ሊፒት-እሽታር
ሊፒት-እሽታር በሱመር የኢሲን ሥርወ መንግሥት 5ኛው ንጉሥ ነበረ (1833-1823 ዓክልበ. የነገሠ)። በርሱ ዘመን መጀመርያ የኢሲን ተወዳዳሪ የላርሳ ንጉሥ ጉንጉኑም ኡርን ከኢሲን ያዘ። ሊፒት-እሽታር በተለይ የሚታወቀው በ1832 ዓክልበ. ባወጣው ሕገ መንግሥት ምክንያት ነው። ይህ ሕገ ፍትሕ ከላጋሽ ንጉስ ከኡሩካጊና ሕግጋት በኋላ፣ ከኡርም ንጉሥ ከኡር-ናሙ ሕግጋት በኋላ የወጣ ሲሆን ለሱመር ሦስተኛው የሚታወቀው ሕገ መንግሥት ነው።
ዘመን
በሱመራዊ ነገሥታት ዝርዝር ላይ ፲፩ ዓመታት እንደ ነገሠ ሲለን ከዘመኑ ፲ የዓመት ስሞች ብቻ ይታወቃሉ።[1] ከመጀመርያው ዓመቱ በቀር ግን የሌሎቹ ዓመታት (a-i) ቅድም-ተከተላቸው እርግጥኛ አይደለም። ከነዚህም መካከል ለምሳሌ፦
- ፩ ፦ (1833 አክልበ. ግድም) ሊፒት-እሽታር ንጉሥ የሆነበት ዓመት
- g ፦ (1832 አክልበ. ግድም) ኤኒንሱንዚ የዑር ጣኦት መቅደስ ሴት ካህን የመረጠበት ዓመት
- a ፦ ሊፒት-እሽታር ፍትሕ በሱመርና አካድ ያደረገበት ዓመት
- b ፦ በጣኦታቱ (ኤንሊልና ናና) ትዕዛዝ ኡር የታደሰበት ዓመት
- h ፦ ማረሻ የተሠራበት ዓመት
- i ፦ (1826 አክልበ. ግድም?) ሊፒት-እሽታር አሞራውያንን ያሸነፈበት ዓመት
በተወዳዳሪው ጉንጉኑም ፲፫ኛው ዓመት (1832 ዓክልበ.)፣ የሊፒት-እሽታር ሴት ልጅ ኤኒንሱንዚ የዑር መቅደስ ጣኦት ሴት ካህን ሆና እንድትሾም አረጋገጠ። ስለዚህ የሊፒት-እሽታር ዓመት «g» ከዚያ በኋላ ሊሆን አይችልም።
በ1826 ዓክልበ.፣ ጉንጉኑም «የመንገድ ቤት» እንደ ያዘና ቦይ እንደ ከፈተ ይዘገባል። እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ በሊፒት-እሽታር ሰነዶች ይጠቀሳሉ። የሊፒ- እሽታር ሻለቃ ናና-ኪአጝ በጻፉለት ደብዳቤ ዘንድ፣ ፮ መቶ የጉንጉኑም ወታደሮች «የመንገድ ቤት» ይዘው አዲስ ቦይ ሊከፈቱ ነው ሲል የሊፒት-እሽታርን እርዳታ ይለምናል። በሊፒት-እሽታር መልስ ፪ ሺህ ጦረኞች፣ ፪ ሺህ ቀስተኞች፣ እና ፪ ሺህ ባለ ዶማዎች መላኩን አመለከተ። ጉንጉኑምን ድል እንዳደረጉ አይመስልም፤ ጉንጉኑምም «የሱመርና አካድ ንጉሥ» የሚለውን ማዕረግ ይግባኝ ነበረው፤ ኢሲን ግን ለጊዜው ነጻነቱን ጠበቀው።
የሊፒት-እሽታር ሕግጋት (1832 ዓክልበ.)
