ሪሙሽ
ሪሙሽ ከ2064 እስከ 2056 ዓክልበ. ግድም ድረስ (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) የአካድ ንጉሥ ነበረ። የታላቁ ሳርጎን ልጅና ተከታይ ነበር። እናቱ ምናልባት ንግሥት ታሽሉልቱም ነበረች። የሱመር ነገሥታት ዝርዝር ቅጂዎች ለ7፥ 9 ወይም 15 ዓመታት እንደ ገዛ ቢሉንም፣ በሥነ ቅርስ ከዘመኑ የተገኙት ሰነዶች አንድ የዓመት ስም ብቻ ተገኝቷል፤ እሱም «አዳብ የጠፋበት ዓመት» ይባላል።
በአባቱ ሳርጎን መሞት ሪሙሽ ንጉሥ በሆነበት ወቅት ሳርጎን አሸንፎ የገዛቸው አገራት ሁሉ በአመጽ ተነሡ። ሪሙሽ የኡር ገዥ ካኩ፣ የላጋሽ ገዥ ኪቱሺድ፣ የካዛሉ ገዥ አሻረድ፣ የአዳብ ገዥ መስኪጋላ፣ የዛባላም ገዥ ሉጋል-ጋልዙ ሁላቸውን በዘመቻዎች ማረካቸው፣ በነዚያ ከተሞች ብዙ ሰዎችን ገደለ። የማርሐሺ ገዢ አባልጋማሽና ሻለቃው ሲድጋው ከአዋን ገዥ ኤማህሲኒ ጋር በአመጽ ተነሥተው ከሱስንና ከአዋን መካከል በውግያ ተሸነፉ። አካዳውያን ከኤላምና ከማርሐሺ 30 ምና ወርቅ፣ 3600 ምና ብርና 300 ባርዮቭ ማረኩ። ሪሙሽ አመጸኞቹን በሱመርና በኤላም ቢያሸንፍም፣ ከሐቡር ወንዝ ስሜን ግን ሥልጣኑን ለመስፋፋት አልቻለም። በመጨረሻ በራሱ ሎሌዎች በግድያ ሞቶ ወንድሙ ማኒሽቱሹ እንደ ተከተለው ይመስላል።
ቀዳሚው ታላቁ ሳርጎን |
የአካድ ንጉሥ 2063-2056 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ ማኒሽቱሹ |
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.