ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሰማዕት)
ቅዱስ ጊዮርጊስ አባቱ አንስጣቴዎስ (ዘሮንቶስ) ይባላል። እናቱም ቴዎብስታ ትባላለች የዘር ሐረግዋም ከፍልስጥኤም ወገን ነው ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥር ፪ ቀን ፪፻፸፯ ዓም ተወለደ የተወለደባትም ቦታ ቀጰዶቅያ ትባላለች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት | |
---|---|
'በላሊበላ በቤተ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሚገኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግድግዳ ስዕል' | |
ታላቁ ሰማዕት | |
የተወለደው | ጥር ፪ ቀን ፪፻፸፯ ዓ.ም |
የአባት ስም | አንስታቴዎስ (ዘሮንጦስ) |
የእናት ስም | ቴዎብስታ |
የትውልድ ሀገር | ቀጰዶቂያ |
በዓለ ንግሥ | ሚያዚያ ፳፫ ቀን [1] |
ሃይማኖት | ክርስትና |
የሚከበረው | በምሥራቅም በምዕራብም ቤተክርስቲያኖች ሥንክሳር |
ቀጰዶቅያም በትንሹ ምሥራቃዊ እስያ(እንደዛሬ አጠራር መካከለኛው ምሥራቅ)ትገኛለች ከሮም ገናና መንግሥት በፊት በፋርስ መንግሥት ሥር ነበረች ። ጊዮርጊስም የፋርስ ሰማዕት የሚባለው በዚህ ምክኒያት እንደሆነ ይነገራል ይህችኑ ሀገር ግሪኮችና ሮማውያን በቀኝግዛት ይዘዋት እንደ ነበር ታሪክ ያብራራል ። በዚህ አኳኋን አንዳንድ ሰዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን የግሪክ ተወላጅ ነው ሲሉ ሎችም ደግሞ የሮማ ተወላጅ ነው ይላሉ ጥቂቶችም የእንግሊዝ ዜጋ ነው ይላሉ ለዚህ ሁሉ ከአፈ ታሪክ በስተቀር ብዙ ጊዜ ተመራምሮ እስካሁን ድረስ በቂ ማስረጃ አልተገኘም። ከዚህም የተነሳ ጊዮርጊስ የዚህ ሀገር ተወላጅ የዚያኝው ሀገር ዜጋ ነው የሚል አነጋገር ቢሰጥ አያስደንቅም ምክኒያቱም የሥራ ሰውንና ጅግናን ማንም ሰው የሱ ዜጋ እንዲሆን ሰለሚፈልግ ነው ።
ይሁን እንጂ በዚያን ዘመን ወታደርነት ተፈላጊ ሙያ ስለነበር ቅዱስ ጊዮርጊስም ወታደር ሆኖ ብዙ ጀብዱ ፈፅሟል በወጣትነቱም የውትድርናን ሥራ እንደሠራ በግሪክና በኮብትና በሶርያ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተጽፏል ይልቁንም በመጽሐፈ ስንክሳርና በራሱ ገድል ተብራርቶ ይገኛል።ቅዱስ ጊዮርጊስ ለጥቂት ጊዜ በወታደርነት ከሠራ በኋላ የክርስቶስ ወታደር ሆኖ ቤተክርስቲያንን ያገለግል ጀመረ ። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ድረገጾች አንዱ ለማየት እዚህ ላይ ይጫኑ Archived ዲሴምበር 6, 2019 at the Wayback Machine
ቅዱስ ጊዮርጊስ በድዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግሥት
በድዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግስት ስለ ክርስትና ሃይማኖት ብዙ ተጋድሎ አድርጓል። ወንጌልንም አስተምሮ ያላመኑ
ሰዎችን ወደ ክርስትና እምነት መልሷል ገድሉ እንደሚለው ቢሩታይትን የተባለችውን
ልጃገረድ ድራጎን ለተባለው አውሬ ግብር እንድትሆን ቀርባ ሳለች ዘንዶውን በጦር ወግቶ ገድሎ እሷን ከመበላት አድኗታል።
ይህንንም ዘንዶ ሰዎች ሁሉ አምላክ አድርገው ስለሚያመልኩት በተወሰነ ጊዜ አንዳንድ
ከወንድም ከሴትም ወጣት እየመለመሉ ያቀርቡለት ነበር።
አንዳንድ የቤተክርስቲያን ታሪክ ተንታኞች
