ብርቱካን (ፍሬ)
ብርቱካን (ወይም ኦሬንጅ) ማለት የዛፍ አይነትም ሆነ በተለይ የዚሁ ዛፍ ፍሬ ማለት ነው። የሌሎች አትክልት ክልስ ሆኖ ከጥንት እንደ ለማ ይታሥባል። እርዝማኔው እስከ 10 ሜትር ድረስ ቢደርስም ዛፉ ትንሽ ይባላል፤ ቡቃያው እሾህ አለበትና ቅጠሎቹ ከ4 እስከ 10 ሳንቲሜትር ድረስ የሚዘረጉ እንደ ጥድም ወገን መቸም የማይረግፉ ናቸው። የፍሬው መጀመርያ ትውልድ በደቡብ-ምሥራቃዊ እስያ በህንደኬ፣ በቬትናም ወይም በደቡብ ቻይና ተገኘ።
ስለ እርሻና ስለጥቅም
የብርቱካን እርሻ በብዙ አገሮች ምጣኔ ሀብት በጣም ታላቅ የንግድ ሥራ ነው። እዚህ ማለት በአሜሪካ፣ በሜዲቴራኔያን አገሮች፣ በሮማንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በቻይና፣ በአውስትራልያም ይከትታል።
ብርቱካን በዓለሙ ውስጥ ሙቅ አየር በሚገኝበት በሰፊ ይበቅላል፤ የብርቱካንም ጣዕም ከጣፋጭ እስከ ኮምጣጣ ድረስ ይለያል። ፍሬው በተለመደ ይላጣል ጥሬም ሆኖ ይበላል፤ አለዚያ ለጭማቂው ይጨመቃል። ወፍራምና መራራ ልጣጩ በተለመደ ወደ ቆሻሻ ይጣላል፤ ነገር ግን በክብደትና በሙቀት አማካኝነት ውሃውን በማስወግድ፣ ለመኖ ሊጠቅም ይችላል። ባንዳንድ የምግብ አሠራር ዘዴ ደግሞ፣ እንደ ጣዕም ወይም እንደ መከሸን ይጨመራል። የልጣጩ አፍአዊው ቆዳ በልዩ መሣርያ በቀጭን ይፋቃልና ይሄ ጣዕሙ ለወጥ የሚወደድ ቅመም ያስገኛል። ከልጣጩ በታች ያለው ነጭና ሥሥ ሽፋን ስለማይረባ ይጣላል። ደግሞ የብርቱካን ዘይት አስታጋሽ መዓዛ ስላለው በሕክምና ይጠቅማል።
ከብርቱካን የተሠራ ሌላ ውጤት እንደሚከተለው ነው፦
- የብርቱካን ጭማቂ በኒው ዮርክ ሸቀጣሸቅጥ ገበያ ላይ የሚነገድ የንግድ ዕቃ ነው። የዓለሙ አንደኛ ብርቱካን ጭማቂ የምታስገኝ ሀገር ብራዚል ስትሆን ሁለተኛዋ ፍሎሪዳ ክፍለሀገር በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ትሆናለች።
- የብርቱካን ዘይት ልጣጩን በመጭመቅ ይሠራል። የዕንጨት ዕቃ መልክ ለማሳምር የጠቅማል፤ ደግሞ የእጅ ማጽዳት ቅባት ያደርጋል። የሚረጭ አይነት በሱቅ ሲሸጥ በጣም ኃይለኛ ማጽደጃ ነውና ለአካባቢ አይጎዳም አይመርዝምም።
- የብርቱካን አበባ የፍሎሪዳ ክፍለሀገር ብሄራዊ ምልክት ቢሆን እንዲሁም በአንዳንድ ባሕል እምነት ውስጥ የመልካም ዕድል ምልክት ሆኛልና ለሙሽሪት እቅፍና ለጌጥ በሠርግ ጊዜ ለረጅም ዘመን ባሕላዊ ነበር። ያበባው ቅጠል ደግሞ መልካም መዓዛ ያለበት ሽቶ ሊሠራ ይችላል።
