ታላቁ ሳርጎን
ታላቁ ሳርጎን (አካድኛ፦ ሻሩ-ኪን «ዕውነተኛ ንጉሥ») ከ2077 እስከ 2064 ዓክልበ. ግድም ድረስ (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) የአካድ ንጉሥ ነበረ።
የሱመር ነገሥታት ዝርዝር ቅጂዎች ለ56፥ 55 ወይም 54 ዓመታት እንደ ገዛ ቢሉንም፣ በሥነ ቅርስ ከዘመኑ የተገኙት ሰነዶች ለአራት ልዩ ልዩ ዓመቶች ብቻ ተገኝተዋል። ስለዚህ በጣም ረጅም ዘመን እንደ ገዛ አጠራጣሪ ነው።
የታወቁት 4 ዓመት ስሞች እንዲህ ናቸው፦ «ሳርጎን ወደ ሲሙሩም የሄደበት ዓመት»፣ «ሳርጎን ኡሩአን ያጠፋበት ዓመት»፣ «ሳርጎን ኤላምን ያጠፋበት ዓመት»፣ እና «ማሪ የጠፋበት ዓመት» ናቸው።[1] ይህ የዓመት ስሞች አቆጣጠር ዘዴ የሚታወቀው በዋናነት ከሳርጎን ዘመን ጀምሮ ነው።
ንጉሥ ከመሆኑ በፊት
የሳርጎን ትውፊት በተባለው ሱመርኛ ጽላት[2] የአባቱ ስም ላዕቡም ይሰጣል። የነገሥታት ዝርዝር የሳርጎን አባት የአጸድ ጠባቂ እንደ ነበር ይለናል። በኋላ ዘመን (7ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ.) በአሦርኛ በተጻፈ ትውፊት ዘንድ፣ ሳርጎን «እናቴ ዝቅተኛ ነበረች፤ አባቴንም አላወቅሁም፣ የአባቴም ወንድም በተራራ ይኖራል» ይላል። ግልጽ የሚሆነው ከንጉሣዊ መነሻ አለመሆኑ ነው። የአሦርኛው ሰነድ ደግሞ እንዳለው እናቱ ዲቃላ ማሳደግ ባለመቻሏ በሸምበቆ ቅርጫት ውስጥ በወንዙ ላይ አስቀመጠችውና የመስኖ ቆፋሪ የሆነ ሰው አኪ አገኝቶት አሳደገው። ሳርጎን ያደገበት መንደር «አዙፒራኑ» በኤፍራጥስ ዳር ሲሆን አኪ የአጸዱ ጠባቂ እንዲሆን እንዳስተማረው ይጨምራል።[3]
ከተራ ክፍል በመወለዱ ምናልባት ሻሩ-ኪን፥ «ዕውነተኛ ንጉሥ»፥ የልደት ስሙ ሳይሆን ዘውድ ከተጫነው የወሰደው ስያሜ ይሆናል የሚያስቡ ሊቃውንት አሉ። በአካድኛው ስሙ ሻሩ-ኪን ሲሆን «ሳርጎን» የሚለው አጻጻፍ በትንቢተ ኢሳይያስ ሞክሼው የአሦር ንጉሥ 2 ሳርጎን በዕብራይስጡ እንዲህ ስለሚባል ነው።
ሱመርኛው የሳርጎን ትውፊት ንጉሥ ከመሆኑ በፊት ያለውን ታሪክ እንዲህ ይሰጣል። ሳርጎን ከኪሽ ንጉሥ ኡር-ዛባባ ሎሌዎች መካከል የቤተ መንግሥት አስረካቢ ሲሆን፣ ንጉሡ ኡር-ዛባባ ሕልምን አይቶ ሳርጎንን የ«ዋንጫ ተሸካሚ» ማዕረግ ሾመው፣ ይህም በመጠጦች (ጠጅ) ሳጥን ላይ ሓላፊነቱን ያለው ማለት ነው። ከዚያ ሳርጎን በራሱ ሕልም ኡር-ዛባባ በደም