ግን በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታሪክ አንዲት ልጃገረድን ከድራጎን እንዳዳነ የተመዘገበውን ጽሑፍ ልዩ ትርጉም ሰጥተውታል ። አባባላቸውም በዘመነ ሰማዕታት
፪፻፹ ዓ/ም-፫፻፭ ዓ/ም ድረስ በክርስቲያን
ሴቶች ልጆች ላይ ብዚ ግፍ ይፈፀም ነበር ።
ከዚያም የተነሣ አንድ ግፈኛ መኮንን በአንዲት ልጃገረድ ላይ ግፍ ሊፈፅምባት
ሲሞክር ጊዮርጊስ ደርሶ ገድሎ ልጃገረዲቷን
ከሞት አዳናት።
ይህም ታሪክ በምሳሌያዊ አነጋገር ቀረበ ነገር ግን ከጊዮርጊስ ሥዕል ጋር
የሚታየው ድራጎን በዓለም ላይ የሌለ አውሬ
ነው ተብሎ ተገምቷል በግልጽ አነጋገር ዮሐንስ በራእዩ እንዳየው ዘንዶ ምሳሌያዊ መልክ ነው ማለታቸው ነው ። ይህንን አባባል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ
ሳትሆን የግብፅ የአርመን የሶርያ የግሪክ
አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ይቃወሙታል።
ቅዲስ ጊዮርጊስ ድራጎኑን ከገደለ በኋላሥራው ባገር ሁሉ ታወቀ በዚያም ዘመን ክርስቲያኖች በየቀኑ እየተገደሉ በየሜዳው ይጣሉ ስለነበር በፈረሱ ጭኖ እየወሰደ እንዲቀበሩ ያደርግ ነበር።በሕይወት ያሉትንም እየተዘዋወረ ያጽናናቸውና በእምነታቸው እንዲተጉ ወንጌልን ያስተምራቸው ነበር። በተጭምሪም የግፍ ሞት ከሚፈፀምበት አደባባይ የደከሙትን ሽማግሌዎችንና አሮጊቶችን እንዳይፈጁ በፈረስ ወደ ሌላ ሥፍራ ያሸሻቸው ነበር ፈረሰኛው ጊዮርጊስ የሚሰኘውም በዚህ ምክንያት ነው።
ስለ ክርስትና እምነት የተጻፉት የቤተክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳትንም በየዋሻው መሬት እየቆፈረ ደብቆ በመቅበር ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ አድርጓል በጠቅላላ በተፈጥሮና በትምህርት ችሎታ በእግዚአብሔር ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተመላ ሰው ስለነበር ስለ እውነት ስለ ኢየሱስ ፍቅር ስለ ሰላም ስለ እኩልነት ስለ ፍትህ ተጋድሏል ይህም ሁሉ በቤተክርስቲያን ስጦታዊ ታሪክ ወርቃዊ ስጦታ ታእምራዊ ሰማዕት ተብሏል።በርግጥም ስለ እውነት ስለ ሰላም የሚመስክር ሰው ተአምረኛው ሊያሰኘው ይገባል።
ይህም መንፈሳዊ ተጋድሎው ከ፪፻፷-፫፻፵ ዓ/ም የነበረው የቤተክርስቲያን አባት የሆነው አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ቅዱስ ጊዮርጊስን ብርቱና ጠንካራ ሰማዕት እንደሆነ መስክሯል የአውሳብዮስ መጽሐፍ ፰-፲ ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ዘመን ስለ እምነቱ ስለ ሀገሩ ነፃነት ስለ እኩልነት ስለ ሰላም ስለ ፍትህ ስለ ወንጌል መስፋፋት ስለ ቤተክርስቲያን ዕድገት ታማኝ ምስክርነትን በየአድባባየ እየመሰከረ ለሰባት ዓመታት ያህል እየታሰረ እየተሰቃየ እየተገረፈና እየተወገረ ጽኑ ተጋድሎ ከፈፀም በኋላ የመንፈስ ዐርበኝ እንደመሆኑ መጠን የመከራውን ሸለቆ ተሻግሮ ከሕይወት ወደብ ደርሶ ምእመናን እየተያዙ በሚገደሉበት በዱዲያኖስ ዘመን መንግሥት በ፫፻፫ ዓ/ም ሚያዝያ ፳፫ ቀን ልዳ በሚባለው ሀገር በሰማዕትንት ዐረፈ በዚህም ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ተስማምተውበታል።ስለ ዜና ቅድስናው ከላይ በተገለፀው መሠረት ቅዱስነቱ ወይም ቅድስና ያለ ሥራ ሊሰጥ ባለመቻሉ ከነአውሳቢዮስ ዘመን ጀምሮ የቅዱስ ጊዮርጊስ የሥራ ታሪክ ጥናት ተጀመረ።