ምክር ቤታዊ አገባብ
ምክር ቤታዊ አገባብ ወይም ፓርላሜንታዊ ሂደት ማለት በማናቸውም ምክር ቤት ወይም በተመሳሳይ በድርጅታዊ ስብሰባ ውስጥ በዘመናት በተደረጀው ልማድ መሠረት የሚጠቀሙት ቅደም-ተከተል ደንቦች ናቸው።
በዝርዝሩ ደንቦቹ እንደየድርጅቱ ሊለዩ ይችላሉ። መንግስት ላልሆኑ ድርጅቶች፣ በዋነኝነት የሚከተለው የሮበርት ቅደም-ተከተል ደንቦች የተባለው መምሪያ መጽሐፍ ነው። የአሜሪካ ብሔራዊ ምክር ቤቶች የጄፈርሶን ፓርላሜንታዊ መምሪያ ይከተላሉ። የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ የእርስክን መይ ፓላሜንታዊ ሂደት መምሪያ ይከተላል። ከአሜሪካ 99 ክፍላገራዊ ምክር ቤቶች[1]፣ 70 የመይሶን ምክር ቤታዊ አገባብ መምሪያ ሲከተሉ፣ 13 በጄፈርሶን መምሪያ፣ 4 በሮበርት መምሪያ ይገዛሉ። ከነዚህ ዋናዎቹ ፓርላሜንታዊ መምሪያዎች ሌሎች አሉ። ብዙ ጊዜ ድርጅቶች ከነዚህ መሠረቶች ለራሳቸው የቅደም-ተከተል ሂደት ደንቦች ለማስተካከል በምርጫ ይስማማሉ።
በፓርላሜንታዊ ሂደት አንድ ማዕከለኛ መርህ «ውሳኔ በድምጽ ብዛት ይወሰናል» የሚል ነው። ከስብሰባው አካላት ወይም «መቀመጫዎች» መካከል፣ አንዱ አባል በተራው («ወለል»ን ሲይዝ) ሃሣቡን ለ«ሊቀ ወምበር» ማቅረብ ይችላል። ሀሣቡ በተለይ ለቁርጥ ሀሣብ እንዲሆን ከሆነ፣ በጽሑፍም ይቀርባል። በልማድ፣ ለሀሣቡ በቂ ትኩረት እንዳለ ለማሳየት፣ ሁለተኛ አባል «ሃሣቡን እደግማለሁ» ማለት አለበት። ከዚያ በቅደም-ተከተሉ ሲነሣ የተገኙት አባላቱ ሁሉ በተራቸው ስለ ሀሣቡ አስተያየት፣ ምክርና ክርክር ውይይት ያደርጋሉ። የሀሣቡን ረቂቅ ጽሑፍ ቃላት ለመቀይር በንዑስ-ሀሣብ የሚፈልጉ ሊኖሩ ይቻላል። አባላቱ በዋና ሀሣብ ሳይወስኑ መጀመርያ ስለዚያው ንዑስ-ሀሣብ ወይም ቃላት ለውጥ መወሰን አለባቸው።
ምርጫው በድምጽ ብዛት ሲባል፣ ይህ ለቀላል ጥያቄ በውነት በድምጽ ብዛት «አዎ» ወይም «አይ» በመጮህ ሊደረግ ይችላል። ስምምነት መኖሩ ካልመሰለ፣ እያንዳንዱ አባል በየተራው «አዎ» ወይም «አይ» በመጮህ፣ በጽሑፍ ምርጫ፣ በምስጢራዊ (የአምራጮች መታወቂያ በማይገለጽበት) ቆጠራ ወይም በልዩ ልዩ ዘዴዎች ሊቆጠር ይቻላል። በድምጽ ብዛት ሲባል ደግሞ፣ ያነሱትን ወገን መብቶች ለሚነካው ጥያቄ ለምሳሌ «ውይይቱን ሁሉ ለማስጨርስና ቀጥታ ወደ ምርጫው ለማለፍ» ወይም አባልን በቅጣት ለማስወጣት ቢሆን፣ ከ50% በላይ ድጋፍ፣ ብዙ ጊዜ 2/3 ወይም 3/4 ድጋፍ ማስፈለጉ ሊደረግ ይችላል።
በረቂቅ ሀሣብ ብዙ ጊዜ መቅደም አንቀጾች በ«Whereas» /ወራዝ/ ጀምረው የሀሣቡን መሠረታዊ ምክንያቶች ይዘርዝራሉ። በእንግሊዝኛ የ«Whereas:» ትርጉም «እንዲህ በመሆኑ» ማለት ያህል ነው። የሚከተሉ አንቀጾች የቀረበው ሀሳብ ቁርጥ እንቅስቃሴዎች ናቸው፣ በዘልማድም እነዚህ አንቀጾች «(be it) Resolved» («ይወሰን») በሚለው ቃል ይጀመራሉ። ስለዚህ የረቂቅ ሀሣብ መዋቅር እንዲህ ሊመስል ይችላል፦
- Whereas (ምክንያት ሀ)፣
- Whereas (ምክንያት ለ)፣
- Whereas (ምክንያት ሐ)፣ therefore (ስለዚህ)፣
- Resolved፣ (እንቅስቃሴ 1)
- Resolved፣ (እንቅስቃሴ 2)
- Resolved፣ (እንቅስቃሴ 3)
- ነብራስካ አንድ ምክር ቤት አለው፣ ሌሎቹ 49 ክፍላገራት ሁለት፣ = 99።