መንግስቱ ለማ

መንግሥቱ ለማ (1924-1988) በጣሊያን ወረራ ዋዜማ በሀረር ሀደሬ ጢቆ መካነ ሥላሴ ተወልዶ ከቆሎ ተማሪነት ተነስቶ የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ደቀመዝሙርነት እስከመሆን በቅቶ የቅኔ ቤት ሊቅነት ሳይበቃው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ቀደምቶች መሃከል ለመደብለቅ የበቃ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ድንቅ ገጣምያን/ፀሃፌ ተውኔቶች አንዱ ነው። አባቱ አለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ-ታሪክ (ታሪክ የእናታቸው ስም ነው - ምናልባት በኢትዮጵያ ታሪክ የእናታቸውን ስም ከስማቸው አስተባብረው በመጻፍ የመጀመሪያው ሳይሆኑ አይቀሩም) ታዋቂ የቤተክርስቲያን ሊቅ የነበሩ ሲሆን በመጀመሪያ ላይ የመንግስቱን የአስኳላ (በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት የሚጠራው እንዲህ ነበር) ትምህርት ባይወዱለትም ጣሊያኖቹ ልጁን የማያስተምር ሰው ሁሉ ይቀጡ ስለነበር ለማስተማር ተገደዋል። ሁዋላ ላይ ግን እሳቸው አዲስ አበባቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ ተቀይረው መጥተው እሱ የኮተቤ ተማሪ ከሆነና የትምህርት ውጤቱም እስደሳች ሲሆን የቀድሞ ቅዋሜያቸውን ሳያላሉት አልቀሩም።

መንግስቱ በእንግሊዝ አገር ወደ ስድስት አመት ቢቆይም ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ ነው በ1956 ዓ.ም ወደ አገሩ ለመመለስ የበቃው። ይሁን እና በቆይታው ከብዙ የእንግሊዝ ደራስያን ጋር ለመተዋወቅ በቅቷል። በተለይም ከጆርጅ በርናርድ ሾው ጋር ወዳጆች እንደነበሩ ይነገራል።

መንግሥቱ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በሁዋላ የተሰማራው ወደ መንግስት ሥራ ሲሆን በህንድ አገር ዲፕሎማት ሆኖ ከሄደ በሁዋላ ምናልባትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ ኮሜድ ተውኔት «ጠልፎ በኪሴ"ን ደርሷል:: ከዚያ በሁዋላ የደረሳቸው እነ «ያላቻ ጋብቻ»፣ «ጸረ-ኮሎኒያሊስት»፣ «ባለካባና ባለዳባ» የመንግስቱን ስም በኢትዮጵያ የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ ካደረጉት ስራዎቹ መካከል ናቸው። በተጨማሪም «The bear» የተሰኘውን እና የታዋቂው የሩሲያ ደራሲ አንቷን ቼኾቭ ተውኔት የሆነውን «ዳንዴዎ ጨቡዴ» በሚል የተረጎመ ሲሆን የጄ.ቢ. ፕሪስትሊን «The Inspector Calls»ን ተርጉሞ ለመድረክ አብቅቷል።

መንግስቱ ከተውኔቱ በተጨማሪም በስነ-ግጥም የተዋጣለት እንደነበር ስራዎቹ ይመሰክራሉ። «የግጥም ጉባኤ» የተሰኘው ስብስብ መንግስቱ የግጥም መክሊት የተቸረው ደራሲ እንደነበር ይመሰክራል።

መንግሥቱ ደራሲም ብቻ አልነበረም፤ በተማሪዎቹ የተወደደ መምህር በሳል ተመራማሪ ለባህሉ እና ለቋንቋው ሙት የነበረ ከኢትዮጵያ ብርቅዬዎች አንዱ ነው።

Archived ፌብሩዌሪ 2, 2007 at the Wayback Machine Archived ሜይ 17, 2006 at the Wayback Machine Archived ማርች 7, 2007 at the Wayback Machine

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.