ምድያም
ምድያም (ዕብራይስጥ፦ מִדְיָן /ሚድያን/፣ አረብኛ፦ مدين /ማድያን/፣ ግሪክኛ፦ Μαδιάμ /ማዲያም/) በመጽሐፍ ቅዱስና በቁርዓን የሚጠቀስ አገርና ሕዝብ ነው። በአብዛኛው ሊቃውንት ዘንድ የምድያም ሥፍራ «በስሜን-ምዕራብ አረባዊ ልሳነ ምድር፣ በአቀባ ወሽመጥ ምሥራቅ ዳር፣ በቀይ ባሕር ላይ» ተገኘ።[1] ፕቶሎመይ ደግሞ «ሞዲያና» የተባለ ሠፈር በዚህ አካባቢ አለው።
የምድያም ሰዎች ከአብርሃምና ኬጡራ ልጅ ምድያም ተወለዱ (ዘፍ. ፳፭፡፪)። በዘፍ. ፴፯፡፳፰ የምድያም ልጆች ዮሴፍን በጉድጓድ አገኝተውት ለእስማኤላውያንና ወደ ግብጽ ባርነት ሸጡት።
ከዚህ በኋላ ሙሴ ከግብጽ ፈርዖን በሸሸ ጊዜ በምድያም ካህን ራጉኤል ወይም ዮቶር ቤተሠብ አድሮ ልጁን ሲፓራ አገባት (ዘጸአት ፪፡፲፭-፫፡፩)።
የእስራኤል ነገዶች ወደ ከነዓን ተመርተው በቀረቡበት ጊዜ ምድያም የሞአብ ጎረቤትና ባለሟል ነበር፤ አንድላይ በእስራኤል ላይ ተመካከሩ (ዘኊልቊ ፳፪፡፬-፯)። የሞአብና የምድያም ሴቶች የእስራኤላውያን ወንዶች በማዳራት ወደ አረመኔ ጣኦታቸው እንዲሰግዱ ያባባሏቸው ጀመር። በዚህ ወቅት የምድያም አለቃ ሱር ነበር፤ የራሱም ሴት ልጅ ከስቢና የእስራኤል ሰው ዘንበሪ አንድላይ በድንኳኑ በፊንሐስ ጦር በሆዳቸው ተገደሉ። ምድያም የእስራኤልን ልጆች በዚህ አይነት ሽንግላ ስላስጨነቃቸው እግዚአብሔር ምድያምን እንዲያጥፉት አዘዘ (ዘኊልቊ ፳፭)። ይህ ዘመቻ በምዕራፍ ፴፩ ይገለጻል፤ ሱር እና አራት ሌሎች የምድያም አለቆች (ኤዊ፣ ሮቆም፣ ሑር እና ሪባ) በሠይፍ ተገደሉ። ከ፴፪ ሺህ ድንግል ሴቶች በቀር ወገናቸው ሁሉ ተገደለ፣ የተማረኩት ድንግል ሴቶች ለእስራኤላውያን ተጨመሩ።
ሆኖም የምድያም ሕዝብ ሁሉ ያንጊዜ እንደ ጠፉ አይመስልም። በመጽሐፈ መሳፍንት ፮፣ ፯፣ ፰ ዘንድ፣ እስራኤላውያን ለ፯ አመታት ለምድያም ተገዙ። የምድያምና የአማሌቅ ሰዎች ሰብሉን ሁሉ ይቀሙ ነበር። ጌዴዎን ግን አሸነፋቸው፣ የምድያም መኳንንት ሔሬብና ዜብ ተገደሉ። ከዚያ ጌዴዎን የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልና ስልማና እስከ ቀርቀር ድረስ አሳደዳቸውና ገደላቸው።
በተጨማሪ በ1 ነገሥታት 11:17-18 ዘንድ የኤዶምያስ ሰው ሃዳድ ከኤዶምያስ ወደ ግብጽ በሸሸበት ወቅት፣ በምድያምና በፋራን አገሮች እንዳለፈ ይነግራል።
በአዋልድ መጻሕፍት በመጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ክፉው ንጉሥ ጺሩጻይዳን የሞአብና የምድያም ንጉሥ ሲለው በመግቢያው ግን በ«ምድያም» ፋንታ «ሜዶናውያን» አለው። እንዲያውም ጺሩጻይዳን የታሪካዊ የሰሌውቅያ ንጉሥ አንጥያኮስ አፊፋኖስ መጠሪያ እንደ ነበር ይመስላል።
በቁርዓን
በቁርዓን ምድያም (ማድያን) ፲ ጊዜ ይጠቀሳል። በሱራ ፯፣ የማድያን ሰዎች ሀሣዊ ሚዛንና መለኪያ ስለ ተጠቀሙ፣ በመንገድም ለቅሚያ ስላደፈጡ፣ ነብዩ ሹዓይብ ንሥሐ እንዲገቡ የሚል ተግሳጽ አቀረበላቸው። (በአንዳንድ አስተያየት ይህ «ሹዓይብ»ና የምድያም ካህን ዮቶር ወይም ራጉኤል መታወቂያ አንድ ነው።) ሹዓይብን ስላልሰሙ ግን የማድያን ሰዎች በምድር መንቀጥቀጥ ጠፉ ይላል።
ዋቢ ምንጮች
- Dever, William G. Who were the Early Israelites and Where Did They Come From? William B Eerdmans Publishing Co (24 May 2006) ISBN 978-0-8028-4416-3 p.34
- Clines, David and John Sawyer, eds. "Midian, Moab and Edom: The History and Archaeology of Late Bronze and Iron Age Jordan and North-West Arabia". Journal for the Study of the Old Testament, Supplement Series, No. 24. Sheffield Academic Press, 1983.
- Singer, Isidore and M. Seligsohn. "Midian and Midianites". Jewish Encyclopedia. Funk and Wagnalls, 1901–1906, which cites to:
- Archaeology of Timna
- Another Timna archaeology site
- Richard Burton's account of his travels in "The Land of Midian" Archived ጁላይ 21, 2005 at the Wayback Machine