ወንዝ ውስጥ ሲሰመጥ ያያል። ስለዚህ ኡር-ዛባባ ሰምቶ እጅግ ተቸግሮ ሳርጎንን በተንኮል ለመግደል ያቅዳል። ሳርጎን የንጉሥ ተልዕኮ ሆኖ አንድ መልዕክት በሸክላ ጽላት ለኡሩክ ንጉሥ ሉጋል-ዛገሢ እንዲወስደው ታዘዘ። መልዕክቱ ግን መልዕክተኛውን ስለ መግደል የሚል ልመና ነበር። ሰነዱ ተሰብሮ ከዚያ በኋላ ምን እንደ ሆነ ቢያጣም፣ ሳርጎን የአካድ መንግሥት መሥራች ለመሆን ስለ በቃ ሴራው እንዳልተከናወነ መገመት እንችላለን።
የነገሥታት ዝርዝሩና የባቢሎን መቅደስ ዜና መዋዕል (ወይም «የቫይድነር ዜና መዋዕል» [4]) የተባለው ጽላት ሳርጎን የኡር-ዛባባ «ዋንጫ ተሸካሚ» በማድረጋቸው ከሱመርኛው ሳርጎን ትውፊት ጋራ ይስማማሉ። ዜና መዋዕሉ እንዲህ አለው፦ ኡር-ዛባባ ዋንጫ ተሸካሚውን ሳርጎንን የመቅደሱን ወይን ጠጅ መሥዋዕት እንዲቀይር አዘዘው። አልቀየረም ግን ለመቅደሱ ቶሎ እንዲሠዋ ጠነቀቀ። ከዚህ በኋላ በአረመኔው ጣኦት ሜሮዳክ ሞገስ የዓለም 4 ሩቦች ግዛት እንዳገኘው በማለት ይጨምራል። ይህ ማለት በኒፑር የነበሩት ቄሳውንት ንጉሥነቱን እንዳዳገፉት ይሆናል።
የሳርጎን መንግሥት
ስለ ሳርጎን መንግሥት በአካድ የተለያዩ ምንጮች አሉ። የሚከተለው ታላቅ የጽላት መዝገብ ስለ ሳርጎን መንግሥት ብዙ መረጃ ይሰጣል[5]፦
- «ሳርጎን የዓለም ንጉሥ ከ9 የአካድ ሥራዊቶች ጋር ኡሩክን አሸነፈ። እርሱ እራሱ ሀምሳ ከንቲቦችንና ንጉሡን ማረከ። በናጉርዛም ደግሞ በውግያ ተዋገና አሸነፈ። እንደገና ለ3ኛ ጊዜ ሁለቱ ተዋጉና እርሱ አሸነፈ።
- ኡሩክ ከተማ አጠፋ፣ ከዚያም ግድግዶቹን አፈራረሰ። የጦር መሳርያዎቹን ከኡሩካዊው ሰው ጋር አጋጨ፣ ድልም አደረገው። ከሉጋል-ዛገ-ሲ የኡሩክ ንጉሥ ጋር የጦር መሳርያዎቹን አጋጨ፣ ከዚያም ያዘው። በአንገት ብረት ወደ መቅደሱ በር አመጣው። ሳርጎን የአካድ ንጉሥ ከዑር ሰው ጋር የጦር መሳርያዎቹን አጋጨ፣ ድልም አደረገው። ከተማውን አጠፋ፣ ከዚያም ግድግዶቹን አፈራረሰ። የጨረቃ ጣኦት መስጊድ አጠፋ፣ ከዚያም ግድግዶቹን አፈራረሰ። ከላጋሽ እስከ ባሕር ድረስ ያሉትን አገሮች ሁሉ አጠፋቸው፣ መሣሪያዎቹንም በባሕር አጠባቸው።
- ደግሞ በኡማ ከተማ ላይ በውግያ ድል አደረገ። ለአገሩ ንጉሥ ለሳርጎን ኤንሊል ጠላትን አልሰጠውም። ከላይኛው ባሕር እስከ ታችኛው ባሕር ድረስ ያለውን ግዛት ኤንሊል ሰጠው። በተጨማሪ ከታችኛው ባሕር እስከ ላይኛው ባሕር ድረስ የአካድ ዜጋዎች ብቻ አገረ-ገዥነትን ያዙ። የማሪ ሰው እና የኤላም ሰው በአገሩ ንጉሥ ሳርጎን ፊት ለማገልገል ቆሙ። ያገሩ ንጉሥ ሳርጎን ኪሽን ወደ ቀድሞ ሥፍራዋ መለሳት፤ ከተሞቿም ለእርሱ ጣቢያ ሆነው ተመደቡ።
