ሠርፀ ድንግል

ዓፄ ሠርጸ ድንግል ( 1542 - መስከረም 27, 1590 ) በዙፋን ስማቸው "መለክ ሰገድ" ኢትዮጵያን ከ1555 - 1590 ዓ.ም. የመሩ ንጉሥ ነበሩ። አባታቸው ዓፄ ሚናስ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ እቴጌ አድማስ ሞገስ ነበሩ። ከግራኝ ወረራ ጀምሮ እስከ ዓፄ ሚናስ ዘመን የቀጠለው አለመረጋጋት በኒህ ንጉሥ ዘመን አንጻራዊ እልባት አግኝቷል። ለዚህ ተጠያቂ የሚሆኑ አራት ጉልህ ክስተቶች፡ ፩) በሰሜን የቱርኮች ወረራ በንጉሡ ወታደራዊ ብቃት በመክሸፉ ፪) በደቡብ የባሬንቱ ኦሮሞዎች ሐረርን በመውረራቸው የአዳል ግዛት ኃይል በመዳከሙ እና ስለዚህ ምክንያት ከአዳል ጦርነት በማብቃቱ ፫) የቦረና ኦሮሞዎች ወደ ሸዋ የሚያካሂዱትን ዘመቻ ለጊዜው መግታት በመቻሉ፣ ፬) የአገሪቱን ዋና ከተማ ከመካከለኛው ክፍል ወደ አባይ ምዕራብ በማሻገሩ ነበር[1]። በአጠቃላይ መልኩ ይህ ንጉስ ከሚናስ የተረከበውን ግዛት አስፍቶና አጠናክሮ ለቀጣዩ መሪ ትቶ አልፈዋል። የንግሱ ባለቤት እቴጌ ማርያም ሰናም ለተከታዮቹ ነገሥታት መነሳትም ሆነ መውደቅ ባበረክተችው አስተዋጽኦ በታሪክ ትታወሳለች።

ዓፄ ሠርጸ ድንግል
በ1571 ዓፄ ሠርፀ ድንግል የገነቡት የጉዛራ ቤተ መንግስት፣ በእምፍራዝ፣
በ1571 ዓፄ ሠርፀ ድንግል የገነቡት የጉዛራ ቤተ መንግስት፣ በእምፍራዝ
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ግዛት ከ1555 እስከ 1589 እ.ኤ.አ.
ቀዳሚ ዓፄ ሚናስ
ተከታይ ዓፄ ያዕቆብ
ባለቤት ንግሥት ማርያም ሰና
ሙሉ ስም መልአክ ሰገድ (የዙፋን ስም)
ሥርወ-መንግሥት ሰሎሞን
አባት ዓፄ ሚናስ
እናት አድማስ ሞገሴ
የተወለዱት 1542
የሞቱት 1589
የተቀበሩት መድሀኒ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፤ ሬማ ደሴት
ሀይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና

ቅድመ መለክ ስገድ

በሠርፀ ድንግል የህጻንነት ዘመን የነበረችው አገር ብዙ ውዝግቦችን እምታስተናግድ ነበረች። ከምክንያቶቹ ውስጥ አንደኛው ዓፄ ሚናስ ከፖርቱጋል ካቶሊኮች ጋር አለመስማማቱ ሲሆን ካቶሊኮቹም አንድ ጊዜ ከባህር ንጉስ ይስሐቅ ጋር በማበር ሌላ ጊዜ ባህር ንጉሱ ከቱርኮች ጋር በመተጋገዝ በሚናስ ላይ አመጽና ዘመቻ በመፈጸማቸው ነበር። ሌላው ምክንያት የአዳል ግዛት ኃይሉ እምብዛም ያልተዳከመ ስለነበር በመካከለኛው መንግስት ላይ ጦር የመክፈት ልማዱ አልተገታም ነበር። ሦስተኛው በዘመኑ የአገሪቱ የአስተዳደር ማዕከል የነበረው የሸዋ እና ፈጠገር ክፍሎችን ቦረናዎች መውረር መጀመራችው ነበር። በነዚህ ምክያቶች አገሪቱ በበጋው ወቅት ጦርነት የሚካሄድባት በክረምት ደግሞ ሰፊ ሰራዊት በመያዝ ከጊዜ ወደጊዜ በሚቀያየሩት ዋና ከተሞች የሚሰፈርባት ነበረች[2]