ቅዱስ የተባለውን ስም ለማግኘት በሥራና በአካሄድ ክርስቶስን መምሰል እንደሱ ሌላውን ማገልገልና ለራስ ሳይሆን ሰለ ሌላው መኖር ያሻል ስለ ሌላው ተላልፎ መሞት መከራን መቀበል መሰቀልንም መሸከም በሰው ፊት መመስከርና ራስን መካድ ያስፈልጋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስም ይህን ሁሉ ተግባር ሠርቶ በመገኘቱ ብዙ ምስክር ተገኝቶለት በ፮ኛው መቶ ዘመን በደቡብ ሶርያ በምትገኘው አድራ ወይም (ይድራስ) በተባለች ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የቤተክርስቲያን አባቶች እውነተኛ ሰማዕትነቱንና ቅድስናውን በጉባኤ አጽድቀው ውሳኔውን ለሕዝብ አስተላልፈዋል።በ፩ሺህ፺፮ ዓ/ም ደግሞ በአንጾኪያ በትደርግው የሃይማኖት ጦርንት በራዕይ እንደታየ ተረጋግጦ ስመ ገናና መሆን ጀመረ ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ደሞ ማርያም ልጇን እየሱስ ክርስቶስን ይዛ በምትታይበት ስዕል ሥር "አክሊለ ፅጌ ማርያም ለጊዮርጊስ ቀፀላ መንግሥቱ አንቲ ሁሉ ታስግዲ ሎቱ ወለኪሰ ይሰግድ ውእቱ" ተብሎ ይጻፋል
ቅዱስ ጊዮርጊስ በእንግሊዝ አገር
ቅዱስ ጊዮርጊስ በእንግሊዝ አገር ስመ ጥሩ ሰማዕት ነው ። "የእንግሊዝ መንግሥት ጠባቂ"በሚል የቅፅል ስም ይጠራል።
ከ፰ኛው መቶ ዓ/ም ጀምሮ በእንግሊዝ አገር ዝነኛ እንደሆነ እንግሊዞች ያምናሉ በ፩ሺህ፷፩ዓ/ም ገድሉ በአንግሎ ሳክሶን ቋንቋ ተተረጎመ በዚሁ ዓ/ም በስሙ ቤተክርስቲያን ታነጸ በ፩ሺ፪፻፳፪ ዓ/ም ደግሞ በኦክስፎርድ በተደረገእ የሲኖዶስ ጉባኤ በዐሉ ከንኡሳን በዐላት ጋር ገብቶ እንዲቆጠር ተወሰነ ። በ፩ሺህ፫፻ ዓ/ም ፫ኛው ኤድዋርድ በነገሠ ጊዜ መደቡ ነጭ የሆነ ቀይ መስቀል ያለበት ባንዲራ ተሠርቶ የተጋዳዩ ጊዮርጊስ ባንዲራ ተባለ ይህም ለምድር ጦርና ለባሕር ኃይል መለያ እንዲሆን ተሰጠ የእንግሊዝ መንግሥት ጠባቂ በሚል እንደገና በ፩ሺህ፬፻፲፭ ዓ/ም በዐሉ ከዐበይት በዐላት ጋር እንዲቆጠር ተወሰነ ። ዛሬም ቢሆን በእንግሊዝ ቤተክርስቲያን የዘውትር የጸሎት መጻሐፍ ላይ የሚገኘውን ኮመንተሪ የበዓላትም ቀን መቁጠሪያ ካላንደር ሚያዚያ ፳፫ ቀን የቅደስ ጊዮርጊስ ዕረፍት መታሰቢያ ዕለት እንደሆነ ያመለክታል ለዕለቱም ተስማሚ የሆነ ምንባብና መዥሙር በዚሁ የጸሎትም መጻሐፋቸው ተዘጋጅቷል ። ይሁን እንጂ አከባበሩ ሥራ ፈቶ በመዋል ሳይሆን ከመንፈሳዊ ሥራቸው ጎን የዕለት ተግባራቸውንም በማከናወን በዐሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብራሉ በዚያም ሆነ በዚህ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእንግሊዝ አገር ታላቅ አክብሮት ያለው ሰማዕት ነው ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በህንፃው አሠራርም ሆነ በውስጣዊ ድርጅቱ መሟላት በካህናት ብዛት ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ገዳማትና አድባራት እጅግ የላቅነው እንዲሁም በኦክስፎርድ በሰሜን አይርላንድና በእስኮትላንድ የሚገኙት ታላላቅ ካቴድራሎች ለቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያነት የተሰየሙ ናቸው።በእንግሊዝ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክብር ከሌሎች ቅዱሳን የላቀና የተወደደ ሆኖ እናገኘዋለን ።
- ከላይ የተገለጸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ የተገኘው:
- ፩ኛ/ ዲክሽነሪ ኦፍ ክርስቲያ ባዮግራፊ ቮልዩም ፪ኛ ከ፭፻፵፭-፮፻፵፰።
- ፪ኛ/ ኢንሳይሎፔድያ ብሪታኒካ ገጽ ፯፻፷፰
- ፫ኛ/ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ዘቤተ ክርስቲያን
