳ ገድሉ ያስረዳናል። በተለያዩ ባዕድ አምልኮ ያመልክ የነበረ ሕዝብም በጣፋጭ ስብከቱ እግዚአብሔርን ወደ ማመን መልሶታል ። በጸሎቱ አጋንንትን ጠራርጎ ከአገራችን በማስወጣት ሰላም የሰጠን የሰላም አባት ነው። ˝ሰላማ˝ ማለት ˝ሰውና እግዚአብሔርን የሚያስታርቅ˝ ማለት ነው። ወዳጄ ሆይ! አባታችን አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በ 350 ዓ.ም ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ እንዲታወጅ አድርጓል። ˝አቡነ ̋ /አባታችን/ የሚለውን ማዕረግ ለመጀመሪያ የተሰጠው ለርሱ ነው። ጻድቁ አባታችን በዕድሜም በጸጋም ትልቅ አባት በመሆኑ ከኋላው ለመጡት ብዙዎች ቅዱሳን መምህራቸውና አባታቸው ነው። ለዚህም ነው አባታችን ቅዱስ ያሬድ “ዝንቱ ብእሲ መምህርነ ዘተፈነወ ውስተ ምድርነ ይከሰተ ብርሃነ” በማለት አመስግኖታል። ብርሃንን ለመግለጥ ወደ አገራችን የተላከ መምህራችን ማለቱ ነው። ወዳጄ ሆይ! በልጅነታቸው የመጡት አባታችን አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የአገራችን ፍቅር አስገድዷቸው እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው በአገራችን የኖሩ ሲሆን በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥ ከሰሯቸው የተለያዩ ድንቅ ሥራዎች ውስጥ በጥቂቱ እንደሚከተለው ይሆናል።
- ወንጌል የሚያስተምሩ፣ የሚያጠምቁና የሚያቆርቡ ካህናትና ዲያቆናት ሾመዋል። - ለምእመናን መካሪ የንስሐ አባት እንዲኖራቸው አድርገዋል። - ከአብርሃ ወአጽብሃ ጋር በመሆን አብያተ ክርስቲያን አንጸዋል። - ቅዱሳት መጻሕፍት ከሱርስት፣ ከዕብራይስጥና ከግሪክ ወደ ግእዝ ቋንቋ እንዲተረጎሙ አድርገዋል። - የሳባውያን ፊደል አቀማመጥ በማስተካከል ከግራ ወደ ቀኝ የመጻፍንና የማንበብን ዘዴ በማስተማር ብዙ ውለታ የዋሉ ታላቅ አባት ናቸው።
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.