ሠርፀ ድንግል መንገሱ

ዓፄ ሚናስ በ1555 ሲሞቱ ቀጣዩ ንጉስን ለመምረጥ የአገሪቱ መሳፍንቶች በሸዋ ተሰበሰቡ። ምንም እንኳ ሠረፀ ድንግል የሚናስ ታላቁ ልጅ ቢሆንም ብዙ ተቀናቃኞች ነበሩት። ከነዚሁም ውስጥ፣ የዓፄ ልብነ ድንግል እህት የወይዘሮ ሮማነወርቅ ልጅ የነበረው ሐመልማል ዋና ሲሆን ሌሎች እንደ ሐርቦአቤቶ ፋሲል እና ይስሐቅ ያሉ ተገዳዳሪዎች ስብሰባው የተወዛገበ እንዲሆን አድርገውት ነበር። የዚህ ስብሰባ ውጤት የ13 ዓመቱ ሠርፀ ድንግል ንጉስ እንዲሆን ነበር። ሆኖም ሐምልማል ይህን ውጤት ባለመቀበል የጎጃም እና ደምበያ መሳፍንቶችን በማስተባበር በወጣቱ ንጉስ ላይ ዘመቻ ከፍቶ በመጀመሪያ አካባቢ ድል ተቀዳጅቶ ነበር። ይሁንና የቀሳውስቱን እና እንዲሁም እቴጌ ሰብለ ወንጌልን ድጋፍ በማግኘቱ፣ ይህንም ተከትሎ በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመሩ የሄዱ መሳፍንቶችን ከርሱ ጎን በመሰለፋቸው በመጨረሻ ሐመልማልን በጦርነት ለማሸነፍ ቻለ። ጎጃምን ለተሸነፈው ለሐመልማል እንደ ግዛት በመስጠት ሰላም ለማስፈን ቻለ።

የአጎቱ ልጆች ማመጽ

ይህ ከሆነ በኋላ ባህር ንጉስ ይስሃቅ የተባለው ያሁኑ ኤርትራ መሪ በአጼ ሚናስ ዘመን ያመጸ ቢሆንም ልጁ ሲነግስ የልጁን ስልጣን ተቀበለ። ክሁለት አመት በኋል ፋሲል የተባለው ሌላው ያጎቱ ልጅ አመጽ አስነስተውብታል (ምንም እንኳ ሁቱም ቢሸነፉ)።

የቱርኮች ጦርነት፣ የግንቦች መታነጽ ፣ በአክሱም የአክሊል መድፋት

መልሶም በ1569 ከቱርኮች ጋር ባደረገው ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ ቱርኮችን አሸነፈ። ለዚህ መታሰቢያ በእምፍራዝ (ጉዛራ) በ1571 ቤ/መንግስት አሰራ። ወደ ሰሜንም በመዝለቅ በወገራ እና በአይባ ሌሎች ቤ/መንግስቶችን አሰርቷል። የኪዳነ ምህርት ቤ/ክርስቲያንም እንዲሁ።

ከዚያም ባህር ንጉስ ይስሐቅኦቶማን ቱርኮችና በአዳል ሰራዊት ታግዞ አመጽ ማስነሳቱ አልቀረም። በዚህ ጊዜ ንጉሱ ወደ ትግራይ በመዝመት በ1578 ባህረ ነጋሹንና (በአዲ ቆሮ) አባሪ ኦቶማኑን ኦዝደሚር ፓሻንና የአዳል መሪ የነበረውን ሱልጣን መሃመድ አራተኛ (በተምቤን) ጦርነት አሸንፎ ገደላቸው። በድባርዋ (የድሮው ኤርትራ ዋና ከተማ) የነበሩት ቱርኮችም ያለምንም ተኩስ እጃቸውን ሰጡ። በዚያውም ሰርጸ ድንግል በአክሱም ስርዓተ ተክሊሉን ፈጸመ (ይህ እንግዲህ ከዘርዓ ያዕቆብ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው)፣ መልአክ ሰገድ የሚለውንም ስም ያገኘው በዚህ ጊዜ ነበር። ከ10 አመት በሁዋላ፣ በ1588 ኦቶማን ቱርኮች፣ ከተባረሩበት ድባርዋ መልሰው ሊቆጣጠሩ ሲሞክሩ በመሸነፋቸው አርቂቆ ላይ የነበረውን ግዛታቸውን ሰርጸ ድንግል አፈረሰባቸው። በዚህ ምክንያት የቱርኩ መሪ ፓሻ በወርቅ ያጌጠ ፈረስ እስከ ሳዱላው በመላክ ከንጉሱ ዘንድ ሰላም እንደሚሻ አስታወቀ። [3]

ቱርኮችን በ1569 ድል ካድረጉ በኋላ ለመታሰቢያነት በእምፍራዝጎንደር በ1571 ዓፄ ሠርፀ ድንግል የገነቡት የጉዛራ ቤተ መንግስት

ሌሎች ዘመቻዎች እና ሰላም

ሰርጸ ድንግል የኖረበት ዘመን ከግራኝ አህመድ ወረራ ጥቂት ዘመን አሳልፎ ስለነበር የህዝቦች ፍልሰት በዚሁ ዘመን ይታይ ነበር። የኦሮሞን ወደ ሰሜን ወረራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋፈጠ ንጉስ ይሄው ሰርጸ ድንግል ነው። በዚሁ ዘመን የኦሮሞወች ጥንካሬ ከማየሉ የተነሳ ኑር ኢብን ሙጃሂድ የተሰኘውን የግራኝን ምትክ በመግደል ሐረርን ወረው ነበር። ቀጥሎም ወደሰሜን በመዝመት ሰርጸ ድንግል በነገሰ በ10ኛው አመት ዝዋይ ሃይቅ አካባቢ ከንጉሱ ሰራዊት ጋር ተጋጭተው ተሸነፉ። ከዚህ በኋላ ንጉሱ በኦሮሞወች ቡድኖች ላይ በ1578 እና በ1588 ዘምቷል።

