ቅዱስ ያሬድ

አባታችን ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ ፭ ቀን በ፭፻፭ ዓ.ም በአክሱም ከተማ ተወለደ፡፡ አባቱ አብዩድ ወይም ይስሐቅ ይባላል እናቱ ክሪስቲና ወይም ታውክልያ ትባላለች። ቅዱስ ያሬድ በተወለደ በ7 ዓመቱ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ገበዝ ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እንዲያሳድገውና እንዲያስተምረው አደራ ሰጠችው፡፡

ቅዱስ ያሬድ
ቅዱስ ያሬድ ዜማ ሲማር
ሊቀ ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድ
ስም ያሬድ
የተወለደበት ቀን ሚያዚያ ፭ ቀን ፭፻፭ ዓ.ም.
የሚታወቅበት ዜማን በፅሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀናበረ
የትውልድ ቦታ አክሱም
ንግሥ ግንቦት ፲፩
የአባት ስም ይሥአቅ (አብዩድ)
የእናት ስም ክሪስቲን(ተውኪልያ)
ሥራው የቤተክህነት ዜማ አቀናባሪ፣ደራሲ፣ፀሐፊ
የሚከበረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
በኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
በተለያዩ አገሮች አስደናቂ ስጦታውን በሚያውቁት ዘንድ

ያሬድ ከአጎቱ ዘንድ መዝሙረ ዳዊት በሚማርበት ጊዜ ስለሚቆጣውና ስለሚገርፈው መታገስ ተስኖት ማይኪራህ ወደምትባል ቦታ ሄዶ ተደበቀ ያም ቦታ የቀዳማዊ ምኒልክ መቃብር ቦታ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ወደ አንዲት ዛፍ ስር ተጠግቶ አርፎ እያለ አንዲት ትል የዛፍ ፍሬ ለመብላት ዛፉ ላይ ለመውጣት ስድስት ጊዜ ሲወጣና ሲወርድ ከቆያ በኃላ በሰባተኛው ከዛፉ ላይ ወጥቶ የዛፉን ፍሬ ሲበላ ተመለከተ፡፡ ቅዱስ ያሬድ የትሉን ተስፋ አለመቁረጥ ከፍተኛ የሆነ ትጋቱን እንዲሁም ወደላይ ለመውጣት ብዙ ጊዜ እየሞከረ ቢወድቅም ከዓላማው ሳይናወጥ ከብዙ ድካምና ጥረት በኃላ ያሰበው እንደተፈጸመለት ተመልክቶ “ሰውነቴ ሆይ ግርፋትን ለምን አትታገሽም፤ መከራንስ ለምን አትቀበይም” ብሎ ሰውነቱን ከገሰጸ በኃላ ወደ መምህሩ ተመልሶ “አባቴ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝ እንደቀድሞ አስተምረኝ” አለው፡፡ መምህሩ ጌዴዋንም ተቀብሎ ያስተምረው ጀመር፡፡

ጥበብና ቅዱስ ያሬድ

ወደ አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን አዘውትሮ እየሄደ ጥበብና እውቀትን የሚገልጽ የጌታዬ እናቱ እመቤቴ ሆይ አይነ ልቦናዬን ያበራልኝ ዘንድ ለምኝልኝ እያለ ይለምን ነበር፡፡ ከዚያም በአንድ ቀን 150 መዝሙረ ዳዊት፣ መኃልየ ነቢያት፣ መኃልየ ሰሎሞን ሌሎችን እና ትርጓሜ መጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳትን አወቀ፡፡ በዚያ ዘመን ድምጽን ከፍ አድርጎ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ዜማ አልነበረም ቀስ ብሎ እንደ ውርድ ንባብ እያዜሙ ያመሰግኑ ነበር እንጂ፡፡ እግዚአብሔርም በያሬድ ቃልና ከፍ ባለ ዜማ መመስገን በወደደ ጊዜ ኅዳር 5 ቀን 527ዓ.ም በኤዶም ገነት በሥላሴ አምሳል ሦስት አእዋፍን ወደ እርሱ ላከ እነሱም በግዕዝ፣ ዕዝል እናበአራራይ ዜማ እንደዚሁ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ ሦስቱ አእዋፍ ቅዱስ ያሬድ በቆመበት ቦታ ፊት ለፊት በአየርላይ ቆመው