- ፬ኛ/ ከሚስተር ዴቪድ እስኪዩት የታሪክ ፕሮፌሰር ማስታወሻ።
- እነዚህ መጻሕፍት ታሪኩን ከማብራራት በቀር ቅዱስ ጊዮርጊስ የእንግሊዝ ዜጋ ነው አይሉም።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ
ቅዱስ ጊዮርጊስ በክርስቲያን አገሮች ሁሉ የታወቀ እንደመሆኑ በኢትዮጵያም ታዋቂ ስመጥር ሰማዕት ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ጽላቱ የገባው ብ፲፫ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ ዐምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት እንደነበር ከክብረ ነገሥት መረዳት ይቻላል ። በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ብዙ ዐመታት የኖሩ አባ ልዑለ ቃል የተባሉ መነኩሴ ከሶርያ ደብረ ይድራስ ከሚባለው ገዳም የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ከገድሉ ጋር አምጥተው ለዐፄ አምደ ጽዮን አስረከቡ ዐፄውም ቤተ ክርስቲያን አሠራለት ገድሉም ከዐረብኛ ወደ ግእዝ ተተርጎመ ። ዐምደ ጽዮንም የጊዮርጊስን ጽላት አስይዞ ከጠላቶቹ ጋር በመግጠም አሥር ታላላቅ ዘመቻዎችን በድል አድርጊንት ተወቷል ። ከአንዳንድ የታሪክ ዘጋቢዎች እንደተገለጸው ዐፄ አምደ ጽዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጄና ረዳቴ ስለሆነ አረመኔዎች ድል ሊያደርጉኝ አይችሉም እያለ በቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጅነትና ረዳትነት አብዝቶ ያምን ነበር።
በዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመንም ቢሆን በጥንታዊ ታሪክ እንደተገለጸው በዶዎሮ ክፍለ ሀገር አርዌ በድላይ የተባለ የአረመኔዎች መሪ የነበረ ብዙ ወታደሮች ሰብስቦ ዘርዓ ያዕቆብን ሊወጋው ተነሥ ። ዓፄ ዘርአ ያዕቆብም የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዞ ሠራዊቱን አስከትቶ ዘመተና ጠላቱን ድል መቶ ተመለሰ ። ይህንንም የዘርዓ ያዕቆብ ጸሐፊ ትእዛዝ የነበረው መርቆርዮስ ከዘርዓ ያዕቆብ ታሪክ ጋር መዝግቦታል ። ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ነገሥታት በሚዝምቱበት ታላላቅ ዠመቻዎች ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ትተው አይንቀሳቀሱም ነበር ። ይህንን እውነት ለማረጋገጥ ቢፈለግ በዐድዋ ላይ ከኢጣልያ ጦር ጋር በተደረገው ውግያ ማለትም የአድዋ ጦርነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ታአምራዊ ተሳትፎ ኢትዮጵያን በዓለም ታሪክ በጦር ኃይል ፲ጊዜ እጥፍ የሚበልጣትን አገር አሸንፋ ታዋቂ የነፃነት አገር እንድትባል ያደረጋትን ታሪክ መመልከት ይበቃል ። ይህም ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክወደ ዐድዋ ሲዘምቱ በአራዳ ገነተ ጽጌ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘውን የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት አስይዘው ዘመቱ ። ጦርነቱም እንደተጀመረ ቅዱስ ጊዮርጊስ የእርዳታ እጁን ዘረጋ በዛም ጊዜ ብዙ የጠላት ሠራዊት አለቀ ። ጠላትም እንደመሰከረው አንድ በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ጅግና ነው