ሂክሶስ

ሂክሶስ (ከግሪክኛ Ὑκσώς /ሂውክሶስ/፣ ግብጽኛ፦ /ሄቃ ኻሱት/) በ1661 ዓክልበ. ግድም ከከነዓን ወጥተው ጥንታዊ ግብጽን የወረሩት አሞራውያን ወይም ከነዓናዊ ወገኖች ነበሩ። በስሜኑ ግብጽ የራሳቸውን 15ኛው ሥርወ መንግሥት እስከ 1548 ዓክልበ. ድረስ ያሕል መሠረቱ። በዚያን ጊዜ የደቡቡ ኗሪ ፈርዖን 1 አህሞስ ከግብጽ አስወጣቸው፤ አህሞስም የ18ኛው ሥርወ መንግሥትና የአዲስ መንግሥት መሥራች ሆነ።

፩ አህሞስ ሂክሶስን በ1548 ዓክልበ. ከግብጽ ሲያስወጣቸው

የሂክሶስ ስያሜ «ሄቃ ኻሱ» በግብጽኛ ማለት «ባዕድ ነገሥታት» እንደ ሆነ አሁን ታውቋል። በ1ኛው ክፍለ ዘመን ዓም የጻፈው ሊቅ ዮሴፉስ ግን በመሳሳት ማለቱ «እረኛ ነገሥታት» እንደ ሆነ መሰለው።

ስድስት የሂክሶስ ነገስታት እንደ ገዙ በማለት ማኔቶን እና የቶሪኖ ቀኖና ይስማማሉ፤ ሆኖም እነዚህ ምንጮች ብዙ መቶ አመት ከሂክሶስ ዘመን በኋላ ተመዘገቡ። ለመሆኑም ከሥነ ቅርስ ስድስት «ሂክሶስ» የታሰቡት ነገሥታት ስሞች ተገኝተዋል። ያሉን ፮ ነገስታት ስሞች ሳኪር-ሃርአፐር-አናቲኽያንሻሙቄኑአፐፒ፣ እና ኻሙዲ ናቸው። ቅድም-ተከተላቸው ግን ምንም እርግጥኛ አይደለም።

የቶሪኖ ቀኖና በተባለው ፈርዖኖች ዝርዝር ላይ፣ አምስቱ ስሞች ተደምስሰው ለማንበብ የሚቻለው «...ኻሙዲ። ስድስት ሄቃ-ኻሱት፣ ለመቶ [...] ዓመታት ገዙ።» ስለዚህ ኻሙዲ የሂክሶስ መጨረሻ ንጉሥ እንደ ነበር ይታስባል።

የማኔቶን ዝርዝር በልዩ ልዩ ቅጂዎች ደርሶልናል። ስማቸው በግሪክ አልፋቤት ተጽፈው የተከረሩ ሆነዋል፤ ቅጂዎቹም አይስማሙም።

  • በዮሴፉስ ዘንድ፦ ሳላቲስ (19 ዓመታት)፤ ብኖን (44)፤ አፓኽናን (36 ዓመት 7 ወር)፤ አፖፊስ (61)፤ ያናስ (50 አመት 1 ወር)፤ አሴጥ (49 አመት 2 ወር)፤ ጠቅላላ 259 ዓመት 10 ወር።
  • አውሳብዮስ ዘንድ፦ ሳይቴስ (19)፤ ብኖን (40)፤ አርኽሌስ (30)፤ አፎፊስ (14)፤ ጠቅላላ 103 ዓመታት። (አራት ስሞች ብቻ ተዘረዘሩ።)
  • አፍሪካኑስ ዘንድ፦ ሳይቴስ (19)፤ ብኖን (44)፤ ፓኽናን (61)፤ ስተዓን (50)፤ አርኽሌስ (49)፤ አፎቢስ (61)፤ ጠቅላላ 284 ዓመታት
  • ሱንኬሎስ ዘንድ፦ ሳሊቲስ (19)፤ ባዮን (4)፤ አፓኽናስ (36)፤ አፖፊስ (61)፤ ሴጦስ (50)፤ ኬርቶስ (44)፤ ጠቅላላ 254 ዓመታት።
ግብጽ በሒክሶስ ዘመን

