አረማይክ
አረማይክ ወይም አራማይስጥ፣ የሶርያ ቋንቋ ወዘተ. ( ܐܪܡܝܐ /አራማያ/) ከሴማዊ ቋንቋዎች አንዱ ሲሆን በመካከለኛ ምሥራቅ ከጥንት ጀምሮ ታውቋል።
መጀመርያ የአረማይክ ጽሑፎች ከ1000 ዓክልበ. ግድም በፊንቄ አልፋቤት ነበሩ፤ ይህም የአራም ሕዝብ የተናገሩት ጥንታዊ አራማይስጥ ነበር። በአንድ አስተሳሰብ ቋንቋቸው ከ1100 ዓክልበ. አስቀድሞ ሑርኛ ይሆን ነበር፤ የአሦርም መንግሥት ከገዙአቸው በኋላ እንደ አካድኛ ሴማዊ ሆነ።
ከ800 ዓክልበ. አካባቢ በኋላ የራሱ አረማይክ አልፋቤት ከፊንቄ አልፋቤት ተለማ።
በ740 ዓክልበ. የአሦር ንጉሥ 3 ቴልጌልቴልፌልሶር አረማይስጥ ከአሦርኛ (አካድኛ) ጋር ይፋዊና መደበኛ ቋንቋ አደረገው። ከዚያ ጀምሮ የአረማይስጥ ጥቅም እየተስፋፋ የአካድኛ ጥቅም በየጊዜ ይቀነስ ነበር። ከአሦር ውድቀት (617 ዓክልበ.) በኋላ በባቢሎኒያ መንግሥት፣ ከባቢሎኒያም ውድቀት (547 ዓክልበ.) በኋላ በፋርስ አሓይመኒድ መንግሥት ውስጥ፣ አረማይክ መደበኛና ይፋዊ ቋንቋ ተደረገ፣ ስለዚህ ጥቅሙ በሰፊ ከግብጽ እስከ ባክትሪያ ድረስ ይዘረጋ ነበር። በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የተገኘው አራማይክ በተለይ በትንቢተ ዳንኤል ከዚሁ ዘመን ነው።
የፋርስ መንግሥት ለታላቁ እስክንድር ከወደቀ በኋላ (339 ዓክልበ.) ግሪክኛ ደግሞ ከአረማይክ ጋር መደበኛ ቋንቋ ተደረገ። በኢየሱስ ዘመነ ስብከት 25 ዓም ገደማ፣ የይሁዳ ሕዝቦች መነጋገሪያ አረማይክ ሆኖ ስለ ቀረ፣ ኢየሱስ የሰበከላቸው በአረማይክ ነበር። ወንጌል የተጻፈው በግሪክ ቢሆንም፣ በግሪኩ ውስጥ አንዳንድ አረማይክ ቃላት በንግግሩ ውስጥ ተጽፈዋል፦ ለምሳሌ «ጣሊታ» (ሴት ልጅ) ማር. ፭፡፵፩፣ «ኤፍታህ» (ተከፈት) ማር. ፯፡፴፬።
ከ216 ዓም ያህል በኋላ ከጥንታዊ አራማይስጥ የተለያዩ ቀበሌኞች ሊወሰኑ ይቻላል፦
- ምሥራቅ፦
- ምዕራብ፦
- የፍልስጤም አረማይክ - በፍልስጤም ክፍላገር አይሁዶች (በዕብራይስጡ አልፋቤት) እና ክርስቲያኖች (በሱርስጥ አልፋቤት)፣
- ሳምራዊ አረማይክ (/አራሚት/) - በፍልስጤም ሳምራውያን (ሳምራዊ አልፋቤት)
ከ629 ዓም በኋላ የራሺዱን ኻሊፋት ስለ ወረረ አረብኛ የመካከለኛ ምስራቅ ዋና መደበኛ ቋንቋ ሆነ። እነዚህ «መካከለኛ አረማይክ» አይነቶች እስከ 1200 ዓም አካባቢ ድረስ ቢነገሩም፣ በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶች ውስጥ እስካሁን ይጠቀማሉ።
ከ1200 ዓም አካባቢ እስከ ዛሬ ድረስ የሚነገሩ ዋና አዳዲስ አረማይክ ቋንቋዎች፦ አዲስ አሦራዊ አረማይክ (232,000 ተናጋሪዎች)፣ አዲስ ከለዳዊ አረማይክ (213,000 ተናጋሪዎች) እና ቱሮዮ (250,000) ሁላቸው /ሱረጥ/ ተብለው ከሱርስጥ የወጡ ተመሳሳይ ቀበሌኞች ናቸው። የተዛመዱት የአይሁድ አረማይስጥ ቀበሌኞች በጠቅላላ 25,000 ያህል ተናጋሪዎች አሁን ወደ እስራኤል ተመልሰዋል። ለአዲስ ማንዳይኛ ጥቂት መቶ ተናጋሪዎች በፋርስ ቀርተዋል።
በተጨማሪ አዲስ ምዕራብ አረማይክ (/አሮማይ/) በአንዳንድ መንደር በሶርያ ቀርቶ 24,000 ተናጋሪዎች አሉት።