ሴሶስትሪስ
ሴሶስትሪስ (ግሪክኛ፦ Σέσωστρις) በታሪክ ጸሐፊዎች ሄሮዶቶስ፣ ዲዮዶሮስ ሲኩሉስ፣ ስትራቦንና ማኔጦን የተጠቀሰ የግብጽ ፈርዖን ነበር።
ማኔጦን በ2 ሰኑስረት (ወይም ሰንዎስረት) እና በተከታዩ በ3 ሰኑስረት ፈንታ ለሁለቱ አንድ ስም ብቻ አለው፤ እሱም «ሴሶስትሪስ» ሲሆን ለ፵፰ ዓመታት እንደ ገዛ ይለናል። ፫ ሰኑስረት ቢያንስ በከነዓን እስከ ሴኬም ድረስ በ1884 ዓክልበ. አካባቢ እንደ ዘመተ ይታወቃል።
በሄሮዶቶስ
በሄሮዶቶስ ታሪክ (470 ዓክልበ. ግድም ተጻፈ) ዘንድ፣ ከ«ሞኤሪስ» ቀጥሎ ነገሠ። መጀመርያ በመርከብ ሄዶ በቀይ ባሕር ዳርቻ የኖሩት ሁሉ ተገዥ እንዲሆኑ አደረገ። ከዚያ በኋላ እርሱና ሥራዊቱ እስያን ወርረው ባሸነፉበት ቦታ ሁሉ የጽላት ሐውልት አስቆመ። የአገሩ ኗሪዎች ያለ ምንም ትግል ዕጅ ከሰጡ ግን፣ የሴት ዕቃ የተቀረጸበት ሐውልት ባዚያ ሀገር ያስቆም ነበር ይለናል። ሄሮዶቶስ እራሱ ይህን ምልክት በ«ፓላይስቲና» (የቀድሞው ከነዓን) እና በኢዮንያ (በአናቶሊያ) እንዳየው ይመስክራል። ከጊዜ በኋላ ወደ አውሮጳ ተሻግሮ የእስኩቴስና የጥራክያ ሰዎች ተገዥ እንዲሆኑ አደረገ ይለናል።
ከዚያ ዞሮ ወደ ፋሲስ ወንዝ በኮልቂስ (የአሁኑ ጂዮርጂያ) ደረሰ። በዚያ አገር አንዳንድ ከሥራዊቱ እንደ ሠፈረኞች ሆነው እንደ ተዋቸው ይለናል። ይህንን ለማስረዳት፣ የኮልቂስ ኗሪዎች ከሴሶስትሪስ ሥራዊት ተወለድን የሚል ልማድ እንደ ነበራቸው ይጻፋል። የኮልቂስና የግብጽ ተመሳሳይነት በግዝረት እና የተልባ ጨርቅ በመስራታቸው በኩል ያጠቁማል።
ሴሶስትሪስ ወደ ግብጽ ሊመልስ ሲል ወደ ግብጽ በር ደርሦ ወንድሙ በዚያ ጠብቆት በሽንግላ ሴሶስትሪስንና ከርሱ ጋር የነበሩትን ንግሥቱንና ፮ ልጆቻቸውን ወደ ግብዣ ጠራቸው። ወደ ግብዣው ቤት እንደ ገቡ እሳት በቤቱ ዙሪያ ጨመረ። ሴሶስትሪስና ንግሥቱ ግን ከልጆቻቸው ሁለት እንደ ድልድይ ተጠቀሙና እነዚህ ሁለት ተቃጥለው ቢሞቱም ሌሎቹ እንዲህ ማምለጥ ቻሉ ይለናል።
በወንድሙ ላይ ቂሙን ከበቀለ በኋላ ወደ ግብጽ ያመጡት ምርከኞች ሁሉ ግብጽን በመላው በመስኖዎች እንዲቆፍሩ አስገደደ። ከዚህ በላይ በአይቲዮፒያ ላይ እንደ ገዛ ይጽፋል። ልጁ «ፈሮስ» እንደ ተከተለው ይላል።
በዲዮዶሮስ
በዲዮዶሮስ ታሪክ ዘንድ፣ «ሰሶውሲስ» (Σεσόωσις) ተብሎ ገና ወጣት ሆኖ ፈርዖን ሳይሆን አረቢያንና ሊብያን ተገዥ እንዲሆኑ አደረገ። ወንዶች ሁሉ ሠልፈኞቹ እንዲሆኑ ያስገድ ነበር። ፈርዖን በሆነበት ወቅት ስለ ሴት ልጁ አጢርቲስ ቃል ወይም ንግር ዓለሙን በሙሉ ለማሸነፍ አቀደ። የግብጽ ኖሞችንም ያከፋፈለው እርሱ ነበር ይለናል። ሥራዊቱ 600,000 እግረኞች፣ 24,000 ፈረሰኞችና 27,000 ሠረገሎች ጠቀለለ።
ይህን ሥራዊት ሰብስቦ መጀምርያ አይቲዮፒያን ድል አድርጎ ወደ ግዛቱ ጨመረው። ግብራቸው ቆጲ፣ ወርቅና የዝሆን ጥርስ ሆነ። ከዚያ 400 መርከቦች ወደ ቀይ ባሕር ልኮ እያንዳንዱን ደሴት ወይም ወደብ እስከ ሕንድ ድረስ ያዙ። ይህ ሲሆን እርሱና ሥራዊቱ እስያን በሙሉ እስከ ጋንጅስ ወንዝና እስከ ዶን ወንዝ ያዘ። ሠፈረኞቹን በኮልቂስ የተዋቸው ጊዜ የዛኔ ነበር ይጽፋል። ከዚያ የኪክላደስ ደሴቶች (ግሪክ አገር) እና ጥራክያን ተገዥ አደረጋቸው። በየአገሩ ሓውልት አቁሞ በትግለኞች አገሮች የወንድ ዕቃ፣ በፈሪዎችም አገሮች የሴት ዕቃ ያለበት ጽላት አስቀረጸ። አሕዛብ ሁሉ ከየቦታው ግብራቸውን ወደ ግብጽ እንዲያምጡ አዝዞ ከ፱ ዓመት ዘመቻ በኋላ ወደ ግብጽ ተመለሰና አገሩን አበለጸገ። ከባቢሎን ያመጡት ምርከኞቹ ግን አምጸው የራሳቸውን ግዛት በአባይ ወንዝ አፍ አቆሙ። ፴፫ ዓመታት ከገዛ በኋላ፣ ዓይነ ብርሃኑ ዕውር ስለ ሆነበት ንጉሡ ራሱን እንደ ገደለው ይለናል።