ሄራክሌስ
ሄራክሌስ በግሪክ አገር አፈ ታሪክ በጥንት የኖረ ጀግና ሰው ነበር። ስለዚሁ ሄራክሌስ እጅግ ብዙ ትውፊቶች ተባሉ። በሮሜ አፈ ታሪክ ደግሞ ሄርኩሌስ ይባላል። ይህ መጣጥፍ ስለ ግሪኩ አፈ ታሪክ ነው።
በዲዮዶሮስ
ግሪኩ ጸሐፊ ዲዮዶሮስ ሲኩሉስ በ«የታሪክ መጽሐፍ ቤት» ምዕራፍ ፬ የሄራክሌስ አፈታሪኮች በሙሉ ይገልጻል። ዲዮዶሮስ እንዳለው ሄራክሌስ ከዚውስና አልክሜኔ ተወለደ። እናቱ አልክሜኔ የፔርሴዎስ ልጅ ነበረች። ልጁ ሲወለድ ከመንታ ወንድሙ ኤውሩስጠውስ ጋር ተወለደ። ኤውሩስጠዎስ አስቀድሞ ስለ ተወለደ እርሱ የፔርሴዎስ ልጆች ንጉሥ ሆነና ሄራክሌስ ፲፪ ታላቅ ሥራዎች ለወንድሙ ኤውሩጠዎስ መፈጽም ነበረበት። ልጁ በቲሩንስ በአርጎስ ዙሪያ አደገ።
ሄራክሌስ ሕጻን ሲሆን ሄራ ሁለት እባቦች እንዲገድሉት ላከች። እርሱ ግን በእጁ አንቆ ገደላቸው። ከሌላ ሰው ልጅ ሁሉ ጠንካራ ሆነ። በኋላ የአልክሜኔ ባል አምፊትርዮን ወደ ጤቤስ ተዛወረ። የጤቤስ ንጉሥ ክሬዮን ለሚንያን ሕዝብ ንጉሥ ኤርጊኑስ ተገዥ ነበር። የጤቤስ ሰዎች በየዓመቱ መቶ ከብት ለሚንያውያን መገብር ነበረባቸው። ጭቆናቸው ስለ በዛ ሄራክሌስ ገና ልጅ ሲሆን ሚንያውያንን ከጤቤስ አስወጥቶ ኤርጊኑስን እራሱን ገደለውና ከተማቸውን ኦርቆሜሞስን አጠፋ። ከዚህ ድርጊት በኋላ ሄራክሌስ የክሬዮን ሴት ልጅ መጋራ አገባት።
ከዚያ በኋላ ሄራክሌስ ለወንድሙ የአርጎስ ንጉሥ ኤውሩስጠዎስ ፲፪ቱን ታላላቅ ሥራዎች መፈጸም ስለ ተገደደው ለትንሽ ጊዜ እብድ ሆነና ከመጋራ የተወለዱትን ልጆቹን በስኅተት ጠላቶች መስለውት ገደላቸው። አዕምሮው ወደ ጤንነት በተመለሰ ጊዜ ፲፪ቱን ታላላቅ ሥራዎች ጀመረ።
መጀመርያው ታላቅ ሥራ የነመያ አንበሣን ለመግደል ነበር። ሄራክሌስ ይህን በእጁ ፈጸመና ቆዳውን ለልብሱ አደረገ።
፪ኛው ታላቅ ሥራ የለርናያ ሁድራ ለማሸነፍ ነበር። ይች አስቀያሚ መቶ የእባብ ራሶች የነበሯት ግሩም ፍጡር ነበረች። እንድ ራስ ቢቆረጥ፣ ሁለት ራሶች በፈንታው ወዲያው ይበቅሉ ነበር። ስለዚህ ሄራክሌስ አንድ ራስ እንደ ቆረጠው፣ የወንድሙ ልጅ ዮላዎስ ያንጊዜ አንገቱን በፋና እንዲያቃጥለው አደረገ። በዚህ ዘዴ ራሶቹን ሁሉ ቆርጦ ሄርኩሌስ ሊያሸንፋት ቻለው።
፫ኛው ታላቅ ሥራ የኤሩማንጢዮስ እሪያ በሕይወቱ ከደብረ ላምፐያ በአርካዲያ ለማምጣት ነበር። ይህን በትንቃቄ መፈጽም ቢያስፈልግም ለሄራክሌስ በቀላሉ ተከናወነ። ከዚህ ሥራ በኋላ ሄራክሌስ ከከንታውሮች ወገን ጋር ታገለና ብዙዎችን ገደለ፤ እነኚህ ግማሽ ሰዎች በግማሽም ፈረሶች ነበሩ።
