ኤልሞዳድ
ኤልሞዳድ (ዕብራይስጥ፦ אלמודד) በኦሪት ዘፍጥረት 10:26 መሠረት የዮቅጣን በኲር ልጅ ነበር። በ፩ ዜና መዋዕል 1:20 እንደሚታይ ስሙ ደግሞ አልሞዳድ ተጽፎ ይገኛል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ቅርሶች (ወይም «ፕሲውዶ-ፊሎ») የተባለው ጽሑፍ (ምናልባት 70 ዓ.ም. ግድም ተጽፎ) እንዳለው፣ ዮቅጣን በባቢሎን ግንብ ወቅት የሴም ልጆች አለቃ ሲሆን ከልጆቹ ግን ፭ቱ ከነአልሞዳድ እምቢ ይላሉ፤ ዮቅጣንም ከሰናዖር እንዲያመልጡ ያስችላል።
«ኤልሞዳድ» ማለት ምናልባት «ቀያሹ» ወይም «የኤል (ኤሎሂም) ቀያሽ» ሊሆን ይችላል። በአይሁዳዊው ጽሁፍ ታርጉም ፕሲውዶ-ዮናታን ዘንድ፣ ይህ ኤልሞዳድ ምድርን በገመዶች ይቀይሥ ነበር። ሌሎች ደራስያን የስሙ ትርጉም «የኤል መውደድ» ወይም ፍቅረ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ብለዋል።
ፍላቪዩስ ዮሴፉስ እንደ ጻፈው፣ ኤልሞዳድና ወንድሞቹ ሁሉ በሕንዱስ ወንዝ ላይ ሠፈሩ። አብዛኞቹ ጸሃፊዎች ግን በየመን እንደ ሠፈሩ ይላሉ።
ጀርመናዊው መኖክሴ ዮሐንስ አቬንቲኑስ (1515 ዓ.ም. ግድም) አንዳለው ግን ከዮቅጣን ልጆች አንዳንድ በአውሮፓ ሠፍረው ነበር። ከነዚህ መካከል ድልማጥያ አገር ስሙን ከ«ዳልማታ» (አልሞዳድ) እንደ ወረሰ ይላል።
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.