የፈጀን ብለዋል በወቅቱ የነበረ አንድ የኢጣልይ ጋዜጠኛ ወደ አገሩ ባስተላለፈው ዘገባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሠልፎ የኢጣሊያን ሠራዊት አርበደበደው የምንዋጋው ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔርም ጋር ሰለሆነ በጦርነት ድል ልንመታ ችለናል ሲል አስተላልፏል ። በዚህም የተነሣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነቱን ፈጥኖ ደራሽነቱን ስለት ሰሚነቱን አማላጅነቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ስለሚያምኑበትና ስለሚወዱት ጽላቱ በተተከለበት ቤተ ክርስቲያኑ በተሠራበት በዓሉ በሚከበርበት ስሙ በሚጠራበት ሥፍራ ሀሉ እየተገኙ በጸሎትና በምስጋና ያስቡታል ፍጡነ ረድኤት ነውና ።
ተጨማሪ መረጃ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (272-295 ዓም) በታሪካዊ ሰነዶች መሠረት በሮሜ መንግሥት በቄሣሩ ዲዮክሌቲያን ዘመን የነበረ አንድ ክርስቲያን ወታደር ነበር። በዚህ ዘመን ክርስትና በሮሜ መንግሥት ሕግጋት ተከለከለ። ግን በሕዝቡ ዘንድ እንዲሁም በወታደሮች ዘንድ ወንጌል እየተስፋፋ ነበር። በ295 ዓም በዲዮክሌቲያን ትዕዛዝ ወታደሮች ሁሉ ኢየሱስን ለመካድ፣ ለአረመኔ ጣኦት ለመሠው፣ ወይም ለመገደል ተገደዱ። ጊዮርጊስ የተወደደ መኮንንና የንጉሥ ወታደር ሲሆን ለንጉሡ ፊት እምቢ አለው። ስለዚህ እጅግ አሰቃዩት፣ ሆኖም እስከ ሞቱ ድረስ ኢየሱስን ከቶ አልካደም። ነገር ግን በዚህ ወቅት ብዙ የዋሆች ወንዶችም ሴቶችም በገሃድ ተሰቃዩና የሰዎች ስሜት ከንጉሦቹ ጨካኝ ሃይማኖት ወደ ክርስትና በጅምላ እየተዛወረ ነበር። ከጥቂት አመታት በሗላ ክርስትና በሕግ ተፈቀደ፤ በመቶ ዘመን ውስጥ ክርስትና ብቻ በሮማ የመንግሥት ሃይማኖት ሆነ።
ከዚህ በኋላ የጊዮርጊስ ስም በክርስቲያኖች ዘንድ በጣም ዘመናዊ ሆነ፤ በክርስትና እስካሁን ብዙ ቀሳውስት እና ምእመናን «ጊዮርጊስ» ተብለዋል። ከዚህ በላይ እንደ ብዙ አገራት አቃቤ በልማድ ይቆጠራል። የክርስቲያኑን ወታደር የጊዮርጊስን ታሪክ ትዝ ሲሉ፣ ከሌሎች ጥንታዊ አፈ ታሪኮች ጋራ ተዛበ፤ ስለዚህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንዶ በመግደል ሳዱላን አዳነ በማለት ጨምረዋልና ይህ አፈ ታሪክ በመላው ዓለም ተሰማ። ዳሩ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚታወቀው በቤይሩት አገር በየተወሰነ ጊዜ ስው የሚገበርለትን ዘንዶ በመግደሉ ነው።
ጊዮርጊስ ዘንዶውን ስለ መግደሉ መጀመርያ የተጻፈው በአንድ ጅዮርጅኛ ጽሁፍ ከ1050 ዓም ገደማ ነበር። እንዲሁም በዚያን ወቅት ጊዮርጊስ ዘንዶውን ሲገድል የሚያሳዩ ምስሎች በክርስቲያናዊ ሥነ ጥበብ በሰፊ ይታዩ ጀመር። ይህም በተለይ ከጅዮርጅያና አናቶሊያ ተስፋፋ። ሆኖም ከ1050 ዓም አስቀድሞ በወጣው ሥነ ጥበብ ዘንድ፣ ጊዮርጊስ ሳይሆን ሌላ በ295 ዓም የተገደለ ክርስቲያን ሰማዕት ቅዱስ ቴዎድሮስ ቲሮ ዘንዶውን እንደ ገደለ የሚል ተመሳሳይ ትውፊት ይታወቅ ነበር። በማኒኪስም ተጽእኖ በኩል፣ በአለም ፍጥረት የዘንዶ ውግያ እንደ ተከሰተ የሚሉ የባቢሎን፣ የግብጽ ወይም የፋርስ አረመኔ እምነቶች ቀርተው ፣ እንደ ተስፋፉ ይታያል, ምዕራባውያን የትንሣኤን ዓለማዊ በዓል የሚያከብሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የፋሲካ ጥንቸል።
- ታሪካቸው በኢትዮጵያ [ሥንክሳር በሚያዝያ ፳፫ የሰማዕታትና ቅዱሳን ታሪክ ውስጥ ይነበባል