- ሳርጎን የዓለም ንጉሥ በ34 ውግያዎች አሸናፊ ሆነ፤ እስከ ባህር ዳርቻ ድረስ የከተሞችን ግድግዶች አፈራረሰ። የሜሉሓ መርከቦች፣ የማጋን መርከቦች፣ የድልሙን መርከቦች በአካድ ወደብ አሠረ። ላይኛው አገራት ተሰጠ፦ ማሪ፣ ያርሙቲ፣ ኤብላ፣ እስከ አርዘ ሊባኖስ ደን፣ እስከ ብር ተራሮች ድረስ። ሳርጎን ኤንሊል ተፎካካሪ ያልፈቀደለት ንጉሥ፣ ቀን በቀን በፊቱ 5400 ሰዎች ዳቦ እንዲበሉ አደረገ።
- ሳርጎን የዓለም ንጉሥ ኤላምንና ፓራሕሱምን አሸነፈ። የሉሒሻን ልጅ ሂሸፕራሺኒ፥ የኤላምን ንጉሥ፥ ማረከው።»
በኋላ ዘመን በተጻፈ ሌላ ሰነድ እንደሚለው የሳርጎን መንግሥት ከላይኛ ባሕር (ሜዲቴራኒያን) ማዶ እስከ አናኪና ካፕታራ (ቆጵሮስና ቀርጤስ) ድረስ፣ ከታችኛው ባሕር (የፋርስ ወሽመጥ) ማዶ እስከ ድልሙንና ማጋን (ባሕሬንና ኦማን) ድረስ ተዘረጋ። ሆኖም ከድልሙን በቀር እነዚህ ፉከራዎች በሌላ ምንጭ አልተገኙምና ኣጠራጣሪ ይሆናሉ።
ከሳርጎን በፊት የሱመር ይፋዊ እና መደበኛ ቋንቋ ሱመርኛ ሲሆን፣ በአካድ መንግሥት ከሳርጎን ጀምሮ አካድኛ ይፋዊ ሆነ። ይህ የሴማዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ አባል ነው። ከዚህ በላይ ለጊዜው በኤላም አካድኛ ይፋዊ ሆኖ እንዳደረገው ይመስላል።
የቀድሞ ነገሥታት ዜና መዋዕል (ABC 20)[6] ስለ ሳርጎን እንዲህ ይላል፦
- «ባሕሩን በምሥራቅ ተሻገረ፣
- በ11ኛው ዓመት ምዕራቡን አገር እስከ ሩቅ ጫፉ ድረስ አሸነፈ።
- በአንድ ሥልጣን ሥር አመጣው፣ ሐውልቶችን በዚያ አቆመ፣
- የምዕራቡም ምርኮ በጀልባዎች አዛወረ።
- የችሎቱ ሹሞች የ10 ሰዓት ቀን እንዲቀመጡ አደረገና
- የአገራት ወገኖችን በአንድነት ገዛ።
- ወደ ካዛሉ ገሥግሦ ካዛሉ የፍርስራሽ ቁልል አደረገው፣
- የወፍ መሥፈሪያ ቦታ ስንኳ አልቀረም።
- በኋላ፣ በእርጅናው፣ አገራት ሁሉ እንደገና አመጹና
- በአካድ ከበቡት። ሳርጎን ለመውጋት ወጥቶ ድል አደረጋቸው።
- ገለበጣቸው፣ ሰፊ ሥራዊታቸውን በተናቸው።
- በኋላ፣ ሱባርቱ በመላው ሓያላት ሳርጎንን አጠቃ፣ ወደ ጦሩ ጠራው።
- ሳርጎን ደፈጣ አዘጋጅቶ በፍጹም ድል አደረጋቸው።
- ሰፊ ሥራዊታቸውን በተናቸው፣