፬ኛው ታላቅ ሥራ ወቃማ ቀንዶች ያለውን አጋዘን ለመማረክ ነበር፤ ይህንን በቀላል ፈጸመ።
፭ኛው ታላቅ ሥራ የስቱምፋሊያ ሐይቅ አዕዋፍ ለማብረር ነበር። እነዚህ አዕዋፍ ከብዛታቸው የተነሣ ፍራፍሬውን ያጠፉ ነበር። ሄራክሌስ ከነሐስ አንድ መንኳኳያ ሠርቶ ታላቅ ድምጽን በማሰማት ከሐይቁ አባረራቸው።
፮ኛው ታላቅ ሥራ የአውገያስን ጋጣ በአንድ ቀን ውስጥ ለማጽዳት ነበር። ይህን ለመፈጽም ሄራክሌስ የአልፈዮስ ወንዝ ፈሳሽ ከመኝታው ወደ ጋጣው አስለወጠ።
፯ኛው ታላቅ ሥራ የቀርጤስ ወይፈንን ለማምጣት ነበር፤ ይህንም በቀርጤስ ንጉሥ ሚኖስ እርዳታ ቶሎ አደረገ። ከዚሁ ሥራ በኋላ ሄራክሌስ መጀመርያ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንደ መሠረተ ይለናል።
፰ኛው ታላው ሥራ የዲዮሜዴስ ፈረሶችን ከጥራክያ አገር ለማምጣት ነበር። (እስካሁን ድረስ የተጠቀሱት ቦታዎች ሁሉ በግሪክ አገር ውስጥ ናቸው።) እነዚህ ፈረሶች የሰው ሥጋ የሚበሉ ነበሩ፤ ሄርኩሌስ ግን ጠባቂያቸውን ዲዮሜዴስን አመገባቸውና ሰረቃቸው። ከዚህ ሥራ በኋላ ሄራክሌስ በስመ ጥሩ ጉዞ ከያሶንና አርጎናውቶች ጋራ ወደ ኮልቂስ (የአሁን ጂዮርጂያ) ወርቃማ ሱፍን ለማግኘት ተጓዘ።
፱ኛው ታላቅ ሥራ የአማዞኖች አለቃ ሂፖሊቴ መታጠቂያ ለማምጣት ነበር። በጥቁር ባሕር በኩል ሄዶ ወደ አማዞኖች ከተማ ጠሚስኩራ (በአሁኑ ቱርክ) ደርሶ አማዞኖቹን ድል አደረጋቸውና አብዛኞቹን ገደላቸው። እንዲህ መታጠቂያውን ይዞ ተመለሰ።
፲ኛው ታላቅ ሥራ የቅሩሳውር ፫ ልጆች ጌርዮኔስ ለማሸበፍና ከብታችውን ከኢቤሪያ (የአሁን እስፓንያ) ለማምጣት ነበር።
- መጀመርያ ወደ ቀርጤስ ሄዶ ሄራክሌስ ለዘመቻ እያዘጋጀ ደሴቱን ከአውሬዎች አነጻ።
- ከዚያ ወደ ሊብያ ተጉዞ አንታዮስ የሚባል ታላቅ ትግለኛ ገደለ።
- ቀጥሎ ወደ ግብጽ ገብቶ የግብጽ ንጉሥ ቡሲሪስን ገደለ።
- ወደ ሊብያ ተመልሶ አንድ ከተማ «ሄካቶምፑሎን» («መቶ በሮች») መሠረተ።
- እስከ ጋዴራ ድረስ ደርሶ ሁለቱን የሄራክሌስ ዓምዶች መሠረተ።
- ወደ ኢቤሪያ ገብቶ ፫ቱን ጌርዮኔስ ገደላቸው፣ አዲስ ንጉሥ ሰጣቸው።
- ከዚያ በኬልቲካ (የአሁን ፈረንሳይ) ዓለፈ፣ የሕገ ወጥ ሁኔታ እዚያ አቀና፣ አንድ ከተማ አሌሲያ መሠረተ።
- ከዚያ ወደ ሊጉርያ (ጣልያን) እየሄደ መንገድ በአልፕ ተራሮች በኩል ጠረገ።
- ወደ ቲቤር ወንዝ በሮሜ ከተማ ሥፍር ሠፈረ።
- ወደ ደቡብ ተጉዞ በደብረ ቬሱቪዩስ የጊጋንቴስን ወገን በውግያ አሸነፋቸው።