ጽሑፉ በብዙ ፍርስራሽ ላይ ተገኝቷል። በሙሉ የተገኙት ሕግጋት የሚከተሉት ናቸው።
- §8 ሰው አትክልት እንዲትክልበት መሬቱን ለባልንጀራው ቢሰጥ፣ ባልንጀራውም መሬቱን በሙሉ ካልተከለበት፣ ያልተከለበትን መሬት ለባለቤቱ ሰው ከነድርሻው ይመልሰው።
- §9 ሰው ወደ ባለቤቱ አትክልት ቦታ ገብቶ በዚያ በስርቆት ቢያዝ፣ 10 ሰቀል ብር ይክፈል።
- §10 ሰው በባልንጀራው አትክልት ቦታ ዛፍ ቢቆርጥ፣ ግማሽ ሚና ብር ይክፈል።
- §11 በሰው ቤት አጠገብ የባልንጀራው ምድረ በዳ ካለ፣ ባለቤቱም ለባለ መሬቱ «መሬትህ ባዶ ስለ ሆነ ሌባ እቤቴ ሰርቆ ቢገባስ፤ ቤትህን አጥና» ብሎ ቢነግረው፣ ይህም ስምምነት ከተረጋገጠ፣ ባለ መሬቱ ለባለ ቤቱ ማንኛውን የጠፋውን ንብረት ያተካል።
- §12 የሰው ገረድ ወይም ባርያ ወደ ከተማው መሃል ቢሸሽ / ብትሸሽ፣ በሌላ ሰው ቤት ላንድ ወር እንደ ኖረ(ች) ከተረጋገጠ፣ በባርያው ፋንታ ባርያ ይስጠው።
- §13 ባርያ ከሌለው፣ 15 ሰቀል ብር ይክፈል።
- §14 የሰው ባርያ ባርነቱን ለጌታው ሁለት እጥፍ እንደ ረከበው ከተረጋገጠ፣ ያው ባርያ ነፃ ይወጣል።
- §15 ሚቅቱም (አገልጋይ) የንጉሥ ሥጦታ ከሆነ፣ አይወሰደም።
- §16 ሚቅቱም በነጻ ፈቃዱ ወደ ሰው ቤት ቢሄድ፣ ያ ሰው ከግድ ሊይዘው አይችልም፤ ወደ ወደደበትም ሊሄድ ይችላል።
- §17 ሰው ያለ ፈቃድ ባልንጀራውን የማያውቅበት ነገር ውስጥ ካሰረው፣ ባልንጀራው ግድ የለውም፣ ሰውዬውም ባሰረው ነገር ውስጥ ቅጣቱን ይሸክማል።
- §18 የርስት ባለቤት ወይም የርስት እመቤት የርስቱን ግብር መክፈል ካልቻለ(ች)፣ ሌላ ሰውም ከከፈለው፣ ባለቤቱ ለሦስት ዓመት ለቆ እንዲወጣ አይገደድም። ከዚያ በኋላ ግብሩን የከፈለው ሰው ርስቱን ይይዛል፣ የቀድሞውም ባለ ርስት ምንም ይግባኝ አያነሣም።
- §22 አባትዬዋ እየኖረ፣ ሴት ልጂቱ የቤተ መቀደስ አገልጋይም ሆነ ሠራተኛ ብትሆን፣ እቤተሠቡ እንደ አንዲት ወራሽ ትኖራለች።
- §24 ሰው ያገባት ሁለተኛው ሚሥት ልጆች ከወለደችለት፣ ከአባትዋ ቤት ያመጣችው ጥሎሽ ለልጆችዋ ይሁን፣ ዳሩ ግን የመጀመርያይቱ ሚስቱ ልጆችና የ2ኛይቱ ልጆች የአባታቸውን ርስት በእኩልነት ይካፈሉ።
- §25 ሰው ሚስቱን ገብቶ ልጆችን ወልዶ እነዚያም ልጆች በሕይወት ቢሆኑ፣ ከዚህም ሌላ ደግሞ ባርያይቱ ለጌታዋ ልጆች ከወለደችለት፣ አባቱም ደግሞ ለባርያይቱና ለልጆችዋ ነጻነትን ከሠጣቸው እንደ ሆነ፣ የባርያይቱ ልጆች ግን ርስቱን ከቀድሞው ጌታቸው ልጆች ጋር አይካፈሉም።
- §27 የሰው ሚስት ልጆችን ካልወለደችለት የአደባባይ ሸርሙጣ ግን ልጆች ከወለደችለት፣ እርሱ ለዚያች ሸርሙጣ እህልን፣ ዘይትንና ልብስን ያስገኛል። ሸርሙጣዋ የወለደችለት ልጆች ወራሾቹ ይሆናሉ፤ ሚስቱ እየኖረች ግን ሸርሙጣዋ እቤቱ ከሚስቱ ጋር ከቶ አትኖርም።
- §29 አማች ወደ ዐማቶቹ ቤት ገብቶ፣ ከዚያም ከቤቱ አስወጥተውት ሚስቱንም ለባልንጀራው ለመስጠት ቃል ከገቡ፣ አማቹ ያመጣውን ስጦታዎች በሙሉ ይመልሱለትና ሚስቱ ባልንጀራውን ልታገባ ሕጋዊ አይሆንም።
- §34 ሰው በሬን ተከራይቶ ሥጋውንም በአፍንጫው ቀለበት ከቀደደው፣ የዋጋውን ሲሶ ይክፈል።
- §35 ሰው በሬን ተከራይቶ ዓይኑንም ካጎዳ፣ የዋጋውን ግማሽ ይክፈል።
- §36 ሰው በሬን ተከራይቶ ቀንዱን ከሰበረው፣ የዋጋውን ሩብ ይክፈል።
- §37 ሰው በሬን ተከራይቶ ጅራቱን ካጎዳ፣ የዋጋውን ሩብ ይክፈል።
ቀዳሚው እሽመ-ዳጋን |
የኢሲንና የሱመር ንጉሥ 1833-1823 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ ኡር-ኒኑርታ |
ዋቢ ምንጮች
- James R. Court, Codex Collections from Mesopotamia and Asia Minor. Scholars Press, 1995. (እንግሊዝኛ)
- Francis R. Steele, The Code of Lipit Ishtar - University of Pennsylvania Museum Monographs, 1948 - includes complete text and analysis of all fragments [reprinted from American Journal of Archaeology 52 (1948)] (እንግሊዝኛ)