ሙሴ ቀስተኛ

ሙሴ ቀስተኛ (ሴባስቲያኖ ካስታኛ)ጣልያንኛ፡ Sebastiano Castagna) ይሄ ሰው በአድዋ ጦርነትጣልያን መንግሥት አገራችንን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመግዛት ከገቡት ወታደሮች አንዱ ሲሆን፣ ለወረራ የመጣው የጠላት ኃይል በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ እና በሠራዊታቸው ቆራጥነት አድዋ ላይ ድል ሲሆን ተማርኮ የቀረና እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖር ኢጣልያዊ ነው።

ሰላዩ ሙሴ ቀስተኛ

ሙሴ ቀስተኛ በ፲፰፻፷ ዓ/ም በሲሲሊ ደሴት አይዶኔ በሚባል ሥፍራ ተወለደ። ስለልጅነት ዘመኖቹ እና በወጣትነቱም የጣልያንን የጦር ሠራዊት እንዴት እና ለምን እንደተቆራኘ መቼ፣ ከማን ሠራዊት ጋር፣ የትኛው ወደብ ላይ ኢትዮጵያ ላይ ለመዝመት እንደመጣ በእርግጠኛነት ባይታወቅም፤ ድሉ የኢትዮጵያ ሆኖ ሙሴ ቀስተኛ በምርኮኛነት በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ሠራዊት እጅ ወደቀ። ከተማረከም በኋላ በፈቃዳቸው እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀሩት ብዙ ጣልያኖች አንዱ እንደነበረና በተግባረ ዕድ ሞያው ታዋቂነትን አትርፎ በምህንድስና ተግባራት እንደተሰማራና ኢትዮጵያም ውስጥ እስከ ሁለተኛው የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ድረስ ኖሯል። በወረራውም ጊዜ የጣልያንን ጦር ዓለቆች በሰላይነት እንዳገለገላቸውና በመጨረሻም በአንድ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ አርበኛ እጅ ሕይወቱን እንዳጣ ስለእሱ ከተጻፉ ጥቂት ታሪካዊ መሥመሮች ላይ እንገነዘባለን።

ይሄ ሰው በአገራችን የታሪክ ዘገባዎች ላይ፣ ምናልባትም በታሪካችን ላይ በተጫወተው ሚና ረገድ በቂም ባይሆንም፣ ‘ብቅ፣ ጥልቅ’ እያለ ሲመዘገብ እናገኘዋለን። ስለዚህ ሰው አሟሟት ፀሐፊው በልጅነት ዘመን ያጠናው በመሆኑ ስለሰውዬው ማንነት እና አመጣጥ ለመመርመር ላደረገው ጥረት መነሻ ነው።

ከአድዋ ድል መልስ

ፔጎሎቲ የሚባል ጸሐፊ “ኢጣልያዊው በንጉሥ ምኒልክ ቤተ መንግሥት” (“Un Italiano alla Corte di Menelik,” Storia Illustrata 148 (March 1970): 79-85.) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ሙሴ ቀስተኛ በፋሽሽት ኢጣልያ ሁለተኛ የሙከራ ጊዜ ፣ በአድዋ ጦርነት ላይ የተሳተፈ አዛውንት እንደነበረና አዲስ አበባ ላይ በተግባረ ዕድ ችሎታው በዳግማዊ ምኒልክ እንዲሁም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተወዳጅነትን እንዳፈራ ይዘግብና ለጥቆም በ ‘ሕዝብ ሥራ ሚኒስቴር’ ውስጥ ዲሬክቶር ሆኖ ይሠራ እንደነበር፣ በተለይም የራስ ደስታ ዳምጠውን አክስት ካገባ በኋላ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ምን ያህል አክብሮት እንዳገኘ ይነግረናል። [1] በትውልድ አገሩ አይዶኔ ደግሞ ስለእሱ የታተመ ጽሑፍ ላይ አንጀላ ሪታ ፓሌርሞ ከዚሁ ከወይዘሮ በላይነሽ ጋብቻ ማሪያ እና ጁሴፒና የተባሉ ሁለት ሴት ልጆች እንደተወለዱለት ታበሥራለች። [2]