- ወደ ሲኪሊያ ተሻገረ - በመዋኘት። ከንጉሡ ኤሩክስ ጋራ የትግል ቁማርት ተጫወተ። ኤሩክስ ቢያሸንፍ ከብቱን ይወስድና ሄራክሌስ ቢያሸንፍ አገሩን ይወስዳል የሚል ጨዋታ ነበር። ሄራክሌስ አሸነፈውና አገሩን ለኗሪዎቹ ሰጠው።
- ወደ ጣልያን ተመልሶ አድሪያቲክ ባሕርን ዞሮ ወደ ግሪክ አገር ተመለሰና ከብቱን ለኤውሩጠዎስ አቀረበ።
፲፩ኛው ታላቅ ሥራ ወደ ሃደስ (ሢኦል በግሪኮች እምነት) መግባትና ውሻውን ኬርቤሮስን ለማምጣት ነበር፤ ይህንም በፐርሰፎኔ እርዳታ አደረገ።
፲፪ኛውና መጨረሻው ታላቅ ሥራ የሄስፔሪዴስ ወርቃማ ቱፋሆች ከሊብያ ምዕራብ (ከአትላንቲክ ጠረፍ) ለማምጣት ነበር። ይህን አድርጎ ደግሞ አንታዮስንና ቡሲሪስን እንዲሁም የአይቲዮፒያ ንጉሥ ኤማጥዮንን የገደላቸው በዚህ ጉዞ እንደ ነበር አንዳንዴ ይባላል። ከዚያ በፊት የቡሲሪስ መርከበኞች ቁንጃጅት ከሄስፔሪዴስ ይሠርቁ ነበር ይለናል።
በዚያን ጊዜ ሄራክሌስ በአፍሪካ እያለ የተረፉት አማዞኖችና የእስኩቴስ ሰዎች አብረው በጥራክያ አልፈው ወደ ግሪክ ገብተው አቲካን ወረሩ፤ ጤሴዎስ ግን አሸነፋቸው።
ከዚያ በኋላ ሄራክሌስ የወንድሙን ልጅ ዮላዎስን ወደ ሳርዲኒያ ልኮ ቅኝ አገር በዚያ ተመሰረተ። ሄራክሌስ እንደገና አብዶ ኢፎቶስን ገደለ፣ ስለዚህ ለማዮንያ (ልድያ) ንግሥት ኦምፋሌ ለጊዜው እንደ ባርያ ማገልገል ቅጣቱ ሆነ። የኦምፋሌ ባርያ እየሆነ ሄራክሌስ የማዮንያ ጠላት የሆነ የኢቶኒያ ሕዝብ ድል አደረጋቸው።
ቀጥሎ ሄራክሌስ በኢሊዩም (ትሮይ) ንጉሥ ላዎሜዶን ላይ ቂም ስላለው የመርከቦች ኃይል ይዞ ጦርነት በትሮይ ላይ ሠራ። ላዎሜዶንን ገድሎ ልጁን ፕሪያም የኢሊዩም ንጉሥ እንዲሆን ሾመው።
ይህን አድርጎ ሄራክሌስ በግሪክ አገር ቆይቶ አውገያስንና አንዳንድ ከተሞች አሸነፈ። በግሪክ ጉዳዮች ጥልቅ አድርጎ ባገኙት ሴቶች ሌሎች ልጆች ወለደ። በመጨረሻ በደብረ ኦይቴ ራሱን ወደ እሳት ጥሎ ሞተ።
በሥነ ጥበብ
እስከ እስፓንያ ድረስ የገዛው ሄራክሌስ በግሪክ አፈ ታሪክ ስለ ተወደደ፣ በባህላቸው ብዙ የሄራክሌስ ምስል ሠሩ። ከታላቁ እስክንድር በኋላ ግሪኮች ይህንን ልማድ እስከ ባክትሪያ ወይም የዛሬው አፍጋኒስታን ድረስ ወሰዱት። በዚያ የቆሙ ግሪኮች መንግሥታት በኋላ ቡዲስት ሆኑና የሄራክሌስ ምስል መሥራት ወደ ቡዲስት ሃይማኖት አስገቡ፤ ቅርጹም ለጎታማ ቡዳ ዘበኛ ቫጅራፓኒ ተጠቀመ። ይህም የቫጅራፓኒ ምስል ልማድ እስከ ጃፓን ድረስ ገብቶ የጣኦታቸው ሹኮንጎሺን መነሻ ሆነ።
ዋቢ ምንጭ
- የሄራክሌስ ታሪክ በዲዮዶሮስ (እንግሊዝኛ)