አሪስጣጣሊስ

አሪስጣጣሊስ በግሪኩ Ἀριστοτέλης ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ384 ዓ.ዓ. እስከ ታህሳስ7፣ 322ዓ.ዓ. የኖረ የጥንቱ ግሪክ ፈላስፋ ነበር። በምዕራቡ አለም ስልጣኔ ከፍተኛ ግምት ያለው ፈላስፋ ነበር። ምንም እንኳ አሪስጣጣሊስ ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ቢሆንም ዘመናትን አልፈው ተርፈው የሚገኙት መጻሕፍት ጥቂት ናቸው። የፕላቶ ተማሪ የሆነው አሪስጣጣሊስ በተራው የንጉሱ ታላቁ እስክንድር አስተማሪ የነበርና ንጉሱ በእድሜ ጎልምሶ የዚያን ዘመን አለም በሚገዛ ወቅት በስሩ ከሚያስገብራቸው እንግዳ አገሮች እጽዋትንና እንሣትን ለፈላስፍው መምህሩ ይልከለት ነበር።

የአሪስጣጣሊስ ሐውልት: ከሊሲፐስ ነሐስ ሃውልት የተቀዳ፣ ለቭር ቤተ መዘክር

የህይወት ታሪክ

አባቱ ኒቆማቀስመቄዶንያ ንጉስ የነበረው ንጉስ አሚንታስ ሐኪም ነበር። ከ18 እስከ 37 አመት እድሜው፣ ኑሮውን በአቴና ያደረገው አሪስጣጣሊስ በወቅቱ የፕላቶ ተማሪና እንደ ጸጉረ ልውጥነቱ ለአቴና ሜቲክ የነበረ ነበር።[1]

አሪስጣጣሊስ ፕላቶ በ347ዓ.ዓ. እስከሞተ ድረስ ከአስተማሪው ሳይለይ ለ20 አመት በፕላቶ አካዳሚ ህይወቱን አሳልፏል። ከዚህ በኋላ ከዜኖክራቴስ ጋር በመሆን ትንሹ እስያን በመጎብኘት ስለአካባቢው አትክልትና እንሣት ምርምር ቢያደርግም በካከሉ የመቄዶንያው ንጉስ ዳግማዊ ፊሊጶስ ልጅን ታላቁ እስክንድርን እንዲያስተምር በ343 ዓ.ዓ. ግብዣ አደርገለት።[2]

መቄዶንያ አካዳሚ እራስነት የተሾመው ፈላስፋ እስክድንርን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሁለት ነግስታትን፡ [[ቀዳማዊ ቶሎሚ]ንና ካሳንደርን ለማስተማር በቅቷል። አሪስጣጣሊስ እስክንድር ወደ ምስራቃዊ የዚያ ዘመን አለም እንዲስፋፋ፣ ፋርስንም እንዲያስገብር ይገፋፋው ነበር። ለወደፊቱን ንጉስ እንዲህ ሲል ይመክረው ነበር፡ "ለግሪኮች መልካም መሪ ሁን፣ ለአረመኔወቹ ግን አምባ ገነን ሁን" በማለት። [3]p58

335 ዓ.ዓ. ላይ አሪስጣጣሊስ ወደአቴና በመመለስ ሊሲየም የተስኘውን የራሱን ትምህርት ቤት ከፈት። ለሚቀጥሉት 12 አመታት በዚሁ ትምህርት ቤቱ አብዛኛውን ጽሁፎችን እንደጻፈ ይገመታል[2] .[4]

የአርሲጣጣሊስ ሙሉ ስራወች የጥንቱ ግሪክ እውቀት አጠቃላይ መዝገብ ነው ሊባል ይችላል። በአንድ አንዶች አስተሳሰብ አሪስጣጣሊስ በርሱ ዘመን የሚታወቀን ማናቸውን እውቀት ጠቅልሎ በማወቅ የመጨረሻውን ሰው ነበር ሲባል ይጠቀሳል[5]

