ቆጵሮስ

ቆጵሮስ (ግሪክኛ፦ Κύπρος /ኪፕሮስ/) በሜድትራኒያን ባሕር የምትገኝ ደሴት አገር ናት። ዋና ከተማው ሌፍኮዚያ ነው።

ቆጵሮስ የተባባሪ መንግሥታት አባል ቢሆንም፣ ከአንዱ ሌላ አባል እርሱም ቱርክ (ስለ ስሜን ቆጵሮስ ጉዳይ) ዲፕሎማቲክ ተቀባይነት የለውም።

1966 ዓም የቱርክ ሥራዊት ወረራ ጀምሮ የስሜኑ ክፍሎች በቱርኮች አስተዳደር ሆነዋል። ከክፍሎቹ መካከል ቀጭን የተባባሪ መንግሥታት መሃልገብ ዞን ይገኛል።

ስም

ስሙ ከግሪክኛ Κύπρος (/ኪፕሮስ/፣ ጥንታዊ አጠራር /ኪውፕሮስ/) ደረሰ፣ በምዕራብ አውሮፓ በፊደሉ C ድምጽ ለውጦች ምክንያት፣ የሀገሩ ስም አጠራር በእንግሊዝኛ /ሳይፕረስ/፣ በጣልኛ /ቺፕሮ/፣ በፈረንሳይኛም /ሺፕር/ ሆነ። የግሪኩ ቃል Κύπρος ደግሞ ሂና ማለት ነበር፣ ስያሜው ከተክሉ ወደ አገሩ ወይም ከአገሩ ወደ ተክሉ እንደ ተዛወረ እርግጥኛ አይደለም። እንዲሁም ከግሪኩ /ኪውፓሪሦስ/ «ሰኖባር» ሊሆን ይችላል። ደሤቱ በጥንት ዋና የመዳብ ምንጭ በመሆኑ፣ ሦስተኛ ሀሣብ ከመዳብ ጥንታዊ ስም በማይታወቅ ቋንቋ እንደ ደረሰ ይላል፤ ለምሳሌ በሱመርኛ መዳብ «ዙባር»፣ ነሐስም «ኩባር» ተብሎ ነበር። ያም ሆነ ይህ፣ ደሴቱ ሰፊ የመዳብ ምንጭ ሲሆን፣ የመዳብ (ኮፐር) ስም በሮማይስጥ cuprum /ኩፕሩም/ በእርግጥ ከደሴቱ ስም መጣ።

የአገሩ ጥንታዊ ስም አላሺያ እንደ ነበር ይመስላል፣ ይህም ከያዋን ልጅ ኤሊሳ ስም ጋር ግንኙነት እንዳለው ይታስባል። ዮሴፉስ እንደ ጻፈ ግን አገሩ በያዋን ሌላ ልጅ በኪቲም ስም ተባለ፣ ኪቲዮን የተባለውን ከተማ ይጠቅሳል። እንደገና ከምጽራይም ልጆች መካከል ከፍቶሪም የሚባለው በአንድ አስተሳሰብ ዘንድ በግብጽ መዝገቦች ከሚጠቀሰው ደሴት አገር «ከፍቲው» ጋር አዛምደው የቆጵሮስ ወይም የቀርጤስ ስም ይሆናል ይላሉ። በመጽሐፈ ኩፋሌ የ«ከፍቱር» ወይም በሌላ ቦታ የ«ከማቱሪ» ደሴቶች በአርፋክስድሴም ዕጣ ወጣ ሲባል፣ ይህ ቆጵሮስና ቀርጤስ ወይም «ከፍቶሪም» ማለት እንደ ነበር ይታስባል።




This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.