በ1580 እና 85 ደግሞ በቤተ እስራኤል (ፈላሾች) ቡድኖች ላይ ዘምቷአል። አገው ላይም በ1581 እና 85፣ ጋምቦ ላይ በ 1590 እናም ሱዳን ውስጥ በሻንቅላ ላይ አድርጓል። እንራያ ደግሞ ሁለት ጊዜ በ 1586 እና 97 ጦርነት በመክፍት ህዝቡን ከነመሪያቸው ክርስቲያን አደርገ። ስለመጨረሻው የ1597 ዓ.ም. ዘመቻው የንጉሱ ዜና-መዋዕል [4] እንዲህ ሲል ያትታል፡

መነኮሳት ተሰብስበው ንጉሱ ወደዳሞት ጦር ሜዳ እንዳይሄድ ለመኑት፣ ንጉሱ ግን ልቡ እንደደነደነ ስለተገነዘቡ በተወሰነ ወንዝ [አሳ የሚበዛበት የገሊላ ወንዝ ] ውስጥ የሚገኝን አሳ እንዳይበላ አጥብቀው አስጠነቀቁት። እሱ ግን የተባለውን ቸል በማለት ባስጠነቀቁት ወንዝ ሲያልፍ ከዚይ ወንዝ የወጣን አሳ በላ። ሳይዘገይም በጸና ታመመና ሞተ። [5]

በሞተም ጊዜ ሬማ ደሴት፣ ጣና ሃይቅመድሃኔ አለም ቤ/ክርስቲያን ተቀበረ። [6]

የሰርጸ ድንግል መንግስት ረጅምና ከመጀመሪያው ጀምሮ ብዙ ጦርነት የበዛበት ቢሆንም ንጉሱ ለልጁ ያዕቆብ ያስረከበው ግዛት ግን ሰላማዊና ያልተከፋፈለ ታላቅ ሃገር ነበር። [7]

የስልጣን ሽግግር

በጥንቱ ኢትዮጵያ ታሪክ የስልጣን ሽግግር ብዙ ችግር የተሞላበት ነበር። የሰርጸ ድንግል ስርዓትም ከዚህ አላመለጠም። አጼ ሰርጸ ድንግል ከህጋዊ ባለቤታቸው ንግስት ማርያም ሰና ሴት ልጆችን እንጂ ወንድ ልጅ አላገኙም። ሐረግዋ ከተባለች የቤተ እስራኤል (ፈላሻ) ቅምጣቸው ግን ያዕቆብ የሚባል ወንድ ልጅ ነበራቸው። ይሁንና ልጅ አባቱ በሞተ ጊዜ ገና የ7 አመት ህጻን ነበር። በዚህ ምክንያት የሰርጸ ድንግል ወንድም ልጅ የነበረው ዘድንግል ስልጣን ላይ ይወጣል የሚል ግምት በመላ ሃገሪቱ ተንሰራፍቶ ነበር። ነገር ግን ንግስት ማርያም ሰና ከልጆቻ ባለቤቶች ራስ አትናትዮስ የጎንደር መሪ እና ራስ ክፍለ ዋህድ የትግራይ መሪ ጋር በመሆን ህጻኑን የእንጀራ ልጇን ያዕቆብን በራስ አትናቲዮስ ሞግዚትነት የንጉሰ ነገስትነቱን ስልጣን እንዲወርስ አደረገች።

ማጣቀሻወች

  1. Roland Oliver and Anthony Atmore, Medieval Africa, 1250-1800 (Cambridge, England: Cambridge University Press, 2001), 129-130, http://www.questia.com/read/105180324.
  2. Roland Oliver and Anthony Atmore, Medieval Africa, 1250-1800 (Cambridge, England: Cambridge University Press, 2001), 129-130, http://www.questia.com/read/105180324.
  3. Hubert Jules Deschamps,(sous la direction). Histoire générale de l'Afrique noire de Madagascar et de ses archipels Tome I : Des origines à 1800. Page 410-411 P.U.F Paris (1970);
  4. በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኸርስት የተተረጎመ "The Ethiopian Royal Chronicles. Addis Ababa: Oxford University Press, 1967.
  5. G.W.B. Huntingford, Historical Geography of Ethiopia (London: British Academy, 1989), p.149.
  6. R.E. Cheesman, "Lake Tana and Its Islands", Geographical Journal, 85 (1935), p. 498
  7. Hubert Jules Deschamps,(sous la direction). Histoire générale de l'Afrique noire de Madagascar et de ses archipels Tome I : Des origines à 1800. Page 410-411 P.U.F Paris (1970);

ዋቢ መጻሕፍት



This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.