አራታ
አራታ በሱመር አፈ ታሪክ የተገኘ ጥንታዊ መንግስት ነበር። በዚያው መሠረት አራታ ሀብታም፣ ተራራማ፣ በወንዞቹ ምንጭ ያለበት አገር ይባላል።
በተለይ የሚታወቀው ከ4 ጥንታዊ ጽሕፈቶች ነው። እነሱም፦
- ኤንመርካርና የአራታ ንጉስ Archived ሴፕቴምበር 26, 2011 at the Wayback Machine - ኢናና የምትባል ንግሥት ከአራታ ግቢ ወደ ኡሩክ ንጉስ ኤንመርካር ግቢ በመዛወርዋ የአንጋሽ ሚና እየተጫወተች ነው። የሁለቱም ነገሥታት ሚስት ትባላለች። (ኋላም እንደ አምላክ ተቆጥራ የብዙዎች አማልክት ሚስት በሱመር ሀይማኖት ተባለች።) ኤንመርካር በኡሩክ ታላቅ ግንብ እንዲሠራ ከአራታ የተከበሩ ድንጋዮች ይጠይቃል። የአራታ ንጉስ ግን እንቢ ብሎ ከኤንመርካር ጋር እንደ ተለየ ይመዝገባል። የኤንመርካር ወኪሎች ሱሳን፣ አንሻንንና ሰባት ተራሮች በመሻገር ወደ አራታ ይደርሳሉ።
- ኤንመርካርና ኤንሱህከሽዳና - በዚሁ ጽሑፍ መሠረት የአራታ ንጉስ ስም ኤንሱህከሽዳና (ወይም ኤንሱህጊራና) ይሠጣል።
- ሉጋልባንዳ በተራራ ዋሻ - በኋላ የኤንመርካር ተከታይ ንጉስ የሆነ ሉጋልባንዳ በዚህ ዘመን የኤንመርካር ሻለቃ ነው። የኤንመርካር ሠራዊት በአራታ ላይ ዘመቻ ያደርጋል።
- ሉጋልባንዳና አንዙ ወፍ - ሉጋልባንዳ እንደገና በኤንመርካር ሠራዊት አለቃ ሆኖ በአራታ ላይ እንደ ዘመተ ይላል።
የታሪክ ሊቃውንት ሁሉ ስለ ስፍራው በአንድነት አይስማሙም፤ ብዙዎቹ የአዘርባይጃንና የአራክስ ወንዝ አካባቢ እንደ ጠቀለለ የሚል አስተያየት አላቸው። አራታ አንዳንዴ የሚጠቀሰው በዚያች አራራት አገር በኋላ ዘመን በኖረው በኡራርቱ በሚነካ ጉዳይ ሲያውሩ ነው። ሌሎች ግን በፋርስ ወይም በዛሬው አፍጋኒስታን እንደ ነበር የሚል ግመት አላቸው። በዚህ ረገድ በሳንስክሪት ጽሕፈቶች ደግሞ «አራጣ» የሚባል አገር በአፍጋኒስታን ይገኛል። ሌሎችም አራታ ከአፈ ታሪክ ውጭ የማይታወቅ ስለ ሆነ ሥፍራው ሊታወቅ አይችልም የሚል አስተያየት አላቸው።
በግሪኩ ሄሮዶቶስ ታሪክ፣ የፋርስ ሕዝብ «አርታዮይ» (አርታያውያን) ተባሉ (VII, 61. 150)። በሄሮዶቶስ ጊዜ የኖረ ሌላ ግሪክ ጸሐፊ ሄላኒኮስ ደግሞ እነዚህ «አርታያ» በሚባል አውራጃ እንደ ኖሩ ይመስክራል።
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.