‘የባሕላዊ ቅርስ ሽግግር’ በካዛንችስ፣ አዲስ አበባ የታሪካዊ ቤት አርዕያዊ ጥገና’ (እንግሊዝኛ “Cultural Heritage Promotion” An exemplary restoration of a historic building in Kasainchis, Addis Abeba, Ethiopia (Addis Abeba November 2005) በሚል ዕትም ላይ በሠፊው፤- በአድዋ ጦርነት ተማርከው ወደ አዲስ አበባ የመጡት የጣልያን ወጥቶ አደሮች አብዛኞቹ በግንባታ እና የመንገድ ሥራ መስክ ተሰማርተው እንደነበር ይገልጽና ሙሴ ቀስተኛም ከነዚህ አንዱ እንደነበር ያረጋግጥልናል።

ይኼው ዕትም ሙሴ ቀስተኛ የካቲት ፳፫ ቀን ፲፱፻፬ የተመረቀውን

ገነተ ጽጌ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ዕቅድ የነደፈው መሐንዲስ እንደነበረ እና በ፲፱፻፴ ዓ/ም የታተመው “በምሥራቅ አፍሪቃ የጣልያን ግዛት” መምሪያ (ጣልያንኛ፣ guida del’Africa Orientale Italiana, Milano, Consociazione Turistica Italiana, 1938) ሕንጻውን በማሞገስ እንደተነተነው አስቀምጦታል።[3] ሆኖም የቤተ ክርስቲያኑን ዕቅድ የነደፈው መሐንዲስ የግሪክ ተወላጁ እንደነበረና ሙሴ ቀስተኛ የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ ተኮናትሮ የሠራ እንደሆነ ሌሎች ታሪካዊ ዘገባዎች ይገልጻሉ። ቀስተኛ ከዚህም ሕንጻ ሌላ በ፲፱፻፪ ዓ/ም የተመረቀውን ዘመናዊ የ'አቢሲኒያ ባንክ' ሕንጻ ኢጣልያዊው መሐንዲስ ቫውዴቶ (Vaudetto) ባዘጋጀው ንድፍ መሠረት ሙሴ ቀስተኛ እንደሠራው ሪቻርድ ፓንክኸርስት ዘግቦታል።

የፋሽሽት ወረራ ዘመን

ጥቅምት ወር ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ወረራው ሲጀመር የኢትዮጵያ ወጥቶ አደሮች እና አርበኞች የጠላትን ጦር ለመከላከል በሰሜን፤ በደቡብ፤ በምሥራቅ እና በምዕራብ ግንባሮች ተሠማርተው የተቻላቸውን ያህል ተቋቋሙ። ሆኖም የፋሽሽት ሠራዊት በዘመናዊ መሣሪያ እና የመርዝ ቦንብ አይሎባቸው በግንባር ለግንባር ግጥሚያ ይሸነፉና ንጉሠ ነገሥቱም በግንቦት ወር ተሰደው ወደ እንግሊዝ አገር ሄዱ። አገሪቷም በጣልያን ቁጥጥር ስር አደረች። የግራዚያኒ ሠራዊት ግን በደቡብ ግንባር ራስ ደስታ ዳምጠው እና ደጃዝማች በየነ መርዕድ ፤ በምዕራብ የባላምባራስ ገረሱ ዱኪ አርበኞች በሰሜን ሸዋ ደግሞ የራስ አበበ አረጋይ ሠራዊት አልበገር ብለው አስቸግረውት ቆዩ።

ግራዚያኒ በድርድር እነኚህን መሪዎች ለማስገባት ባደረገው ጥረት መልእክተኛና ሰላይ አድርጎ የመረጠው የኢትዮጵያውያንን ባህል ለ አርባ ዓመታት ያጠናውንንና የራስ ደስታን አክስት ያገባውን ይሄንኑ ሙሴ ቀስተኛን ነበር።