ከዚህ በኋላ የእስክንድርን "መለኮታዊ ነኝ" አስተሳሰብ በመጻረሩና በመናቁ ከእስክንድር ጋር ተጣሉ፣ እንዲያውም እስክንድር የማስፈራሪያ ደብዳቤዎች ይልክለት ነበር። ሆኖም እስክንድር በ323 ዓ.ዓ. ባቢሎን ውስጥ በመሞቱ ፈላስፋው ጉዳት አልደረሰበትም ነበር። ከእስክንድር ሞት በኋላ አቴናውያን በመቄዶናውያን ላይ በመነሳታቸው አሪስጣጣሊስ አቴናን ለቆ ተሰደደ። በ322ዓ.ዓ. ዩቦያ በተባለ ስፍራ አሪስጣጣሊስ አረፈ።

ፍልስፍና

ታላቆቹ የጥንቱ ግሪክ 3 ፈላስፎች ሶቅራጠስፕላቶ እና አሪስጣጣሊስ ናቸው። ሶቅራጠስ የፕላቶ አስተማሪ ሲሆን ፕላቶ በተራው የአሪስጣጣሊስ ነበር። እኒህ ሶስቱ የምዕራቡ አለም ፍልስፍና መስራቾች ተብለው ይታወቃሉ። [6]

የፕላቶ ዋና ሃሳብ ከስሜት ህዋሳት የሚመነጭ ዕውቀት ምንጊዜም የተወናበደና ያልጠራ ነው። ስለሆነም እውነተኛ ዕውቀት ተጨባጩን አለም ከሚርቅ ሃሳብ ወይም አዕምሮ ይመጣል። አዕምሮ ብቻ ቅርጾችን ማወቅ ይችላል። ቅርጽ ማለቱ የነገሮች እውነተኛ ህልውና። ተጨባጩ አለም የኒህን ቅርጾች የተወላገደ ቅጅ ነው ብሎ ፕላቶ ያምን ነበር።

አሪስጣጣሊስ በበኩሉ ከአስተማሪው በተቃራኒ ያስብ ነበር። በአሪስጣጣሊስ አስተሳሰብ ከስሜት ህዋሳት የሚመነጨው እውቀት የበለጠ ዋና ነበር። ይህ አስተሳሰብ ከብዙ መቶ አመታት በኋላ ሳይንሳዊ ዘዴ የሚባለው የሳይንስ መሳሪያ መሰረት ሆነ[7]። አሪስጣጣሊስ ፊዚክስሜታፊዚክስኒቆሜቂያን ኤቲክስፖለቲክስ እና ፖኤቲክስ የተሰኙ መጽሐፎችን በመድረስ የዘመናዊውን ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች መሰረት ጥሏል።


አሪስጣጣሊስ በአቶም ኅልዮት አያምንም ነበር። በጊዜው የነበረው የግሪኩ ዴሞክሪተስ የቁስ አካልን ከእኑሶች መሰራት በመቃወም ቁስ አካል በሙሉ ከልሙጥ ወጥ አካላት የተሰሩ ናቸው ብሎ ያምን ነበር። ጆን ዳልተን የተሰኘው የእንግሊዙ ሳይንትሲት የአሪስጣጣሊስን አስተሳሰብ በተግባር ውድቅ በማድረግ የዴሞክሪተስን አተማዊ ኅልዮት በ1804 አረጋገጠ።

ሥነ አምክንዮ

አሪስጣጣሊስ ስለ አምክንዮ ብዙ ጽሑፎችን አቅርቧል። ስለሆነም የአምክንዮ አባት በመባል ይታወቃል። አምክንዮ ማለቱ አንድ ሃስብ እውነት ወይም ውሸት መሆኑን ለመወሰን የሚረዳን የዕውቀት ዘርፍ ነው። እስካሁን ዘመን ድረስ የአሪስጣጣሊስ ሥነ አምክንዮ በአለም ዙሪያ ይሰራበታል።

የውጭ ንባብ (እንግሊዝኛ)

ማጣቀሻ

  1. Ackrill J.L. (ed) 1981. Aristotle the philosopher. Oxford.
  2. Bertrand Russell 1972. A history of western philosophy. Simon & Schuster, N.Y.
  3. Green P. 1991. Alexander of Macedon, University of California Press.
  4. Lloyd G.E.R. 1968. Aristotle: the growth and structure of his thought. Cambridge. ISBN 0-521-09456-9.
  5. Neill, Alex; Aaron Ridley (1995). The philosophy of art: readings ancient and modern. McGraw Hill. p. 488. http://www.amazon.com/dp/0070461929/.
  6. Barnes J. 1995. The Cambridge companion to Aristotle, Cambridge University Press
  7. http://www.philosophypages.com/ph/aris.htm
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.