መንፈስ ቅዱስ በወፍ ተመስሎ ለቅዱስ ያሬድ ዜማ ሲገልጹለት

“ብፁዕ ያሬድ ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዕት አጥባት እለ ሐፀናከ፤ የተመሰገንክና የተከበርክ ያሬድ ሆይ አንተን የተሸከመች ማህጸን የተመሰገነች ናት አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው” አለችው ቅዱስ ያሬድም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ ተመልክቶ እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ወፎች ከወዴት መጣችሁ አላቸው ከሦስቱ አንዲቱ እንዲህ ስትል ተናገረችው ከኤዶም ገነት ወደ አንተ ተልከን ሲሆን ይኸውም ከሃያ አራቱ ካህነት ሰማይ ማኅሌትን ትማር ዘንድ ልንነግርህ መጣን አሉት፡፡ ከዚያም ቅዱሳን መላእክት በዜማ ወደ ሚያመሰግኑባት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ፡፡ በዚያም መላእክት ሰማያውያንና ምድራውያን ደቂቀ አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔርን በመኅሌት በቅኔ በከፍተኛ ድምጽ ያለማቋረጥ በመንበሩ ዙሪያ ሆነው ሲያመሰግኑት በሰማ ጊዜ ካለበት ስፍራ ተነስቶ እነሱ ወዳ አሉበት ቦታ ሊገባ ወደደ ነገር ግን አልተቻለውም፡፡ ከዚያም በኃላ እነዛ አእዋፎቹ ወደ እርሱ ተመልሰው መጥተው ያሬድ ሆይ “የሰማኸውን አስተውለኸዋል” ብለው ጠየቁት “አላስተዋልሁም” ብሎ መለሰላቸ እንግዲያውስ አዲሱን የእግዚአብሔርን ምስጋና ጥራ እርሱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው አለችው ቅዱስ ያሬድም “ማኅሌትን በዓይነቱ ልቤ መልካምን ነገር አውጥቶ ተናገረ” እያለ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ተማረ፡፡ ቅዱስ ያሬድም የመላእክት ሥርዐታቸውን ዐይቶ፣ ማሕሌታቸውን አጥንቶ ኅዳር 6 ቀን 527 ዓ.ም በጠዋት ሦስት ሰዓት ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል፡፡

ቅዱስ ያሬድና ቤተክርስቲያን

ከዚያም አክሱም ከተማ ወደምትገኝው ወደ ጽዮን ቤተክርስቲያን ገብቶ በዓውደ ምህረቱ ቆሞ ድምጹን ከፍ አድርጎ “ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ ብሎ በልሳነ ግዕዝ አዜመ፡፡ ይህም ማለት ዓለም ሳይፈጠር ለነበረና ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም ለሚኖር ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፤ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም ደብተራ ኦሪትን እንዴት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው ማለት ነው፡፡” ከሰማይ እንደተመለሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣዕመ ዜማውን ያሰማበት ቦታ “ሙራደ ቃል” (የቃል መውረጃ) እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም ዜማው ከሰማይ የወረደ ለመሆኑ እውነተኛ ማስረጃ ነው፡፡ ይህችንም ዜማ “አርያም” አላት፡፡ ይህም ማለት ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘች ማለት ነው፡፡ ይህንንም ዜማ ከፍ አድርጎ በሚያሰማ/ በሚያዜም/ ጊዜ ሰው፣እንስሳና አዕዋፍ ሁሉ እርሱ ወዳለበት ቦታ ተሰብስበው ከጣዕሙ የተነሣ መንፈስን የሚያድሰውን ልቡናን የሚያስደስተውንና አጥንትን የሚያለመልመውን ሰማያዊን ዜማ ይሰማሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ በግእዝ፣ በዕዝልና በዓራራይ ዜማውን እያስማማ እግዚአብሔርን ማመስገኑን ቀጠለ፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል የዜማውን ጣዕም ከሰሙና ከተረዱ በኋላ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን መገልገያና ለሕዝቡ መባረኪያ የሰጣቸው መሆኑን በመገንዘብ ሊቃውንቱንና ካህናቱን “ተቀበሉትና ለቤተ ክርስቲያን መገልገያ ይኹን” ብለው አዘዟቸው።