በዚህ ዓላማ መጀመሪያ የተላከውም ወደ ራስ ደስታ ዳምጠው ሲሆን፣ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም በባሌ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ቡላንቾ (አርበጎና) የሚባል ሥፍራ ላይ ሁለቱ ተገናኝተው ለሁለት ሰዓት ያህል ተወያዩ።[4] ቀስተኛ ከዚህ ድርድር በኋላ እንደገመተው፣ ራስ ደስታ እጃቸውን እንደሚሰጡና የጭፍሮቻቸውን፣ በተለይም የጣልያንን ወገን ከድተው ከሳቸው ጦር ጋር የተቀላቀሉትን ኤርትራውያን እስከሚያሳምኑ ድረስ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል በሚል ግምገማ ነው። ራስ ደስታ የካቲት ፲፭ ቀን ቡታጅራ አካባቢ ላይ በትግራይ ተውላጅ ደጃዝማች ተክሉ መሸሻ ተይዘው በጠላት እጅ ወዲያው ተረሽነው ሞቱ።

የሙሴ ቀስተኛ ስም በታሪካችን ዘገባ ላይ እንደገና ብቅ የሚለው በ ግንቦት ወር ፲፱፻፴ ዓ/ም ላይ ሲሆን አሁንም እንደቀድሞው የግራዚያኒ መልእክተኛና ሰላይ በመሆን ለዕርቅ ስምምነት ከ ራስ አበበ አረጋይ ጋር ግንደበረት ላይ ተገናኝቶ ለግራዚያኒ አርበኞቹ ለመስማማት የሚፈልጉ መሆናቸውን አስታወቀ። የሠራዊቱንም ብዛት በተመለከተ የስለላ ዘገባውን ለግራዚያኒ አስታውቆ በተከተለው የፋሽሽት ጥቃት ብዙ ኢትዮጵያውያን አርበኞት አልቀዋል።

ሦስተኛውና የመጨረሻው ተልዕኮው በ ጥቅምት ወር ፲፱፻፴፩ ዓ/ም ሲሆን በዳቄሮ በሚባል ሥፍራ ላይ ወደነበሩት ባላምባራስ (በኋላ ደጃዝማች) ገረሱ ዱኪ ነበር። እዚህ ሥፍራ ላይ ከሦስት ባላባቶች ጋራ የመጣው ቀስተኛ የሰባ አንድ ዓመት ሽማግሌ፣ ነጭ ጸጉር እና ባለሙሉ ጺማም ሲሆን አርበኞቹን ሰብስቦ በተጣራ አማርኛ ‘ንጉሠ ነገሥታችሁ እንኳን ትቷት የሄደውን አገር እናንተ በዚህ በልጅነት እድሜያችሁ ቅማል ወሯችሁ የማይቀርላችሁን ሞት ገደል ለገደል ከምታባርሩ ይልቅ ገብታችሁ ከኢጣልያ ጋር አገራችሁን በልማት ብታገለግሉ አይሻልም ወይ? መሣሪያችሁን አስረክባችሁ የገባችሁ እንደሆነ ኢጣልያ ትምራችኋለች፤ ሹመት እና ሽልማትም ትሰጣችኋለች” ብሎ ሲሰብካቸው ወጣት አርበኞቹም ቀደም ሲል በ፲፱፻፴ ዓ.ም ይኼው ሰላይ ወደ ራስ አበበ አረጋይ ዘንድ ሄዶ የጦሩን ኃይል ከሰለለ በኋላ ብዙ አርበኛ እንዳስፈጀ ሰምተው ስለነበር እነሱንም እንደዚሁ ለማስፈጀት እንደመጣ ተገንዝበውታል። ከሰበካው በኋላ ወደ እኩለ ቀን ሲሆን ተበተኑ።

