አራም (ጥንታዊ አገር)

አራም በመጽሀፍ ቅዱስ የሚጠቀስ ጥንታዊ አገር ነው። ይህ አገር በስሜን መስጴጦምያና ከዚያ ምዕራብ በሶርያ ይገኝ ነበር። በጠቅላላ አራማውያን የኖሩባቸው አገሮች ማለት ነው። እነዚህ የሴም ልጅ አራም ዘር መሆናቸውን የሚል ልማድ አለ።

መጽሐፈ ኩፋሌ (9፡19) መሠረት፣ የኖህ ልጆች ምድሪቱን ሲያከፋፈሉ የአራም ልጆች የወረሱት ርስት ከኤፍራጥስና ከጤግሮስ ወንዞች መካከል ያለው አገር ሁሉ ያጠቅልል ነበር። ካራንንም ከተማ የጠቀለለው ሀገር «አራም-ናሐራይን» (የሁለት ወንዞች አራም) ወይም «ፓዳን-አራም» ይባላል። «አራም-ናሐራይን» አንዳንዴ በብሉይ ኪዳን ውስጥ «መስጴጦምያ» (መሳፍንት ፫፣፰) ወይም «የሶርያ ሁለቱ ወንዞች» (መዝሙር ፶፱፣ አርዕስት) ተብሏል። በኋላ ፪ቱ ወንዝች ኤፍራጥስና ሐቡር ወንዝ እንደ ተቆጠሩ ይመስላል። የአራም ሰው ላባንና ዘመዱ ያዕቆብ ጠረፋቸውን በገለዓድ ሀገር እንዳስተካከሉ በኦሪት ዘፍጥረት 31 ይገለጻል። ሆኖም ጎረቤቶቻቸው አሞራውያን ደግሞ ከኤፍራጥስ ምዕራብ ይዘዋወሩ ነበር።

ኤብላ ጽላቶች ላይ (2100 ዓክልበ. ግድም) «አራሙ» እና «አርሚ» የሚሉ ስያሜዎች ይገኛሉ፤ «አርሚ» የሐላብ (አሌፖ) ስም ነበር። በ2034 ዓክልበ. ያሕል በአካድ ንጉሥ ናራም-ሲን በስሜን ተራሮች በተደረገው ዘመቻ «የአራም አለቃ ዱቡል» እንደማረከው ይመዘገባል።[1] የአራም ሕዝብ ወይም አገር ደግሞ በማሪ ጽላቶች (1700 ዓክልበ. ግድም) ታይተዋል።

በ1505 ዓክልበ. ግድም የአራም-ናሐራይም ንጉሥ ኲሰርሰቴም እስራኤልን እንደ ገዛ በመሳፍንት ፫፣፰ ይጻፋል። በግብጽ መዝገቦች የተገኙት የአካድኛ «አማርና ደብዳቤዎች» (~1350 ዓክልበ.) «አህላሙ» የተባለውን ሕዝብ በሶርያ ይጠቅሳሉ። ይህ «አህላሙ» ብሔር ደግሞ በመስጴጦምያ መዝገቦች ይገኛል። በ1100 ዓክልበ. ግድም የአሦር ንጉሥ 1 ቴልጌልቴልፌልሶር «አህላመ-አርማያ» አላቸው። ከዚህ በኋላ ብሔሩ «አራም» በመባል ይታወቅ ነበር፣ የአራማይስጥ ቋንቋ ጽሑፎች ይታዩ ጀመር። አራማይስጥ በሴማዊ ቋንቋች ከአካድኛዕብራይስጥ (ከነዓንኛ) መካከለኛ ቢሆንም ከ1100 ዓክልበ. አስቀድሞ የሑርኛ ተናጋሪዎች (ሑራውያን) እንደ ነበሩ የሚያሥቡ አሉ። በሌሎች ልማዶች ዘንድ ግን የአራም ልጆች (ለዮቅጣንም ወይም ለኤቦር ልጆች እንደሚባል) የሰው ልጆች መጀመርያ ቋንቋ ለመጠበቅ ተፈቀደላቸው።

በእስራኤል ነገሥታት ዘመን አራም-ደማስቆአራም-ረሆብና አራም-ሱባ (ሱባ ወይም «የሶርያ ሶባል») የተባሉት መንግሥታት ይጠቀሳሉ።

  1. Year-Names for Naram-Sin
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.