- የብርቱካን አበባ ማር የሚሠራ የንብ ቀፎ በብርቱካን ደን ውስጥ በማበቡ ጊዜ በማስቀመጥ ነው። ይህ አደራረግ ደግሞ ዘር ያለባቸው ሌሎች አበቦች እንዲራቡ ያደርጋል። የብርቱካን አበባ ማር እጅግ የወደዳል ጣእሙም እንደ ብርቱካን ይመስላልና።
ወገኖች
እንዲያውም ብርቱካን፣ ሎሚ፣ መንደሪን ወዘተ. ሁሉ የአንድ ወገን ናቸው ሁላቸው እርስ በርስ ማራባት ይችላሉ ማለት ነው። በተግባር እነኚህ አይነቶች እንጆሪ ይባላሉ ምክንያቱም ብዙ ዘር እያላቸው ሥጋቸውም ወፍራምና ለስላሳ ሆኖ ከአንድ ዕንቁላል ብቻ ያፈራሉ።
በምድር ላይ ጥቂት አይነቶች ይታረሳሉ። ለምሳሌ ጣፋጭ ብርቱካን የምትባል መጀመርያ በእስፓንያ አገር በቀለች፤ ይቺ ከሁሉ የምትወደድ አይነት ሆናለች። ጣፋጭ ብርቱካን እንደ አየሩ ሁኔታ በልዩ ልዩ መጠኖችና ቀለሞች ትገኛለች፤ አብዛኛው 12 ክፍሎች ውስጥ አሉባቸው።
የሴቪል ብርቱካን በሰፊ የምትታወቅ አሁንም በሜዲቴራኔያን አቅራቢያ በኩል የምትበቀል እጅግ ኮምጣጣ ብርቱካን ናት። ቆዳዋ ወፍራምና ስርጉዳት ያለው ነውና ማርማላታም ሆነ የብርቱካን አረቄ ለመስራት በጣም ትከብራለች። "ይብራ በብርቱካን ወጥ" ሲበሉ ብርቱካን የዚች አይነት ናት።
ባጋጣሚ በብራሲል አገር ውስጥ በ1812 ዓ.ም. በአንድ ገዳም በነበረ የብርቱካን እርሻ ከሆነ ድንገተኛ ለውጥ የተነሣ፤ "የእምብርት ብርቱካን" የሚባል አይነት መጀመርያ ተገኘ። ከዚያ በ1862 ዓ.ም. ነጠላ ቁራጭ ወደ ካሊፎርንያ ተዛዉሮ አዲስ የዓለም አቀፍ ብርቱካን ገበያ የዛኔ ተፈጠረ። ድንገተኛ ለውጡ "መንታ ፍሬ" ያደርጋልና ታናሹ መንታ በታላቁ ውስጥ ተሠውሮ ይገኛል። የእምብርት ብርቱካን ዘር ስለሌለው በእፃዊ ተዋልዶ ይባዛል፤ የፍሬውም መጠን ከጣፋጭ በርቱካን ይበልጣል።
ቫሌንሲያ ወይም ሙርሲያ ብርቱካን በተለይ ለጭማቂ የሚመች ጣፋጭ አይነት ነው። መንደሪን ትመስለዋለች፣ ነገር ግን ይልቁን ትንሽና ጣፋጭ ናት፤ በመጨራሻም፣ "ድፍን ቀይ እምብርት" የተባለው የዚህ አይነት ከነመንታው ለውጥ እንደ እምብርት በርቱካን ነው።
የቃል ታሪክ
በድሮ ጊዜ ፖርቱጋል የምትባል አገር ለምሥራቅ አገሮች የጣፋጭ ብርቱካን ዋና አስገቢ ነበረች። ስለዚህ በብዙ ቋንቋዎች የፍሬው ስም ከዚያው መነሻ ተወስዷል። ለምሳሌ፦
- ዓረብኛ - ቡርቱቃል
- ፋርስ - ፖርተግሐል
- ቱርክ - ፖርታካል
- አዘርኛ - ፖርታጃል
- ዘመናዊ ግሪክ - ፖርቶካሊ
- ሩማንኛ - ፖርቶካላ
- ቡልጋርኛ - ፖርቶካል
- ጂዮርጂያ - ፖርቶቃሊ
ተብሎ ይሰየማል። ባብዛኛው ቋንቋዎች ግን ያለባቸው ቃል ከሳንስክሪት «ናራንጋ» የወጣ ነው፤ በሌሎችም «የቻይና ቱፋህ» (አፕል) ወይም «የወርቅ ቱፋህ» የሚተረጎሙ ቃሎች ለብርቱካን ለማለት የጠቅማቸዋል።