የቀስተኛ (በስተቀኝ በቡሽ ባርኔጣ) መጨረሻ ይስለላ ተልዕኮ

ከዚህ በኋላ ሙሴ ቀስተኛ ወደሠፈረት ቦታ፣ በመጣባት በቅሎ በባሻ ኪዳኔ ወልደመድኅንታጅቦ ሲሄዱ፣ ባሻ ኪዳኔ ቀስተኛ የለበሰው ካፖርት በደም እንዳይበላሽ በማሰብ “ሐሩር ፀሐይ ነውና እንዳይውብቅዎት ካፖርትዎን ያውልቁት” ሲሉት “ልጄ ልትገለኝ ነው” አላቸው። ይሄኔ ባሻ ኪዳኔ ወልደ መድኅን በመውዜር ጠመንጃ ሲመቱት 'ማማ ሚያ፤ ኢጣልያ ለዘለዓለም ትኑር ለኢጣሊያ ስል ሞትኩላት' ብሎ ሲፎክር በሽጉጥ ራሱን መትተው ገደሉት። የለበሰውንም ሙሉ ገበርዲን ልብስና ካፖርት እንዲሁም የንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ምስል ያለበትን የብር ሰዐትና በቅሎውን ከነኮርቻው ማረኩት። እሱም እንደተገደለ አብረውት መጥተው የነበሩት ባላባቶች ለጄነራል ናዚ አስታውቀው ኖሮ ሃያ ዓምስት ባታሊዮን ወታደርና ሃያ ስምንት አውሮፕላን ወደበዳቄሮ ዘምቶ ተርታውን ለሦሥት ቀን ሲከላከሉ ከቆዩ በኋላ አርበኞቹ ተሸንፈው ጠላትም የሙሴ ቀስተኛን እሬሳ አንስቶ ወሰደ። አርበኞቹም ከዚያ ሥፍራ ሸሽተው ሶዶ ላይ እንደገና ለስምንት ቀን ተዋጉ። [5]

አንቶኒ ሞክለር (እንግሊዝኛ፤ Anthony Mockler) ስለቀስተኛ ሞት ሲያወሳን በስህተት በገረሱ ዱኪ ተሰቅሎ ሞተ ይለናል። ሆኖም የጣልያን መንግሥት ገረሱን ለሚገድልለት ሰው ፶ ሺህ ሊራ እንደሚሰጥ ማወጁንና በኋላ የጣልያን መንግሥት እንደራሴ፣ ዱካ ዳኦስታም ይሄንን ሽልማት እጥፍ እንዳደረገው ይነግረናል። [6]

ሙሴ ቀስተኛ በዚያው በ፲፱፻፴ ዓ/ም ከሞት በኋላ የጣልያን መንግሥትን የወርቅ የጦር ጀብዱ ሜዳይ (ጣልያንኛ፤ Medaglia d'oro al valor militare) ተሸልሟል። የመዳልያውን አሰጣጥ የሚተነትነው ጽሑፍ በፋሽሽት ፕሮፓጋንዳ እና ሐሰት የተመረዘ ሲሆን ሙሴ ቀስተኛ በኢጣልያ መንግሥት ሥር የትውልድ አገሩን ሲያገለግል እንደሞተ ይነግረንና፣ “አንድ ፈሪ፣ አረመኔ የሽፍታ ዓለቃ (ገረሱ ዱኪን ማለቱ ነው!) ለውይይት ና ብሎ ጽፎለት በማታለል እጁን ሊይዘው መሆኑን ሲገነዘብ፣ እሱ ግን በዕድሜው የገፋ ቢሆንም እጁን ላለመስጠት ሲያመልጥ ተገደለ።” ይለናል።[7]

ድምዳሜ

ሙሴ ቀስተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከ አድዋ ጀምሮ እስከ ፋሽሽት ወረራ ድረስ ለአርባ ዓመታት ትልቅ ሚና የተጫወተ፣ እንደውም ታሪኳም የነበረ ሰው ቢሆንም በትውልድ አገሩ ኢጣልያም ቢሆን በሚስቱና የልጆቹ አገር ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ‘ብቅ፣ ጥልቅ’ ከማለት በስተቀር እምብዛም ስለሱ የተጻፈ ነገር የለም።