ከግብጽ 13ኛው ሥርወ መንግሥት ፈርዖን ከመርነፈሬ አይ ዘመን (1665-1661 ዓክልበ ግድም) ቀጥሎ፣ የግብጽ ሥራዊትና የግብጽ ሃይል ድንገት እንደ ደከሙ ይመስላል። የመርነፈሬ ተከታዮች ከጤቤስ ከተማ ወይም ከላይኛ (ደቡብ) ግብጽ በጣም ሩቅ ሊገዙ አልቻሉምና። ስለዚህ የሂክሶስ አሞራውያን ከከነዓን የወረሩ ከመርነፈሬ ዘመን መጨረሻ ቀጥሎ ወይም በ1661 ዓክልበ. ተከሠተ። ከዚያው በፊት ዕብራውያን ደግሞ ከከነዓን ወደ ግብጽ ደርሰው የ14ኛው ሥርወ መንግሥት ግዛት (1821-1742 ዓክልበ.) በጌሤም እንደ ነበራቸው ይመስላል። ከ1742 ዓክልበ. በኋላ ግን ወደ ባርነት ገብተው ዕብራውያን ከግብጽ በሙሴ መሪነት ወደ ሲና ልሳነ ምድር የወጡ ደግሞ በ1661 ዓክልበ. እንደ ሆነ በኩፋሌ አቆጣጠር ይስማማል፤ የግብጽም ሥልጣን በዚያው ሰዓት የደከመው በኦሪት ዘጸአት ስለ ተገለጹ ክስተቶች ከሆነ፣ የሂክሶስ-ግብጽ ጦርነቶች ወቅት ዕብራውያን በሲና እየቆዩና ከዚያ ከነዓንን ወርረው እየያዙዋት ነበር። በዘመናት ላይ አንዳንድ ጸሐፊዎች ግን በመሳሳት ዕብራውያን ከግብጽ መውጣታቸውና ሂክሶስ ከግብጽ መውጣታቸው አንድ ድርጊት አድርገው ሂክሶስ እራሳቸው እብራውያን ወይም የሙሴ ወገን ነበሩ ብለዋል።

ሂክሶስ ወደ ግብጽ ሠረገላውን እና ፈረስን መጀመርያ ያስገቡት እንደ ሆኑ ተብሏል። በቅርብም ኗሪ ግብጻውያን ሥራዊት ይጠቅሙዋቸው ጀመር።

ሂክሶስ ከከነዓን ወጥተው የግብጽ ስሜን ከያዙ በኋላ ግብጽ እንደገና በሁለት ተከፈለች (13ኛ እና 15ኛው ሥርወ መንግሥታት)። ሂክሶስ 1661-1548 ዓክልበ. ከኗሪ ግብጻውያን ሥርወ መንግሥታት ጋራ ጦርነቶች ተዋጉ። 13ኛው ሥርወ መንግስት በጤቤስ እስከ 1646 ዓክልበ. ግ. ቀረ፣ በፈንታው 16ኛው ሥርወ መንግሥት በጤቤስና ሌላ «የአቢዶስ ሥርወ መንግሥት» ከዚያ ወደ ስሜን በአቢዶስ እንደ ተነሡ ይመስላል። 15ኛው የሂክሶስ ሥርወ መንግሥት በ1596 ዓክልበ. ግድም የአቢዶስን መንግሥት አሸነፉ፣ በ1590 ዓክልበ. ደግሞ ጤቤስን ይዘው 16ኛውን ሥርወ መንግሥት አስጨረሱ። ይህም የሂክሶስ ጫፍ ነበረ። በ1588 ዓክልበ. ሂክሶስ እንደገና ጤቤስን ትተው አዲሱ 17ኛው ሥርወ መንግሥት በጤቤስ ቆመ። ይህ 17ኛው ሥርወ መንግሥት ሂክሶስን ወደ ስሜን መለሳቸው፤ በመጨረሻም ግብጻዊው ንጉሥ 1 አህሞሰ (1558-1533 ዓክልበ. ግድም) የሂክሶስ ቅሬታ በማስወጣቱ (1548 ዓክልበ.) ግብጽኝ ዳግመኛ ስላዋኸደ፣ የግብጽ «አዲሱ መንግሥት» በዚያው ይጀመራል። ሂክሶስ ወደ ከነዓን ተባርረው የዕብራውያን ነገደ ስምዖን ከተማ የሆነውን ሻሩሄንን ያዙ፤ የአሕሞስም ሥራዊት በዚያ ፮ ዓመታት ከብበዋቸው በ1542 ዓክልበ. አጠፉት።

ሂክሶስ የከነዓን አሞራውያን ዘር ነበሩ ቢመስልም፣ በዘመናት ላይ ስለ መታወቂያቸው ብዙ ተቀራኒ አስተሳስቦች ኑረዋል። ዮሴፉስና ሌሎች እንደ መሠላቸው የሂክሶስ መባረርና የሙሴ ጸአት አንድ ነበሩና ስለዚህ ሂክሶስ ዕብራውያን ነበሩ ብለው ገመቱ። የስኮትላንድ ተጓዥ አቶ ጄምስ ብሩስ እንደ መሰለው ሂክሶስ ከሀበሻና ከዮቅጣን ዘር ነበሩ ስለ ጻፈ፣ አንዳንድ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሓፊዎች ይህንን ተቀብለዋል። ካለፈው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አንዳንድ የአውሮፓ መምህሮች የሂክሶስ መሪዎች ከሚታኒ ሕንዳዊ-አውሮፓዊ ተናጋሪ ወገን ተነሡ የሚለውን ክርክር ለመግፋት ሞክረዋል። ሆኖም ሚታኒ በስሜኑ መስጴጦምያ ከ1512 ዓክልበ. ያሕል በፊት ስላልታዩ፣ ሂክሶስ እንደ ነበሩ አጠራጣሪ ነው።

This article is issued from Wikipedia. The text is licensed under Creative Commons - Attribution - Sharealike. Additional terms may apply for the media files.