ቅዱስ ያሬድ ለንጉሡ ለዐፄ ገብረ መስቀል ዜማውን ሲያሰማ

ነገር ግን ካህናቱና ሊቃውንቱ ምን ምልክት ዐይተን እንቀበለው ብለው መለሱላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ይግለጽልን ብለው ከታኅሣሥ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ሰባት ቀን ሱባዔ እንዲያዝ አወጁ፡፡ ታኅሣሥ አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ውሎ ነበርና ከሰኞ እሰከ እሑድ አንድ ሱባዔ ይዘው በየቀኑ የአክሱም ጽዮን ማርያምን ቤተ ክርስቲያን እየዞሩ አራት መቶ እግዚኦታና አርባ አንድ በእንተ ማርያም እያደረሱ ምሕላውን አካሔዱ፡፡ በሰባተኛው ቀን እሑድ ዕለተ ምሕላውን ጨርሰው ሲያሳርጉ ጌታ በዕለተ ዐርብ እንደተሰቀለ ሆኖ በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ ተገለጸ፡፡ ከዚህም አያይዞ ቅዱስ ያሬድ “ዘበመስቀሉ ተቀነወ ወበነቢያት ተሰብከ መላእክት ወሊቃነ መላእክት ሰብሕዎ ኪያሁ ንሰብክ መድኅነ” ብሎ ነገረ መስቀሉን በማውሳት የወልድ ምሳሌ በሆነው በዕዝል ዜማ ዘመረ፡፡ ትርጓሜውም “በነቢያት ትንቢት የተነገረለትና በመስቀሉ ላይ የተቸነከረው ጌታ መላእክትና የመላእክት አለቆች አመሰገኑት፤ እኛም እርሱ መድኃኒት እንደሆነ እንናገራለን” ማለት ነው፡፡ በዚህ በተገለጸው ምስክርነት መሠረት ዜማው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ መሆኑ ታምኖ ከዚያን ዕለት ጀምሮ የቅዱስ ያሬድ ዜማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ መገልገያ ሆነ፡፡

ቤተክርስቲያ በቅዱስ ያሬድ ዜማ ሲሸበሸብ

ከዚህም በተጨማሪ ይህ ቀን ስብከት ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ስብከት መባሉም ቅዱስ ያሬድ ዜማ ማስተማር የጀመረበት ነቢያት ይወርዳል፣ ይወለዳል ብለው የተናገሩት ትንቢት ለመፈጸሙ መታሰቢያ ስለሆነ ነው ይህም ቀን አስከ ታኅሣሥ 13 ታስቦ ይውላል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች

ቅዱስ ያሬድን ብቸኛ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ መስራች አድርጎ ለማየት በቂ ምክንያት አለን ፡፡ እንዲያዉም የግእዝ ስነ ጽሑፍ መስራች ከማለት ይልቅ ኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ መሥራች ልንለዉ ይገባል ፡፡ "ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የግእዝ ስነ ጽሑፍ ፤ 1999 ፤ ገጽ 3" በዚሁ ጥናታቸዉ እንዳብራሩት የግእዝ ስነ ጽሑፍን ለሁለት ልንከፍለዉ እንችላለን ይላሉ ፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱ ፦ አንዱ ክፍል ከባህር ማዶ ተጽፈዉ ወደ ግእዝ የተተረጎሙትን መጻሕፍት ይይዛል ፡፡ ሁለተኛዉ ክፍል በቀጥታ በግእዝ የተደረሱትን ድርሰቶች ያጠቃልላል ፡፡

እነዚህም ፡-የቅዱስ ያሬድ፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጭ ፣ የርቱዐ ሃይማኖት ፣ የአፄ ዘረአ ያዕቆብ ፣ የዐርከ ሥሉስ ፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች የሚቀድም በግእዝ ቋንቋ የተደረሰ ድርሰት እስከ አሁን አለመገኝቱን ጥናቱ ያሳያል ፡፡

ቅዱስ ያሬድ ድርሰቶችን ሲያዘጋጅ ከቅዱሳን መጻሕፍት የወሰዳቸዉን ርእሰ ጉዳዮች በፈርጅ በፈርጁ እየለየ በድርሰት ሥራዎቹ እንደ ፈርጥ ተጠቅሞባቸዋል ፡፡ ብሉያትን ከሐዲሳት፣ከሊቃዉንት እያጣቀሰ ያለምንም ችግር የድርሰት ሥራዉን ሊያከናዉን ችሏል ፡፡ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች መንፈሳዊ ይዘት ያላቸዉ ናቸዉ ፡፡ በድርሰቶቹ የሚታዩት የቃላት አመራረጥ ፣ የዐረፍተ ነገር አወቃቀር ፣ የሚስጥር ፣ የዘይቤ አገላለጥ ቅዱስ ያሬድ ከፍተኛ የስነ-ጽሑፍ ተሰጥኦ እንደነበረዉ ለመረዳት ይቻላል፡፡

በቅዱስ ያሬድ የተደረሱት የዜማ መጻሕፍት አምስት ናቸዉ እነርሱም :

  • ድጓ
  • ጾመድጓ
  • ዝማሬ
  • ምሥዋዕት
  • ምዕራፍ

ናቸዉ፡፡

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.