ሑራውያን
ሑራውያን (ሑርኛ፦ ሑሪ ) በጥንት በስሜን መስጴጦምያ አካባቢ የተገኘ ብሔር ነበሩ።
ቋንቋቸው ሑርኛ የኡራርትኛ ዘመድ ሲሆን ሕዝቡ ከአራራት ዙሪያ ወደ ደቡብ እንደ ደረሱ ይታስባል። መጀመርያው በእርግጥ የሚታወቁ በአካድ መንግሥት ዘመን (2075 ዓክልበ. ግድም) ሲሆን ለራሳቸው መንግስታት አቆሙ። አንዱ የሑራውያን መንግሥት በኡርከሽና በናጋር ሌላውም በአራጳና በኑዚ ነበር።
ከዚህ በላይ ብዙ ሑራውያን ቤተሠቦች ወደ ጎረቤቶቻቸው ግዛቶች ወደ አሙሩ፣ አሦር፣ እና ሐቲ ይፈልሱ ነበር። አንዳንዴ የሑርያውያንም ግዛቶች ለነዚህ ሃያላት ይገዙ ነበር።
በኋለኛ ዘመን ከባቢሎን መንግሥት ውድቀት (1507 ዓክልበ.) በኋላ፣ «ሚታኒ» የሚባሉ ሕንዳዊ-አውሮጳዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ አባላት የነበሩ አለቆች አዲስ መንግሥት በሶርያ አቆሙ፣ ኗሪዎቹ ግን በብዛት ሑራውያን ነበሩ። አራጳ እንደገና በዚህ ዘመን የሑራውያን መንግሥት አጸና።
በ13ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ. ላይ አሦራውያን እነዚህን መንግሥታት አጥፈው በሶርያ የቀሩት ትውልዳት ሑርኛ ትተው አሦርኛን ተማሩ፣ ቀበሌኛቸውም አራማይስጥ እንደ ሆነ ተብሏል። ሌሎች ሑራውያን በአራራት አካባቢ ቀሩ፣ እነዚህም በኋላ የኡራርቱ መንግሥት አቆሙ፣ ቋንቋቸውም ኡራርትኛ ሆነ። ይህም አገር በመጨረሻ በሕንዳዊ-አውሮጳውያን ተናጋሪዎች (በፍርግያውያን) ተገዛ፡ ቋንቋቸውም አርሜንኛ ሆነና ከሑርኛ ተጽእኖ አለው።
በብሉይ ኪዳን የተጠቀሱት ሖራውያን (ዘዳግም ፪፤፲፪) ወይም «የሖሪ ሰዎች» በሴይር በደቡብ ከነዓን ስለ ተገኙ፤ ከከነዓን ዘር ኤዊያዊ ስለ ሆኑ፣ ከነዚህ ሑራውያን ጋር አንድላይ እንደ ነበሩ አይታሥብም።
- የሑርኛ ቃላት ናሙና ለማየት የጥንታዊ ልሳናት ሷዴሽ በውክሸነሪ ይዩ።
- ኡርከሽ የተገኘ ቅርስ
- የሑራውያን ዕጣን ማጠኛ