ከአድዋ ጦርነት በኋላ በምርኮኝነት ኢትዮጵያ ላይ ይቅር እንጂ ከዚያ በኋላ ኑሮውን እዚያው ያደረገው በውዴታ ይሁን በግዴታ አይታወቅም። እጃንሆይ ምኒልክስ ዘንድ በማን አስተዋዋቂነት/አቅራቢነት ኖሯል የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ዕቅድ ለመንደፍ የበቃው? በሕዝብ የሥራ ሚኒስቴር ውስጥ ዲሬክቶር በነበረበት ጊዜ ሌላ በሙያው የሠራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ከራስ ደስታ ዳምጠው አክስት ጋር ለጋብቻ የበቃውስ በምን ሁኔታ ነበር? እነኚህንና የመሳሰሉ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

[8]ኢትዮጵያዊው ምሁር መርሳዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ (18 91 -1971 እ.ኢ.አ.) “ትዝታዪ ስለ ራሴ የማስታውሰው“ በሚለው የህይወት ታሪክ መፅሀፋቸው፤ ሙሴ ቀስተኛ ከሌላ ጣሊያናዊ ቴንቲኒ ባንዲ ከተባለ ጋር በንጉስ ዳግማዎ ሚኒሊክ ዕቅድ ከአዲስ አበባ እስከ አዲስ ዐለም ያለውን መንገድ በድንጋይ ንጣፍ ለማልበስ የቅድመ ምርመራ “survey “ስራውን እንደሰሩ ማወቃቸውን ተርከዋል፤[9] በሌላ መፅሀፍ የወቅቷን አዲስ አበባ በፎቶግራፍ በሚያሳይ መፅሀፍ ኢጣሊያዊው መሀንዲስ ቀስተኛ ወደ እንጦጦ ማርያም ቤተ/ክርስቲያን የሚያመራውን የመንገድ ስራ በበላይነት ቀጥጥር ላይ እንደተሳተፍ ተገልፆል፤[10] ከሌላም ምንጭ እንደተገለፀውም በዐባይ ወንዝ ላይ ለተሰራው ድልድይም አቅጣጫዎችን መርቷል፡፡

ማገናዘቢያ

  1. Pegolotti (1970): pp 79-85.
  2. www.quiaidone.it/giornalino/Gennaio2009.pdf sebastiano castagna
  3. “Cultural Heritage Promotion” An exemplary restoration of a historic building in Kasainchis, Addis Abeba, Ethiopia (Addis Abeba November 2005) p12
  4. Sbacchi(1997) p176
  5. 4 አዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ ፴፰ኛ ዓመት ቁጥር ፴፰፣ ቅዳሜ ጥቅምት ፲፮ ቀን ፲፱፻፸፪ ዓ/ ም
  6. Mockler(2003), p191
  7. http://www.quirinale.it/elementi/DettaglioOnorificenze.aspx?decorato=13955
  8. ትዝታዪ ስለ ራሴ የማስታውሰው አምኀ መርሳዔ ኀዘን
  9. The City and it’s Architectural Heritage A.A. 1886 -1941 Fasil Giorghis & Denis Gerhard
  10. https://ru.wikipedia.org/wiki/%D0%9A%D0%B0%D1%81%D1%82%D0%B0%D0%BD%D1%8C%D1%8F,_%D0%A1%D0%B5%D0%B1%D0%B0%D1%81%D1%82%D1%8C%D1%8F%D0%BD%D0%BE

ዋቢ ምንጮች

  • Mockler, Anthony; Haile Selassie’s War (2003)
  • Pegolotti, B, “Un Italiano alla Corte di Menelik,” Storia Illustrata 148 (March 1970)
  • Sbacchi, Alberto: Legacy of Bitterness Ethiopia & Fascist Italy 1935-1941 (1997)
  • “Cultural Heritage Promotion” An exemplary restoration of a historic building in Kasainchis, Addis Abeba, Ethiopia (Addis Abeba November 2005)
This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.