- ንብረታቸውንም ወደ አካድ ላከው።
- የባቢሎን ጒድጓድ አፈር ቆፍሮ
- አዲስ ባቢሎን በአካድ ፊት ሠራ።
- ስላደረገው በደል ታላቅ ጌታ ሜሮዳክ ተቆጥቶ ቤቱን በረሃብ አጠፋ።
- ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተገዦቹ አመጹበት፣
- ሜሮዳክም በመናወዝ ቀሠፈው።»
የቫይድነር ዜና መዋዕል ስለ ሳርጎን ዘመን ተመሳሳይ ታሪክ ይገልጻል፦
- «ቤተ መቅደሱን ጠበቀው። በዙፋን የቀመጡት ሁሉ ግብራቸውን ወደ ባቢሎን አመጡ።
- ነገር ግን ቤል (ሜሮዳክ) የሰጠውን ትዕዛዝ ቸል አለ። ከጒድጓዱ አፈር ቆፍሮ
- በአካድ ፊት ከተማ ሠራ፣ ስሙንም 'ባቢሎን' አለው።
- ኤንሊል (ሜሮዳክ) የሰጠውን ትዕዛዝ ለወጠና ሰዎች ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ድረስ (ሳርጎንን) ተቃወሙት። እንቁልፉን አጣ።»
ከነዚህ ምንጮች፣ የሱመር ዋና ቤተ መቅደስ ከኒፑር ወደ ባቢሎን አዲስ ሥፍራ ስላዛወረው ሕዝቡና ቄሳውንቱ እንዳመጹበት ይመስላል። ከዚህ ዘመን አስቀድሞ «ባቢሎን» ማለት የኤሪዱ መጠሪያ እንደ ነበር የሚል ማስረጃ አለ።[7]
ወደ ምዕራብ ስላደረጉት ዘመቻዎች ሌሎች መዝገቦች ይታወቃሉ። በአንዳንድ ጽላት ዘንድ፣ ሳርጎን የ40 ሺህ ወታደሮች ሠራዊት ነበረው። ከሥራዊቱ ጋር ደብረ አማናን ተሻገረ፣ ወደ አርዘ ሊባኖስ ደን ደረሱ። ወደ ማርዳማን አገር (ከስሜን ጤግሮስ ምዕራብ የነበረ የሑራውያን ክፍላገር) ለመውረር ያቅዳል። ከዚያ አገር የመጣ ተልእኮ ግን እንዲህ ይጠይቃል፦ «በዳርቻው ክፋቶች የሚያድቡበት የአሙሩ አገር አይደለምን?» ነገር ግን ሳርጎን አይመልስም፣ የሲሙሩም ሰዎችና ከብቶች ሁሉ ይዘው ከተማውን አፈራረሰ። ይህ በስሜን መስጴጦምያ የተገኘ የሆራውያን ከተማ-አገር ነበር። አሙሩ እና ሱባርቱ አገሮች እንደ ያዙ ይላል።[8]
በኬጥኛ የተጻፈው ግጥም የውግያ ንጉሥ ስለ ሳርጎን ምዕራብ ዘመቻ ነው። ይህ ጽሑፍ በአካድኛ ትርጉም ደግሞ በአሦርና በአማርና ደብዳቤዎች መካከል (በግብጽ) ተገኝቷል። ሳርጎን በጥልቅ በሐቲ አገር (አናቶሊያ) እንደ ዘመተ ይናገራሉ። ጽሁፉ እንደሚተርከው፣ በሐቲ በካነሽ የኖሩት አካዳዊ ነጋዴዎች በቡሩሻንዳ ንጉሥ ኑርዳጋል ስለ ተበደሉ ሳርጎን በሩቅ መንገድ ከሠራዊቱ ጋር መጥቶ ኑርዳጋልን እንዲቀጣው በሚል ልመና ልከው አስረዱት። የኑርዳጋል ሰዎች በጸጥታቸው እየኮሩ ዝም ብሎ የሳርጎን ሥራዊት ደረሰና ቶሎ አሸነፋቸው። ሦስት ዓመት በቡሩሻንዳ ቆይተው የከተማውን ግድግዶች ሰበሩ።
በአሦርኛው ሳርጎን ትውፊት እንደሚለው፣
- «ለ[...]4 ዓመታት መንግሥቴን ገዛሁት። የጥቁር ራስ ሕዝብ ላይ ገዛሁት፣ ነገሥኩት፤ ታላላቅ ተራሮች በነሐስ መጥረቢያዎች አጠፋሁ። በላይኛ ተራሮች ወጣሁ፣ በታችኛ ተራሮች በኩል ፈነዳሁ። የባሕሩን አገር ሦስት ጊዜ ወረርሁት፣ ድልሙንን ያዝኩ። ወደ ታላቅ ዱር-ኢሉ ወጣሁ። ... ከኔ በኋላ የሚከበር ማናቸውንም ንጉሥ... የጥቁር ራስ ሕዝብ ላይ ይግዛ፣ ይነግስ። ታላላቅ ተራሮች በነሐስ መጥረቢያዎች ያጥፋቸው፤ በላይኛ ተራሮች ይውጣ፣ በታችኛው ተራሮች በኩል ይፈነዳ፤ የባሕሩን አገር ሦስት ጊዜ ይውረር፤ ድልሙንን ይይዝ፣ ወደ ታላቅ ዱር-ኢሉ ይውጣ።»
ቤተሠብ
በሳርጎን ዘመን ከተቀረጹ ሰነዶች፣ የሳርጎን ንግሥት ታሽሉልቱም እንደ ነበረች፣ ወንድ ልጆቻቸውም ሪሙሽ፣ ማኒሽቱሹ፣ ሹ-ኤንሊል (ኢባሩም) እና ኢላባኢሽ-ታካል እንደ ነበሩ ይታወቃል። ከነዚህም ሪሙሽና ማኒሽቱሹ በአካድ ዙፋን ተከተሉ። ሴት ልጃቸው ኤንሄዱአና የመቅደሱ ዋና ሴት ካህን ሆና በራስዋ በኩል ዝነኛ የማሕሌት ጸሐፊ ሆነች። ብዙ የጻፈች መዝሙሮች በሥነ ቅርስ ተገኝተዋል።
ቀዳሚው የኡሩክ ንጉሥ ሉጋል-ዛገ-ሲ |
የአካድና የሱመር ንጉሥ 2077-2064 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ ሪሙሽ |
ቀዳሚው ሉሒሻን (የአዋን ሥርወ መንግሥት) |
የኤላም ገዢ 2070-2064 ዓክልበ. ግድም |
ዋቢ መጽሐፍት
- የሳርጎን ዓመት ስሞች
- ሱመርኛው የሳርጎን ትውፊት (እንግሊዝኛ)
- አሦርኛው የሳርጎን ትውፊት Archived ዲሴምበር 22, 2013 at the Wayback Machine (እንግሊዝኛ)
- "ABC19". Archived from the original on 2006-02-28. በ2013-07-13 የተወሰደ.
- CDLI የሳርጎን ጽላት
- "ABC20". Archived from the original on 2006-02-28. በ2013-07-14 የተወሰደ.
- "Babylon as a Name for Other Cities..." Archived ጁላይ 30, 2012 at the Wayback Machine p. 25-33. (እንግሊዝኛ)
- Joan Goodnick Westenholz, Legends of the Kings of Akkad: the Texts, Text 6, 7.